Connect with us

Africa

የዓለም ማኅበረሰብ ጥሪና የኢሳያስ መልስ

Published

on

የዓለም ማኅበረሰብ ጥሪና የኢሳያስ መልስ

የዓለም ማኅበረሰብ ጥሪና የኢሳያስ መልስ | በኃይሉ ሚዴቅሳ ፍስሃጽዮን

1993 ዓ.ም. የበጋ ወራት ፣በዚያ ሰሞን ኤርትራ በተሰኘች አርበ ጠባብ አገር ቁዘማ በዝቷል፡፡ከተሞቿ የመከፋት ደመና ካንዣበባቸው ሰንበት ብሏል፡፡አስመራ፣ምጽዋ፣ከረን፣ተሰነይ፣ሜንደፍራ… ድብርት ተጫጭኗቸዋል፡፡ባለሥልጣናት ቁጭት ውስጥ ናቸው፡፡ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ተደርጎ አስርሺህዎች ካለቁ ዓመት አልሞላውም፡፡ጦርነቱ በኤርትራ ተሸናፊነት መጠናቀቁና ከሰብዓዊ ኪሳራ እስከ ኢኮኖሚያዊ ድቀት ማድረሱ ያልተገመተ ነበር፡፡እናቶች መርዷቸውን እንኳ የሚነግራቸው መንግሥት አላገኙም፡፡አባቶች ያለጡዋሪ ቀባሪ ያስቀራቸውን መንግሥት እየረገሙ ናቸው፡፡ወጣቶች በአስገዳጅ ወታደራዊ ምልመላ ወደ ሳዋ መጋዛቸውን ቀጥለዋል፡፡የአገሪቱ ታዛዎች ወደ ውስጥ የሚፈስ እንባ እያረሰረሳቸው ነው፡፡

ኢሳይያስ አፈወርቂ የተባሉት የአገሪቱ መሪ ምን እያሰቡ እንደሆነ አይታወቅም፡፡በ1989 ዓ.ም የተረቀቀውን ሕገመንግሥት ገቢራዊ ላለማድረግ ከኢትዮጵያ ጋር የገቡበትን ጦርነት ሰበብ አድርገውት ነበር፡፡ጦርነቱ ከተጠናቀቀ ከዓመት በኋላም ሰነዱን ሥራ ላይ ለማዋል ፍላጎት አላሳዩም፡፡ይህ ጉዳይ የሁለት አካላትን ትኩረት ሳበ፡፡የጋዜጠኞችንና የተራማጅ ባለሥልጣናትን! በአንድ ወገን የአገሪቱ ጋዜጦች፣የወታደራዊ ሽንፈቱን ቁጭት እየተረኩ ነው፡፡የዚህ ሁሉ ችግር መንስኤም ፕሬዚዳንቱ እንደሆኑ እያተቱ ነው፡፡በሌላ በኩል ደግሞ የኢሳይያስ የካቢኔ አባላትና የበረሃው ዘመን ጓዶች ምን እናድርግ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ በምስጢር ተደራጁ፡፡በድምሩ 15 ናቸው፡፡በተለምዶ G-15 እየተባሉ ይጠራሉ፡፡ Group 15 እንደማለት!!

እነዚህ ሁለት ወገኖች ተናበቡ፡፡ባለሥልጣናቱ አለቃቸውን ‹‹ሕገወጥ ነው፤ምርጫ እንዳይካሄድ እየከለከለ ነው፤የታገልንለት አጀንዳ በአንድ ሰው መዳፍ ሥር ወድቋል፤ ብሔራዊ ክብራችንን ባዋረደ ጦርት ውስጥ እንድንሳተፍ አድርጎናል›› ብለው ወቀሱ፡፡

በመጀመሪያዎቹ የውይይታቸው ወቅቶች ከአስመራ ወጣ ያሉ ቦታዎችን ይመርጡ ነበር፡፡ግንኙነታቸው ፍጹም ምስጢራዊ እንዲሆን ጥረት ሲያደርጉ ቆዩ፡፡ከአቶ ኢሳይያስ ጋር ለመወያየትም ሞከሩ፡፡ነገሩ ውሃ ቢወቅጡት እምቦጭ ሆነባቸው፡፡የፕሬዚዳንቱ የቅርብ ወዳጅ የነበሩት እነ መሐመድ ሸሪፎና ጴጥሮስ ሰሎሞን ሳይቀሩ አለቃቸውን ናቁ፡፡ተነሱባቸውም፡፡እነርሱ ዘንድ‹‹አምባገነን›› እያሉ መናገርም ቀላል ሆነ፡፡

