Connect with us

Art and Culture

በበግ ቤት በግ ገባ | ከአሳዬ ደርቤ

Published

on

በበግ ቤት በግ ገባ | ከአሳዬ ደርቤ

በበግ ቤት በግ ገባ | ከአሳዬ ደርቤ

ለመጀመሪያ ጊዜ ለፋሲካ በዓል በግ መግዛት የቻለው ካድሬው ጎረቤቴ አካብዶ ሊሞት ነው፡፡

ሰውዬው እዚህ ሶሻል ሚዲያው ላይ ‹‹በዶክተር ዐቢይ አመራር የተመዘገቡ እልፍ-አዕላፍ ለውጦች›› በሚል ርዕስ በሚጽፋቸው አርቲክሎቹ ይታወቃል፡፡

እናም በእያንዳንዱ ጽሑፍ ድርጅቱ የሚከፈለውን ገንዘብ ሲያጠራቅም ከርሞ በገዛው በግ ኮንዶሚንየማችንን ሲንጠው ዋለ፡፡ በዚህ ዓይነት መኪና ቢገዛ’ማ ‹‹ጣሪያ ላይ ወጥቼ ካልነዳሁ›› ማለቱ አይቀርም ነበር፡፡

ሥጋውን ከመብላት በላይ በጉን ለእኔ ማሳየት ትልቅ እርካታ እንደሚያመጣለት ጠንቅቄ ስለምረዳ… የቤቴን በር ዘግቼ ዝም አልኩት፡፡ ይሄን ማድረጌ ግን ኮሪደሩ ላይ እንዳይፈነጭ አልከለከለውም፡፡ ይልቅስ ‹‹ቤትን ዘግቶ ‘ለውጥ የለም’ ከማለት አስቀድሞ ወጣ ብሎ የለውጡን ትሩፋቶች መመልከት ያስፈልጋል›› እያለ ጡርንባውን መንፋቱን ተያይዞታል፡፡

የመስኮቴን መጋረጃ በስሱ ገለጥ አድርጌ ስመለከት… ከአጠገቡ ያለውን ‹በግ› አርዶ ሊበላው ሳይሆን ሰርዶ ሊያበላው የገዛው ይመስል ‹‹መግደል መሸነፍ ነው›› የሚል ታፔላ አንገቱ ላይ አንጠልጥሎበታል፡፡ (አይ የካድሬ ነገር…)

ቀጫጫ ሚስቱ አሮጌ ሞባይል አንከርፍፋ ከፊት ለፊቱ ቆማለች፡፡ እናም የሆነ ብርቅዬ አራዊት የገዛ ይመስል በጉን ተደግፎ ‹‹ፌስቡክ ላይ የምለጥፈው ስለሆነ አሪፍ ፎቶ አንሺኝ›› ይላታል፡፡

‹‹ፌስቡክ ላይ ደግሞ ምን ሊያደርግህል ነው የምትለጥፈው?›› ስትለው በአገጩ ወደ እኔ ቤት እያመለከተ ‹‹በራቸውን ዘግተው የተቀመጡ ምቀኞች ፌስቡካቸውንም ዘግተው ይቀመጡ እንደሁ አያቸዋለሁ›› እያለ ይደሰኩራል፡፡

የበግ ሥጋ የመብላትም ሆነ የማየት እድሉን አግኝቶ የማያውቀውን የአምስት ዓመት ልጁን ‹‹ና በግህን አቅፈህ ፎቶ ተነሳ›› ሲለው ‹‹እንቢየው ይበላኛል›› ብሎ መለሰለት፡፡

ባለቤቱ መዓት ፎቶ ካነሳችው በኋላ ‹‹እኔና አንተም የሰርጋችን ቀን ይሄን ያህል ፎቶ አልተነሳን›› ብላው ሞባይሉን ስትመልስለት ‹‹ለሰርጋችን እኮ የሚታረድ በግ አልገዛንም›› በማለት ብዙ ፎቶ ያልተነሱበትን ምክንያት ነገራት፡፡

እዚህ ላይ እውነት ብሏል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ በጉልባን የተጋቡ ጥንዶች እነሱ ናቸው፡፡

