Connect with us

Art and Culture

“ዘፈን” በመጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሜዎች ውስጥ!

Published

on

"ዘፈን" በመጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሜዎች ውስጥ!

“ዘፈን” በመጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሜዎች ውስጥ!

ከሠርፀ ፍሬስብሐት
ሚያዝያ ፳፻፲፩ ዓ.ም.
============
❄❄❄
“…የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፤ ‘ዘፈን’ በሚለው ቃል አጠቃቀም ምክንያት የተፈጠረው ችግር፣ የቃሉን ዐውዳዊ ንባብ ካለመረዳት የመነጨ እንደኾነ በማመን፤ ምዕመናን በየቤተክርስቲያናቸው፣ በመጽሐፍ ቅዱስ መምህሮቻቸው አማካኝነት፣ ትክክለኛ የቃሉን ዐውዳዊ መልዕክት በመገንዘብ መንፈሳዊ ሕይወታቸውን እንዲያንፁ ያስፈልጋል እንላለን፡፡”
❄❄❄

ከላይ ያነበባችሁት የመደምደሚያ ሐሳብ የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ሐሳብ ነው። ማኅበሩ ይህንን የጽሑፍ ምላሽ የሰጠው፣ የዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ፣ ሙዚቀኛ ዮናስ ጎርፌ Yonas Gorfe “ቤት ያጣው ቤተኛ” በሚል ርዕስ በጻፈው መጽሐፍ ሰበብነት ነው።

መጽሐፉ፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ በመደገፍ “ዘፈን እና ዘፋኝነት ኃጢኣት ነው፤” ለሚለው የማኅበረሰባችን የባጀ አባባል፣ ምክንያታዊ ምላሽ ለመስጠት የተጻፈ ነበር።

ይኹን እንጂ፣ መጽሐፉ ይዞት የተነሳው የመጽሐፍ ቅዱስ የዐማርኛ ትርጓሜን መሠረት ያደረገው ክርክር በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ካለማግኘቱም በላይ፣ ቁጣ የቀሰቀሰ ነበር።

በዚህ አከራካሪነቱ ምክንያት፣ አንድ ልዩ የውይይት መድረክ ተዘጋጅቶም ነበር። በዚህ መድረክ ላይ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ የትርጉም ሥራን እና የዚህን “ዘፈን” የተሰኘ ቃል መጽሐፍ ቅዱሳዊ የትርጉም አረዳድ ለማብራራት፣ የተገባ ሥልጣን ያለው “የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፤” የጽሑፍ ምላሽ ልኮ፣ ለታዳሚው ተነቦ ነበር።

እኔም በተለያዩ አጋጣሚዎች፣ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ሐሳቤን እንድገልፅ የተገደድኩባቸው አጋጣሚዎች በርካታ ከመኾናቸው አንፃር፣ ይህ የማኅበሩ ምላሽ ለጠያቂዎች ኹሉ እፎይታን እንደሚሰጥ በማመን፣ ከመጠነኛ አርትዖት ጋር፣ እነሆ፥ በዚህ የንባብ ሑዳድ ላይ እንዲህ አቅርቤላችኋለሁ።

#ማስታወሻ :- ጽሑፉ ረዘም ያለ እና ከመጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሜዎች ጋር ማመሳከር የሚፈልግ በመኾኑ፥ በትዕግስት፣ በአስተውሎት እና ከቁጣ በራቀ ስሜት አንብቡት። አደራ!!!
🌿🌿🌿
I. አጠቃላይ ግንዛቤ፡-
=============
*በዓለም ላይ 6,901 ቋንቋዎች ይነገራሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በሀገራችን ከ80 ያላነሱ ቋንቋዎች እንደሚነገሩ ሲታወቅ፤ እነዚህ ቋንቋዎች፣ በዓለምም ኾነ በኢትዮጵያ፣ አብዛኛዎቹ ከሚሊዮኖች በላይ የሚናገሯቸው ቋንቋዎች ናቸው፡፡

*በዓለም አቀፍ ደረጃ መጽሐፍ ቅዱስ በ541 ቋንቋዎች ተተርጉሟል፡፡ በኢትዮጵያ ደግሞ በ9 ቋንቋዎች ተተርጉሟል፡፡

*የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሥራ፤ ከማንኛውም የሥነ-ጽሑፍ የትርጉም ሥራ ይለያል፡፡ በአተረጓጎም ሒደቱም ኾነ ጥንቃቄው እጅግ አድካሚ፣ ረጅም ጊዜ የሚወስድ እና ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚጠይቅ ውድ የትርጉም ሥራ ነው፡፡