በመጨረሻ ይህንን ሐሳባቸውን በጋዜጦች ማውጣት ጀመሩ፡፡ ‹‹የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሕገወጥ ነው›› ሲሉም በጽሁፍ፣በቃለ መጠይቅና በብዙ መንገዶች ኢሳይያስ አፈወርቁን መሞገት ቀጠሉ፡፡በአስመራ የጋዜጣ ገበያ ደራ፡፡በየማለዳው የሚነበቡ የከተማዋ ጋዜጦች ዋነኛ አጀንዳቸው የፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ፈላጭ ቆራጭነት ሆነ፡፡

በዚህ መሀል ቤተመንግሥቱ የተከፈተበትን ዘመቻ ለመከላከል ‹‹ባዶ ሰልስተ (03)›› የሚባል ጸረ-ፕሮፓጋንዳ ተቋም መሠረተ፡፡አንደብርሃን ወልደጊዮርጊስ የተባሉ የቀድሞ አምባሳደርም የዚህ ሥራ ዋና ኃላፊ ሆኑ፡፡ለወራትም ጋዜጠኞቹንና ባለሥልጣናቱን ‹‹የሲአይኤ ወኪሎችና ከሀዲዎች›› በማለት ሲያጣጥል ሰነበተ፡፡ሆኖም የሚፈለገውን ግብ አልመታም፡፡የተቃውሞው ዘመቻ ተቀባይነቱ እያየለ መጣ፡፡በዚህ መልኩ ከመጋቢት እስከ መስከረም ሰነበቱ፡፡

በመጨረሻም ኢሳይያስ አፈወርቂ በትራቸውን አነሱ፡፡መስከረም ስምንት እና ዘጠኝ 1994 ዓ.ም በዘመቻ ማሰር ጀመሩ፡፡ጋዜጠኞቹም ባለሥልጣናቱም እየተለቀሙ በባሕር ኃይል ኮንቴይነሮች ውስጥ ታጎሩ፡፡ወደ አሜሪካ ከኮበለሉት ሶስት ባለሥልጣናትና 11ኛው ሰዓት ላይ ወደ ኢሳይያስ ጎራ ከተቀላቀለው ሙሐመድ ብርሃን በስተቀር ሌሎቹ ዘብጥያ ወረዱ፡፡18 ጋዜጠኞችም ተለቃቅመው ታሰሩ፡፡በእነዚያ የሁለት ቀን ዘመቻዎች የታሰሩት እነዚያ ኤርትራዊያን እስካሁን የት እንዳሉ አይታወቅም፡፡ክስም አልተመሠረተባቸው፡፡ቤተሰብም ሆነ ወዳጅ ጠይቋቸውም አያውቅ፡፡

መስከረም 1-1994 ዓ.ም አልቃኢዳ በአሜሪካ ያደረሰው የሽብር ጥቃት ደግሞ በኤርትራ የሆነው ነገር እዚህ ግባ የሚባል አለማቀፋዊ ትኩረት እንዳያገኝ ምክንያት ሆነ፡፡አቶ ኢሳይያስ በግርግር ባላንጣዎቻቸውን አስረው ከዲፕሎማሲያዊ ውግዘት ለጊዜውም ቢሆን አምልጠው ነበር፡፡

ይህ ከሆነ ከ18 ዓመታት በኋላ የተባበሩት መንግሥታት ሰሞኑን መግለጫ አውጥቷል፡፡‹‹ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር እርቅ ካወረደችም በኋላ በአስመራው መንግሥት ላይ የባሕርይ ለውጥ አልመጣም›› የሚል ይዘት ያለው ይህ መግለጫ፣ወታደራዊ ግዳጅም ሆነ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ረገጣ እንደቀጠለ መሆኑን ገልጧል፡፡

እዚህ ጋር የድርጅቱን መግለጫ ተንተርሰን ጥያቄዎችን እናንሳ፡፡ከመግለጫው መረዳት እንደሚቻለው የመንግሥታቱን ድርጅት፣‹‹የአስመራ መንግሥት ከአዲስ አበባ አቻው ጋር እርቅ ማውረዱ፣በኤርትራ የፖለቲካ ለውጦች ይፈጠራሉ ብሎ እንዲጠብቅ›› አድርጎታል፡፡ግን አልሆነም፡፡

