Connect with us

Ethiopia

የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ 25/1988ን የሚያሻሽል ረቂቅ አዋጅ ለውይይት ቀረበ

Published

on

የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ 25/1988ን የሚያሻሽል ረቂቅ አዋጅ ለውይይት ቀረበ

በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ስር የተደራጀው የዳኝነት ስርዓት ማሻሻያ አማካሪ ጉባዔ የፌዴራል የፍርድ ቤቶች አዋጅ 25/88ን ለማሻሻል ያዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ሰሞኑን ለውይይት አቀረበ፡፡

ፌዴራል ፍርድ ቤቶች አሁን ላለባቸው የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር አንደኛው ምክንያት አደረጃጀታቸው መሆኑን በጥናት የለየው አማካሪ ጉባዔ ችግሩን ለመቅረፍ አዋጁ መሻሻል እንዳለበት ምክረ ሃሳብ አቅርቧል፡፡ ይንንም ተከትሎ ማሻሻያ ረቂቅ ዓዋጅ ተዘጋጅቶ ለተጨማሪ ግብዓት ለውይይት እንዲቀርብ አድርጓል፡፡

በውይይቱ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አመራሮችና ዳኞች፣ የህግ ባለሙያዎች፣ ጠበቆች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈውበታል፡፡ ለውይይት መነሻ እንዲሆንም ማሻሻያ አዋጁ ያካተታቸው ለውጦች በአቶ አብደላ አሊ ቀርቧል፡፡

ረቂቅ አዋጁ የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት በተመለከተ ለሰበር ውሳኔዎች ተገማች አለመሆንና ለአቤቱታዎች መብዛት ምክንያት ነው የተባለው የመሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት የሚልው ጽንሰ ሃሳብ ግልጽ በሆነ መልኩ አለመተርጎሙ እና አመላካቾች አለመቀመጣቸው መሆኑን በመረዳት የመሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ትርጉም በረቂቅ አዋጁ እንዲካተት ተደርጓል፡፡

ለሰበር ችሎት የሚቀርቡ ጉዳዮች ፍሰታቸው በየጊዜው እየጨመረ መምጣትን ለመቀነስ ግምታቸው አነስተኛ ዋጋ ያላቸውና በማህበራዊ ፍርድ ቤት የሚነሱ አነስተኛ የጉዳዮች ዓይነት እና መሰል ጉዳዮች ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት እንዳይቀርቡ ማድረግና መሰል ጉዳዮችን የሚዘረዝር መመሪያ ማውጣት አሁን ስራ ላይ የሌለ አዲስ ሃሳብ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

አጣሪ ችሎቱ በጠቅላይ ፍድ ቤት በመደበኛ ችሎት ባለ አምስት ዳኛ የታዩ ጉዳዮችን በሶስት ዳኛ በማየቱና ብዙዎቹን መዛግብት አያስቀርብም በማለት መዝጋቱ እንደችግር የተለየ መሆኑን በመጠቆም አጣሪ ችሎት ቀርቶ በባለ አምስት ዳኞች ሰበር ሰሚ ችሎት አንዲያተዩ የሚያስችል አንቀጾች ማካተቱም ተነግሯል፡፡

ማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ ከዘጠኝ ያላነሱ ዳኞች ስለሚሰየሙበት የሰበር ፓናል ችሎት ስለሚቋቋምበትና በችሎቱ ስለሚቀርቡ ጉዳዮች የሚዘረዝር ክፍልም መጨመሩ እንደዚሁ ተብራርቷል፡፡

በሌላ በኩል የፌዴራል መጀመሪያ እና ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፍትሃ ብሄር ዳኝነት ስልጣን ሽግሽግ አስፈላጊነትን በማብራራት የማሸጋሸጊያና የመሸጋገሪያ ድንጋጌዎችም አንደተጨመሩበት ተነግሯል፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በሶስት ዳኞች እስከ 20 ሚሊዮን ብር የሚደርሱና በገንዘብ የማይገመቱ የፍትሃ ብሔር ጉዳዮች ሁሉ እንዲያይ ስልጣን የሚሰጥ ሲሆን ከፍተኛው ፍርድ ቤት ደግሞ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸውን ጉዳዮች በመጀመሪያ ደረጃ የዳኝነት ስልጣን እና በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሚሰጡ ውሳኔዎችን በይግባኝ አንዲያይ ሃሳብ ቀርቦበታል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን ለመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት እየቀረቡ ካሉት የፌዴራል ያልሆኑ ጉዳዮችን በውክልና ለከተሞች ፍ/ቤቶች በማስተላለፍ የፍርድ ቤቱን የመዝገብ ፍሰትም መቀነስ እንዲቻል በረቂቅ አዋጁ ድንጋጌ ተበጅቶለታል፡፡

አዋጅ 25/88 ሽፋን ያልሰጠው የፌዴራል ከፍተኛና መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ምድብ ችሎቶች ተጠሪ ዳኞችና የችሎት ሰብሳቢ ዳኞች ስልጣንና ሃላፊነት በማሻሻያው እንዲካተት ተደርጓል፡፡

ረቂቅ አዋጁ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የስራ ጫናን ለማቃለል የመዛግብት ብዛት ዳኞች ሊሸከሙት ከሚችሉት ቁጥር በላይ በሚሆንበት ጊዜ ቀደም ሲል ዳኝነትን በመልካም ስነ ምግባር ይሰሩ ከነበሩ መካከል ተመርጠው ስራውን እንዲያግዙ ለማድረግ ስልጣን የሚሰጥ አንቀጽ ተቀርጾ መካተቱ ተመልክቷል፡፡

በመጨረሻም የጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉባዔ ስያሜና የአባላቱን ስብስብ የሚያሻሽል ሃሳብም ቀርቦበታል፡፡

የውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች ረቂቅ አዋጁ ስለያዛቸው ሃሳቦች እና ሊካተቱ የሚገቡ ጉዳዮችን በስፋት ያነሱ ሲሆን የአዋጅ ማሻሻያ ንኡስ ኮሚቴ የተሰጡትን አስተያየቶችና የሃሳብ ግብአቶች በማካተት ለሁለተኛ ጊዜ ለተጨማሪ ሃሰብ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚያቀርብ ውይይቱን የመሩት የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዝደንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ እና የአማካሪ ጉባዔው ሊቀመንበር ገልጸዋል፡፡

(ምንጭ:-ፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት)

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close