*ምንም ያህል ጥንቃቄ ቢደረግም፤ ከቀዳሚዎቹ የጽርዕ እና የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱሶች ወደ ተቀባይ ቋንቋ የሚደረገው የትርጉም ሥራ፤ በተለየያዩ ምክንያቶች በሚፈለገው ልክ ትክክለኛውን የትርጓሜ መልክ ይዞ የማይገኝባቸው ኹኔታዎች በርካታ ናቸው፡፡

*ይህም የሚኾንባቸው ምክንያቶች፤ በተቀባዩ ቋንቋ የሚኖረው የባህል፣ የዕምነት፣ የአመለካከት፣ የአስተሳሰብ ልዩነቶች የሚፈጥሩት ተግዳሮት ነው፡፡ ወደ ተቀባዩ ቋንቋ በትክክል ለመተርጎም በሚደረግ ጥረት፤ ቃሉ የያዘውን መልዕክት የሚወክል ትክክለኛ ቃል፣ በኹሉም ቋንቋዎች ውስጥ ፈልጎ ማግኘት ከባድ በመኾኑ፣ በሚቀርብ አማራጭ ለመተርጎም በሚደረግ ጥረት፣ ብዙ የዐውድ መፋለሶች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡

II. የኢትዮጵያ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሜ ሥራዎች፡-
=============================

ሀ- የ1954 ዓ.ም. የዐማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ዕትም፡-
————————————————————
*በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ተወዳጅ የኾነው፣ በብዛት የተሰራጨው የዐማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ የ1954 ዓ.ም. ዕትም የኾነው መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡

*የዚህ መጽሐፍ ቅዱስ የትርጉም ሥራ የበላይ ጠባቂ የነበሩት ዐፄ ኃይለ ሥላሴ፤ የሰዋስው ሥርዓትን በጠበቀ መልኩ ከመሠረታዊ ቋንቋው (ከዕብራይስጡ እና ከጽርዑ) ጋር ዕየተያየ እንዲዘጋጅ በማሰብ፣ በ1939 ዓ.ም. ሥራውን የሚያከናውኑ ሊቃውንትን በማሰባሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ የትርጉም ኮሚቴ በማቋቋም የትርጉም ሥራው እንዲካሔድ አድርገዋል፡፡

*ኮሚቴው ሥራውን ለአምስት ዓመታት ሲያካሂድ ቆይቶ በ1944 ዓ.ም. በማጠናቀቁ የመጀመሪያው ዕትም በ1953 ዓ.ም. በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ታትሞ ለሕዝብ ተሠራጭቷል፡፡

*የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበርም 66 መጽሐፍት የያዘ መጽሐፍ ቅዱስ ከ1954 (1962 እ.ኤ.አ.) ጀምሮ በዘመናዊ ኅትመት በውጪ ሀገር እያሳተመ እስካኹን ድረስ አገልግሎት እንዲሠጥ አድርጓል፡፡

*የ1954ቱ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ የትርጉም ሥራው ቃል በቃል (literary translation) የተባለውን የትርጉም ሥልት የተከተለ ነው፡፡ በቃላት አጠቃቀሙ፣ በፈሊጣዊ አነጋገር አጠቃቀሱ፣ በዐረፍተ ነገር አወቃቀሩ ኹሉ፤ የምንጩን ቋንቋ የዕብራይጡን እና የግሪኩን ይመስለዋል፡፡

*ይኹን እንጂ፣ ከላይ እንደተባለው የትርጉም ይዘቱ ለምንጭ ቋንቋዎቹ የቀረበ ቢኾንም፤ መልዕክቱን ለመረዳት ውስብስብ የኾነ የቃላት፣ የሐረጋት እና የተምሳሌት ይዘቶች እንደነበሩበት መካድ አይቻልም፡፡

ለ- የ1980 እና 1997 ዓ.ም. ቀለል ባለ ዐማርኛ የተተረጎሙት መጽሐፍ ቅዱሶች፡-
——————————————————

*የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ፕሮጀክት ቀርፆ፣ ትርጓሚዎች መድቦ፣ ያስተረጎመው የ1980 ዓ.ም. ትርጉም የኾነው የዐማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ፤ “Good News Bible” የሚባለውን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ የትርጉም ሥራ መሠረት በማድረግ፤ በተለይ ዐማርኛ ቋንቋ ኹለተኛ ቋንቋቸው ለኾኑ የኅበረተሰብ ክፍሎች አረዳድ በሚኾን መልኩ ታስቦበት፣ በቀላል ዐማርኛ የተሰናዳ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡

*ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ከአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት እንዲሻሻል በቀረበበት ጥያቄ መሠረት፣ በ1997 ዓ.ም. በተሻሻለው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲተካ ኾኗል፡፡ የትርጉም ሥልቱም “መልዕክት ተኮር” (Meaning Based) የሚባለውን ዓይነት የትርጉም ሥልት የተከተለ ነው፡፡