ኤርትራና የተባበሩት መንግሥታት

የኤርትራ መንግሥት የሰብዓዊ መብት አያያዝ አሳስቦናል የሚሉ ተቋማት እየበረከቱ ሲመጡ በ2014 (እ.ኤ.አ) የተባበሩት መንግሥታት ጉዳዩን የሚከታተል አጣሪ ኮሚሽን አቋቋመ፡፡ማይክ ስሚዝ የተባሉ የአውስትራሊያ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰርም የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ሆኑ፡፡ለኮሚሽኑ ተልዕኮ የኤርትራ መንግሥት እንዲተባበር ድርጅቱ ጥሪ አቀረበ፡፡የአቶ ኢሳይያስ አስተዳደር ግን እንኳንም ሊተባበር ኮሚሽኑ ኤርትራም እንዳይገባ ከለከለ፡፡በመሆኑም ሁኔታውን ለማጥናት ሌሎች መንገዶችን ለመከተል ተገደደ፡፡

በመጨረሻም በሰኔ 2015 (እ.ኤ.አ) ባለ 483 ገጽ ሪፖርት አወጣ፡፡ በሪፖርቱም ልጅ አባቱን፣ሚስት ባሏን እንዲሰልሉ የሚያደርግ መዋቅር መዘርጋቱንና በአጠቃላይ ማኅበራዊ አለመተማመን ያለበት ኅብረተሰብ እንደተፈጠረና እስር፣ማሰቃየት ወዘተ በፕሬዚዳንት ኢሳይያስና በባለሟሎቻቸው እውቅና እንደሚከናወን ዘረዘረ፡፡ለዚህም 550 ቃለ መጠይቆችንና 160 የጽሁፍ ማስረጃዎችን አቀረበ፡፡

የኢሳይያስ ቤተመንግሥት በድርጊቱ ተበሳጨ፡፡‹‹በርቀት የተሰነደ አሉባልታ›› ሲልም ሪፖርቱን አጣጣለው፡፡በዚህ ሳያበቃም ሪፖረቱን ሕዝብ እንዲቃወመው ቅስቀሳ ጀመረ፡፡በአገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ 300ሺህ ኤርትራዊያንም ይህንን ሪፖርት በፊርማቸው እንዲያወግዙ ሰነድ አዘጋጀ፡፡በውጭ የሚኖር ኤርትራዊ ይህንን ፊርማ ካላስቀመጠ በዜግነቱ ማግኘት የሚገባውን ቪዛና መሠል የጉዞ ማስረጃዎች እንደሚከለከልና እንደ አገር ከሀዲ እንደሚቆጠር በአጽንኦት አሳወቀ፡፡በዚህ መልኩ የተጀመረው ዘመቻ፣በጀኔቫ የኮሚሽኑን ውሳኔ የሚያወግዝ ሰልፍ እንዲካሄድ አደረገ፡፡ሆኖም እዚህ ግባ የሚባል ለውጥ አላመጣም፡፡ይልቁንም የኢሳይያስ መንግሥት ተቃዋሚዎች በሌላ ወገን ያደረጉት ሰልፍ የተሻለ ሽፋን አግኝቶ የመገናኛብዙሃን ትኩረት ሳበ፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ያቋቋመው የኤርትራ ጉዳዮች አጣሪ ኮሚሽን አሁንም በሥራ ላይ ያለ ቢሆንም ከኤርትራ መንግሥት ጋር ወደ ሥምምነት የሚያመጣው ነጥብ ላይ አልደረሰም፡፡ባሳለፍነው ወር አጋማሽ ወደ ኤርትራ ተጉዞ የተመለሰው የኮሚሽኑ ልዑክ አሁንም ‹‹ተስፋ የሚደረግበት ከባቢ አለመኖሩን›› ተናግሯል፡፡18 አባላት ያሉትን ልዑክ መርተው አስመራ የገቡት Christof Heynes ለአሜሪካ ድምጽ እንግሊዝኛው አገልግሎት እንደተናገሩት፣በኤርትራ የሚታየው ነገር አሳሳቢ ነው፡፡

‹‹ብዙ ነገር ጠየቅናቸው፡፡በ1994 የታሰሩት ሰዎች የትናቸው?በሕይወትስ አሉ ወይ? መቼስ ትፈቷቸዋላችሁ?አስገዳጁን ወታደራዊ ምልመላስ መቼ ታቆማላችሁ? የሚሉና መሠል ጥያቄዎችን በተለያዩ የማግባቢያ መንገዶች ጠይቀናቸው ነበር፡፡አንዱንም አልመለሱንም፤የአፈወርቂ መንግሥት ለዴሞክራሲም ሆነ ለሰብዓዊ መብት ጥበቃ ዛሬም አልተዘጋጀም››ብለዋል፡፡

