Connect with us

Ethiopia

የተጣሉ ልጆቻቸው፣ የሚሸማገሉ አባቶቻቸው

Published

on

የተጣሉ ልጆቻቸው፣ የሚሸማገሉ አባቶቻቸው | ከአሳዬ ደርቤ

የተጣሉ ልጆቻቸው፣ የሚሸማገሉ አባቶቻቸው | ከአሳዬ ደርቤ

የእኛ አባቶች በአገራቸው ላይ ቀርቶ በልጆቻቸው እጣ-ፈንታ ላይ የመወሰን አቅም የላቸውም፡፡ ይልቅስ በመንግስታችን እና በሙህራኖቻችን ትዕዛዝ ከወላጆቻቸው እጣ ፈንታ ተሻግረው የአገራቸውንና የክልላቸውን ህልውና የሚወስኑ ወጣቶች ‹‹ቄሮ፣ ፋኖ፣ ዘርማ፣ ኤጄቶ… ›› በሚል የመንጋ ስም በየከልሉ ተቀፍቅፈዋል፡፡

ወጣቶቹ አፍላ እድሜ ላይ የሚገኙና በራሳቸው ጭንቅላት ክፉና ደጉን ማገናዘብ የማይችሉ በመሆናቸው… እንደ ወታደር ‹‹ጀግኖቼ›› እና ‹‹መሪዎቼ›› ከሚሏቸው አክቲቪስቶች ታስቦ የሚሰጣቸውን ትዕዛዝ ተግባራዊ ያደርጋሉ፡፡

ማንኛውም ወታደር ከአለቆቹ የሚሰጠውን ግዳጅ ያለምንም ጥያቄ ተፈጻሚ እንደሚያደርገው ሁሉ… ወጣቶቹም ‹‹የኛ›› ከሚሏቸው ሰዎች የሚመጣን ትዕዛዝ በራሳቸው ሳይመዝኑ ይተገብራሉ፡፡

ስለሆነም የየጎጡ አክቲቪስቶች ወይንም ደግሞ መንግስታት የተቃቃሩ እለት መንጋዎቹ በየቀያቸው ግጭት ፈጣሪና አፈናቃይ ይሆናሉ፡፡ መሪዎቻቸው የተስማሙ ቀን ደግሞ ጥምረት መስርተው በጋራ ይቆማሉ፡፡

እናም በአጠቃላይ ባሁኑ ጊዜ በአንዱ ክልልና በሌላው ክልል መሃከል የሚታየው መነካከስ በኤሊቶችና በመሪዎች ላይ የተመሰረተ እንጂ በህዝብና ህዝብ ወይንም ደግሞ በወጣትና ወጣት የሚፈጠሩ እንዳልሆኑ ግልጽ ነው፡፡

የኦሮሞና የአማራ፣ የአማራና የትግራይ፣ የኦሮሞና የሶማሌ፣ የሲዳማና የወላይታ ህዝቦች እንደ ህዝብ በጅምላ ተጣልተው አያውቁም፡፡ ለመጣላት የሚያበቃም በቂ ምክንያትም የላቸውም፡፡ ወደ ግጭትና ወደ ጦርነት የሚገቡት መንግስታቸውንና አክቲቪስቶቻቸውን ተከትለው ነው፡፡

ሆኖም ግን ባሳለፍናቸው ጊዜያት እነዚህ በብሔር የተደራጁት ሃይሎች መግባባት ባለመፈለጋቸው በእነሱ ትዕዛዝ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች እንዲፈናቀሉ፣ እርስ በእርሱ እንዲገዳደሉና፣ የአገራችንም ህልውና አደጋ ውስጥ እንዲገባ ሁኗል፡፡

ከዚህ ሁሉ ችግር በኋላ ታዲያ ‹‹ጃስ ጃስ›› ሲባባሉ የከረሙት የክልል መንግስታት የምክር-ቤት ስብሰባቸውን በኢህአዴግ ደረጃ ከማድረጋቸው ጋር ተያይዞ የህዝብ ለህዝብ መድረኮችን እያዘጋጁ ይገኛሉ፡፡ እናም መሪዎቻችን ይሄንን ለማድረግ የተነሳሱት በእነሱ መሃከል ያለውን ልዩነት ሙሉ በሙሉ እስወግደውና አገራችንንም ወደ አንድነት ለማምጣት አስበው ከሆነ… ተቀዳሚ ሥራቸው መሆን ያለበት በብሔር ተደራጅተው በጎጣቸው ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ማግኘት የቻሉ አክቲቪስቶችንና ፓርቲዎችን ማስማማት ይመስለኛል፡፡

ኢህአዴግ ግን የችግሩን ባለቤት ለይቶ ትክክለኛውን መፍትሔ ከማምጣት ይልቅ በከንቱ መባዘን የሚወድ በመሆኑ… የክፋት ነብያቱን ትቶ ተከታዮቻቸውን፣ የግጭት መምህራኑን ችላ ብሎ ደቀ-መዝሙራቱን፣ የጦር መሪውን ትቶ መንጋውን በመሰብሰብ የአገራችንን እክል ሊፈታ ደፋ ቀና እያለ ነው፡፡