*ይህም ማለት፤ ቃላትን በእኩያ ቃላት ለመተርጎም ከመሞከር ይልቅ፣ መልዕክቱን በቀላሉ በሚገልጹ ሐረጋት ወይም ዐረፍተ ነገሮች ወይም ምሳሌዎችን ተጠቅሞ መተርጎምን መሠረት ያደረገ ነው ማለት ነው፡፡
❄❄❄

III. መዝሙር፣ ዘፈን፣ ጭፈራ በዐማርኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሜዎች ውስጥ፡-
====================================

*በመጽሐፍ ቅዱስ የቃላት ትርጓሜ ላይ አደናጋሪ ነገር ሲፈጠር፤ ወደ ምንጭ መጽሐፍ ቅዱሱ፤ ማለትም ወደ ዕብራይሰጡ እና ወደ ጽርዑ በመሔድ ዋናውን የቃል ግንድ የሚያብራራ ዐውዳዊ ትርጓሜ ይፈለጋል ወይም ይጠናል፡፡

*በዐዲስ ኪዳን ውስጥ ከመዝሙር፣ ከዘፈን፣ ወይም ከጭፈራ ጋር የተያያዙ ሐሳቦች የተጠቀሱባቸው ክፍሎች፣ የግሪኩን ወይም የዕብራይስጡን መጽሐፍ ቅዱስ መሠረት አድርገን ለመመልከት ብንሞክር፤ ቃላቱ የሚገኙባቸው ክፍሎች አጠቃላይ መልዕክቶች የሚከተሉት ኾነው እናገኛቸዋለን፡፡

1. ‘ሳልሞስ’፡- የውዳሴ መዝሙር (ኤፌ. 5፡ 19፣ ቆላ. 3፡16 ወ.ዘ.ተ)

2. ‘ዖዴ’፡- መንፈሳዊ ዜማ (ኤፌ. 5፡19፣ ቆላ.3፡16፣ ራዕ.5፡9፣ ራዕ. 15፡3)

3. ‘ኮሞስ’፡- ምግብና መጠጥ የበዛበት፣ ሥነ-ምግባር የጎደለው የአምልኮ ጭፈራ (ሮሜ. 13፡13፣ ገላ. 5፡21፣ 1.ጴጥ. 4፡3)

4. ‘ኮሮስ’፡- ቃሉ የኅብረት ውዝዋዜ የሚል ፍቺ የያዘ ሲኾን፤ (ሉቃ.15፡25 ላይ ብቻ ይገኛል፡፡)

5. ‘ኦርኬኦማይ’፡- መጨፈር፣ መወዛወዝ የሚል ፍቺ አለው፡፡ (ማቴ.11፡17፣ ማቴ. 14፡6፣ ማር.6፡22፣ ሉቃ. 7፡32) ናቸው፡፡

*‘ኮሞስ’፣ ‘ኮሮስ’፣ ‘ኦርኬኦማይ’ የሚገኙባቸው (ከተ.ቁ.3-5 ያሉት) የግሪክ ቃላት እና ትርጓሜዎቻቸውን በ1954 ዓ.ም.ቱ ዕትም እና በ1997 ዓ.ም.ቱ ዕትም ላይ እንዴት እንደተገለፁ ማየት መልካም ነው፡፡

i. ‘ኮሞስ'(ቃሉ -የግሪክ)፡-
=============
*(ሮሜ. 13፡13፣) ላይ የሚገኘውን ጥቅስ፣ የ1953ቱ ትርጉም፤ “ዘፈን እና” ብሎ ሲፈታው፤ የ1997ቱ ዕትም ደግሞ “ቅጥ ያጣ ፈንጠዝያ” ሲል ይፈታዋል፡፡

*(ገላ.5፡21) ላይ የሚገኘውን ጥቅስ ደግሞ፤ የ1954ቱ ዕትም “ዘፋኝነት” ሲለው፤ የ1997ቱ ዕትም በበኩሉ፣ “ቅጥ ያጣ ፈንጠዝያ” ይለዋል፡፡

*(1.ጴጥ. 4፡3) የ1954ቱ ትርጉም “በዘፈንም” ሲለው፤ የ1997ቱ ዕትም “ቅጥ ባጣ ፈንጠዝያ” ይለዋል፡፡

ii. ኮሮስ (ቃሉ- የግሪክ)፡-
=======
*(ሉቃ.15፡25) ላይ የሚገኘው ቃል የ1953ቱ ትርጉም “የዘፈን ድምጽ” ሲለው፣ የ1997 ዓ.ም. ዕትም ደግሞ፤ “የጭፈራ ድምጽ” ይለዋል፡፡

iii. ኦርኬኦማይ (ቃሉ-የግሪክ)፡-
==========
*(ማቴ. 14፡6) ላይ ያለውን የ1954 ዓ.ም. ትርጉሙ “ዘፈነች” ሲለው፤ የ1997ቱ ዕትም ደግሞ “እየጨፈረች” ይለዋል፡፡