ለኮሚሽኑ አባላት ማብራሪያ እንዲሰጡ በኤርትራ መንግሥት የተመደቡት ተስፋሚካኤል ገራሀቱ በአንፃሩ፣ኮሚሽኑንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን አውግዘው በአገራቸው ምንም ዓይነት የሰብዓዊ መብት ጥሰት (ቀውስ) እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ስለታሰሩት ሰዎችም ቃል አልተነፈሱም፡፡

አንዱን ይዞ ሌላውን መጣል፤ የኢሳይያስ ዓመል

ዓለማቀፍ መገናኛብዙሃንና የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ሁሉ ኤርትራ ላይ እንዲያተኩር ያደረገው ክስተት ከላይ በመግቢያዬ ላይ የገለጽሁት የባለሥልጣናትና የጋዜጠኞች መታሰር እንዲሁም ወታደራዊ ግዳጅ ናቸው፡፡

18 ጋዜጠኞችና 11 ባለሥልጣናት የታሰሩበት አጋጣሚ ዛሬም መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ከሁሉም የሚያስገርመው ደግሞ አቶ ኢሳይያስ ሚስትን አስረው ባልን አገልጋያቸው፣ወንድምን አስረው እህትን ታዛዣቸው የሚያደርጉበት መንገድ ነው፡፡

ለምሳሌ የኤርትራ ሬድዮና ቴሌቭዥን ዋና ዳይሬክተር የነበረው ጋዜጠኛ ስዩም ተስፋይ በመስከረሙ ዘመቻ የታሰረ ነው፡፡እስካሁንም የት እንዳለ አይታወቅም፡፡የእርሱ ወንድም ዓለም ተስፋይ ግን በሕንድ የኤርትራ መንግሥት አምባሳደር ነው፡፡

ሰናይት ደበሳይ ታዋቂ የሻዕቢያ ታጋይ ነች፡፡ይህች ሴት በአቶ ኢሳይያስ ወታደሮች ተይዛ ከታሰረች ቆይታለች፡፡የት እንዳለችም አይታወቅም፡፡ባሏ አቶ በየነ ርዕሶም ግን በአቶ ኢሳይያስ ፊርማ ተሾመው በኬኒያ የኤርትራ አምባሳደር ናቸው፡፡እኒህ ሰው ከሁለት ዓመት በፊት ከአምባሳደር ዲና ሙፍቲ ጋር ቦክስ ቀረሽ ክርክር ሲያደርጉ በአንድ የኬኒያ ቴሌቭዥን ታይተው ነበር፡፡

በፈረንሳይ የኤርትራ አምባሳደር ሆነው የሚያገለግሉት የሃና ስምኦን እሕት ሩት ስምኦን (የአሶሽዬትድ ፕሬስ ጋዜጠኛ ነበረች) ለዓመታት ታስራ የተፈታችው በቅርቡ ነው፡፡ታዋቂው (የሲዊድን ዜግነት ያለው) ጋዜጠኛ ዳዊት ይስሃቅ በመስከረሙ ዘመቻ ቢታሰርም፣ ወንድሙ ቴድሮሰ ይስሃቅ በሻዕቢያ ደጋፊነቱና አስተባባሪነቱ ዝነኛ ነው፡፡

ይህንን ነው አንዱን ይሎ ሌላውን አንጠልጥሎ ያልኩት፡፡የአንድ ቤተሰብ አባላትን ወዳጅም ጠላትም አድርጎ መያዝ የሚያስችል ኢሳይያሳዊ ጥበብ ነው- አንዱን ጥሎ ሌላውን ማንጠልጠል፡፡

በኤርትራ ሰማይ ሥር እንዲህ ያሉ እስሮች እንደቀጠሉ ናቸው፡፡የዓለማቀፉ ማኅበረስብም ዛሬም የኢሳይያስን መንግሥት እየጠየቀ ነው፣‹‹እንደ ኢትዮጵያ ሁኑ፤እስረኞቹንም ፍቷቸው›› የሚለው ጥሪ ቀጥሏል፡፡ይሁን እንጂ ጥሪው በኢትዮጵያ ታይቷል የሚባለው መልካም ነገር በኤርትራ ላይ ይደገም ዘንድ አንድም ኢሳይያሳዊ ቅንነት፣አለያም ሕዝባዊ ንቃትና መደራጀት እንደሚያስፈልግ አይመክርም፡፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ

** ኢትዮ ጵያን የተመለከቱ የተለያዩ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዘኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close