መጋረጃውን ሸፍዬ ወደ መቀመጫዬ ልመለስ ስል ሚስቱ ‹‹እስከ እሁድ ድረስ የት ልታሳድረው ነው?›› ስትለው ድምጹን ከፍ አድርጎ ‹‹ባለ-አደራ ተቋቁሞ የለ እንዴ ለእነሱ ሰጥቻቸው እመጣለሁ›› የሚል አሽሙር ተናግሮ ከጣሪያ በላይ ገለፈጠ፡፡

ከቤቴ ወጥቼ ለውጡ ያመጣለትን ጸጋ ለማየት አለመፈለጌን ሲረዳ፣ ሰፈራችን ውስጥ ምንም አይነት ሳር በሌለበት ሁኔታ የብሎኩ ነዋሪዎች ላይ ጉራውን ለመንፋት ሲል ብቻ…. ‹‹እስኪመሽ ድረስ ሳር አብልቼው መጣሁ›› ብሏት በጉን እየገተተ ወጣ፡፡ እኛም ለተወሰነ ጊዜ ከእሱ ጉራ ተገላግለን ቆየን፡፡

ከአንድ ሰዓት በኋላ ግን በጉን ትቶ ገመዱን እየወዘወዘ ተመለሰ፡፡

ይሄንንም ያየች ሚስቱ በድንጋጤ ተውጣ ‹‹በጉ’ስ?›› በማለት ስትጠይቀው ‹‹ፎቶውን ፌስቡክ ላይ ለመለጠፍ ስታገል ገመዱን በጥሰው ወሰዱት›› የሚል አጭር መልስ ሰጥቷት ለመታነቅ የቸኮለ ይመስል በጥድፊያ ወደ ቤቱ ገባ፡፡ እሷም ተከትላው ገብታ ‹‹ደግሞ ለበግ ምን ብለህ ነው ራስህን የምታጠፋው? አንተ ሰላም ሁን እንጂ ጻፍ ጻፍ አድረገህ ለዳግማይ ትንሳኤ ታርድልናለህ!›› እያለች ስታጽናናው ቆየች፡፡
.
ምሽት ላይ ታዲያ በደብረ-ብርሃን በጉ ፈንታ ‹‹ባለበግ›› የሚል ጽሑፍ የታተመበትን የደብረ-ብርሃን ብርድ ልብሱን ለብሶ ከሚስቱ ጋር ኮሪደሩ ላይ እየተንጎራደዴ ‹‹በመንግስታችን የተመዘገቡ ሃገራዊ ለውጦችን ሲያደናቅፍ መክረሙ አልበቃው ብሎ በቤታችን ውስጥ እየታዩ ያሉትን የለውጥ ጭላንጭሎች ማክሰም ሲጀምር’ማ ዝም ብዬ አላየውም›› ይላታል፡፡

ይሄንን ጥቃት የፈጸመው እሱ መሆኑን በምን አወቅህ?›› ትለዋለች
‹‹ከእሱ ውጭ በጌን ሊወስድ የሚችል ማንም አይኖርም ስልሽ››
‹‹ግን እኮ ከቤት አልወጣም›› ብላ ስትመልስለት ደግሞ እንዲህ በማለት ሊያሳምናት ይሞክራል፡፡

‹‹ባለፈው ዓመት የትግራይ ነጋዴዎች የጫኑትን አንድ አይሱዙ ሙሉ በግ መንገድ ላይ ያስቀረባቸው ቤቱ ቁጭ ብሎ መስሎኝ››
በሚሰጣት መልስ እኔ ‹‹ኪ ኪ ኪ ኪ…›› እያልኩ ስስቅ፣ ‹በግ› ለመባል ሁለት ቀንድና ሁለት እግር ብቻ የሚጎድለው ዶሮዬ ሳቄን ተከትሎ ‹‹ኩኩኩኡኡ›› የሚል ድምጽ አሰማ፡፡

በዚህን ጊዜም ተወዳጁ ጎረቤቴ ‹‹የበግ ድምጽ ሰማሁ ልበል?›› በማለት ይጠይቃል፡፡
እሷ ‹‹ኧረ የዶሮ ነው›› ትለዋለች፡፡

ሆኖም ግን የካድሬነት ዓመል የራስን ሃሳብ ለማውራት እንጂ የሌሎችን ሃሳብ ለመስማት የማይፈቅድ በመሆኑ ‹‹ከመቼ ወዲህ ነው በዚህ ሰዓት ዶሮ መጮህ የጀመረው?›› እያለ ይሞግታታል፡፡

መልካም በዓል!

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close