*(ሉቃ. 7፡32) ላይ ያለው በ1954 ዓ.ም. ትርጉሙ “አልዘፈናችሁም” ሲል፣ የ1997 ዓ.ም. ትርጉም፣ “አልጨፈራችሁም” ብሎ ይገልፀዋል፡፡

❄❄❄IV.ማጠቃለያ❄❄❄
🌿🌿🌿

*ከዚህ ዝርዝር ሐሳብ እንደምንረዳው፤ የ1954 ዓ.ም. የዐማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ “ኮሞስ”፣ “ኮሮስ”፣ እና “ኦርኬኦማይ” የተባሉት ሦስት የግሪክ ቃላት በአንድ ዓይነት መንገድ፣ ማለትም “ዘፈን” በሚል ቃል ይተርጉመዋል፡፡ ይህ የትርጉም አካሔድ፤በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚታወቅ ነገርን፤ አጠቃላይ በኾነ ቃል የመተርጎም ዘዴን የተከተለ መኾኑን ያሳያል፡፡

*ስለኾነም፣ ይህንን መጽሐፍ ቅዱስ ስንጠቀም፤ ዐውዱን በትክክል ማጥናት ወይም ከመጽሐፍ ቅዱስ መምህር መረዳት እንደሚያስፈልግ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ምክንያቱም፤ “ከዝሙት፣ ጣዖትን ከማምለክ፣ ከቅንኣት፣ ከአድመኝነት፣ ከመለያየት፣ ከመናፍቅነት፣ ከምቀኝነት፣ ከመግደል፣ ወ.ዘ.ተ.” ጋር ተሠልፎ የቀረበው “ዘፈን” እና፣ በጠፋው ልጅ ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሰው “ዘፈን”፣ አንድ ዓይነት ፍቺ ወይም መልዕክት ሊኖራቸው እንደማይችል መገንዘብ ስለማያዳግት ነው፡፡

*በሌላ ወገን ቀለል ባለ አማርኛ የተዘጋጀው መጽሐፍ ቅዱስ የተከተለው የትርጉም ሥልት፣ “መልዕክት ተኮር” በመኾኑ፤ የቃላትን ዐውዳዊ ትርጉም በግልጽ ለማውጣት ይጥራል፡፡ በዚህም መሠረት የ1954 ዓ.ም. ዕትም፤ እሳቤው እንግዳ የኾነ አንድ መልዕክት “ኮሞስ” ከሌሎች ጋር ባለ የተወሰነ የፍቺ ዝምድና ምክንያት በተመሳሳይ አንድ ቃል የተረጎመውን ቀለል ያለው የዐማርኛ ትርጉም በሐረግ ደረጃ በማብራራት መልዕክቱን ያስተላልፋል፡፡

*በተወሰነ ደረጃ በሦስቱ የግሪክ ቃላት መካከል ያለውን ልዩነት ለማሳየትም ይሞክራል፡፡ በእንግሊዝኛ ቋንቋ RSV, NIV, CEV, ወ.ዘ.ተ. በመባል የሚታወቁት አያሌ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በአቀራረባቸው፣ በአተረጓጎም ሥልታቸው ወ.ዘ.ተ. እንደሚለያዩ ኹሉ፤ ቀለል ባለ ዐማርኛ የተዘጋጀው መጽሐፍ ቅዱስ እና የቀድሞው የ1954 ዓ.ም. የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሜ በቋንቋ አጠቃቀማቸው፣ በሚከተሉት የትርጉም ሥልት፣ ታሳቢ ባደረጓቸው ተጠቃሚዎቻቸው እና ለዕብራይስጡ እና ለግሪኩ ቋንቋዎች ባላቸው የቀረቤታ ደረጃ ይለያያሉ፡፡ ኾኖም፤ ኹለቱም ትርጉሞች የታለመላቸውን አገልግሎት በተገቢው መንገድ እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

*ስለኾነም፤ የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፤ “ዘፈን” በሚለው ቃል አጠቃቀም ምክንያት የተፈጠረው ችግር፣ የቃሉን ዐውዳዊ ንባብ ካለመረዳት የመነጨ እንደኾነ በማመን፣ ምዕመናን በየቤተክርስቲያናቸው፣ በመጽሐፍ ቅዱስ መምህሮቻቸው አማካኝነት፣ ትክክለኛ የቃሉን ዐውዳዊ መልዕክት በመገንዘብ መንፈሳዊ ሕይወታቸውን እንዲያንፁ ያስፈልጋል እንላለን፡፡

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close