እንደኔ እንደኔ ግን… በሁለት አገራት መሃከል የተፈጠረን ግጭት መሪዎቻቸውን በማሸማገል እንጂ ወታደሮቻቸውን በማነጋገር ስምምነት ላይ መድረስ እንደማይቻለው ሁሉ… ‹‹አንድን ክልል እንወክላለን›› የሚሉ ሙህራኖች/አክቲቪስቶች በተለያዩ ምክንያቶች የሚለኩሷቸው ግብግቦች ተከታዮቻቸውንና ወላጆቻቸውን በማነጋገር እልባት ማምጣት የሚቻል አይመስለኝም፡፡

አንዳንድ ጊዜ አብረው የሚኖሩና በድንበር የሚዋሰኑ ህዝቦች በግጦሽ መሬቶች ወይንም ደግሞ ለመስኖና ለመጠጥ በሚውሉ የውሃ ምንጮች ሊጣሉ ይችላሉ፡፡ እናም በእንዲህ መሰል ምክንያቶች የሚፈጠሩ ግጭቶችን ተጠቃሚውን ህብረተሰብ በማነጋገር መፍታት ይቻል ይሆናል፡፡

የእኛ ወቅታዊ አለመግባባቶች ግን በሪሶርስ እጥረት ወይንም ደግሞ በዘር ልዩነት ህብረተሰቡ በራሱ ጊዜ የሚቀሰቅሳቸው አይደሉም፡፡ የግጭቶቻቸው መንስኤዎች ሁሉ ውጫዊ ናቸው፡፡

የእኛ ህዝብ ያለውን ሪሶርስ ተካፍሎ ከመኖርም አልፎ በትዳርና በጉርብትና ተቀላቅሎ መኖርን የለመደ በመሆኑ የሚያጣሉት ሰዎች እንጂ በራሱ የሚጣላባቸው ችግሮች የሉትም፡፡ እንዲቀረፉለት የሚፈልጋቸው ችግሮች እንጂ….

እናም የሚያመልካቸው አክቲቪስቶቹና የሚያምናቸው መሪዎቹ ‹‹እንትና የሚባለው ብሔር አያትህን እንዲህ ያደረገ ጠላትህ ነውና….ከቀየህ ላይ ጨፍጭፈህ አባርረው›› ሲሉት አብሮት የኖረውን ጎረቤቱን ያፈናቅላል፡፡ ያገባትን ሚስቱን ይፈታል፡፡
‹‹ይሄ ብሔር ወዳጅህ ነው›› ሲሉት በአንድ መሬት ላይ ቀርቶ በአንድ ቤትም ውስጥ አብሮ መኖር ይጀምራል፡፡

በዚህም መሰረት መንግስታችን እራሱን ወደ አንድነት አምጥቶ… ከይስሙላ በጸዳ መልኩ የአገራችንን ወቅታዊ ችግር በዘላቂነት የመፍታት ቁርጠኝነቱ ካለው…. በራሳቸው ጊዜ የማይጣሉትን ህዝቦች ማቀራረቡን ትቶ፣ በቅድሚያ የተለያዩ የጠብ መንስኤዎች እየጠነሰሱ የሚያጣሏቸውን ግለሰቦችና ፓርቲዎች ማወያየት አለበት፡፡

ልዩ ልዩ መድረኮችን በማዘጋጀት አንዱን ብሔር በጠላትነት ፈርጀው የተመሰረቱ ብሔርተኛ ፓርቲዎችን በመሰብሰብ… ሌላውን ህዝብ በማጥላላት ላይ ያተኮረ ፖሊሲና ስትራቴጂያቸውን ሰርዘው፣ የራሳቸውን ህዝብ በማልማት ላይ እንዲመሰርቱ ማድረግ ሲችል ሁሉም ህዝቦች መቀራረብ ብቻ ሳይሆን እንደ ቀድሞው መዛመድ ይጀምራሉ፡፡

ጥላቻና ግጭት እየጠመቁ ህብረተሰቡን የሚያጣሉና አገርን የሚከፋፍሉ አክቲቪስቶች ወይንም ደግሞ ሙህራኖች የሚቀራረቡባቸው መድረኮችን አዘጋጅቶ ማስማማት ሲችል ቄሮና ፋኖ ከጥፋት ወጥተው የልማት ቡድኖች ይሆናሉ፡፡ የአማራ፣ የትግራይ፣ የኦሮሞ፣ የሶማሊያ፣ የደቡብ ህዝቦች…. በአንድ አገር ላይ የሚኖሩ ብቻ ሳይሆኑ አገራቸውን የሚያስከብሩ ሆነው ይገኛሉ፡፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ

** ኢትዮ ጵያን የተመለከቱ የተለያዩ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዘኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close