Connect with us

Ethiopia

ኦሮ አማራ የፓርቲዎች ሳይኾን የህዝቦች … | ከስናፍቅሽ አዲስ

Published

on

ኦሮ አማራ የፓርቲዎች ሳይኾን የህዝቦች ... | ከስናፍቅሽ አዲስ

ኦሮ አማራ የፓርቲዎች ሳይኾን የህዝቦች፤ የኦዴፓና የአዴፓ ሳይኾን የአማራና የኦሮሞ ድግስ ቢኾን በየጅረቱ መማማል ባላስፈለገው ነበር፤ እናንተ ህዝቡን ደህና አድርጋችሁ ምሩት፤ ህዝቡ ትናንትም አንድ ነበር ነገም አንድ ኾኖ ይኖራል፡፡ **** ከስናፍቅሽ አዲስ

ኦሮማራ በሚለው ፍልስፍና ብዙም የምመሰጥ ሰው አይደለሁም፡፡ ምክንያቴ ሁለቱ ታላላቅ ህዝቦች ከተስማሙ የኢትዮጵያ ጉዳይ አልጋ ባልጋ ነው በሚለው ትንሽ መርህ ስለማላምን ነው፡፡

ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና ስለማቀነቅን የአንድ ዜጋ ኩርፊያ የሀገር ኩርፊያ መስሎ ይሰማኛል፡፡ እናም መርሁን ያን ያህል አላጨበጭብለትም፡፡ ያም ሆኖ ኦሮሞና አማራ ማንና ማን ናቸው የሚለው ግን የኔ ብቻ ሳይሆን የብዙዎች ጥያቄ ኾኗል፡፡ ትናንት ስለ አማራና ተጋሩ የህወሃት ትግል ማበስሪያ ላይ ታድመው ብዙ ሲተነትኑ የኖሩት ዛሬ አዲስ የስራ መደብ አግኝተዋል፡፡

በግሌ በህዝቦች መካከል ትስስር ለመፍጠር የሚሰራ ስራ ያን ያክል ጉዳት ያመጣል የሚል እምነት ግን የለኝም፡፡ ዓላማው ምንም ይሁን ምን፤ ምን አገባት የማያስብለኝ ጥያቄ ግን አማራና ኦሮሞ አዴፓ እና ኦዲፒ ከሆኑ ህወሃትና የትግራይ ህዝብ ይለያያሉ ብሎ መስበክ አይጋጭም ወይ ነው?

አቶ ለማና አቶ ገዱ ጀምረውት አሁን በዶክተር አምባቸውና በአቶ ሽመልስ የቀጠለው ግንኙነት የክልል መንግስታት የሥራ ግንኙነት ከመሆን እንዲዘል ከተፈለገ ህዝባዊ መሆን አለበት፡፡ ለእኔ ከዶክተር አምባቸው እና ከአቶ ሽመልስ ዝምድና ይልቅ የጃዋር መሐመድ እና የጌታቸው ሽፈራሁ፤ የሕዝቃኤል ጋቢሳ እና የሙሉቀን ተስፋው፣ የደረጄና የአያሌው መንበር ወዳጅነት ህዝብን ባህር ከፍሎ የማሻገር አቅም አለው ብዬ አምናለሁ፡፡

አማራና ኦሮሞ ሰፊ ናቸው፡፡ የዘንድሮን ምርጫ ስለመሻገራቸው ጭንቅ ላይ ባሉ ሁለት ደካማ የዘመናት አገልጋይ ፓርቲዎች የሚወከሉ አይመስለኝም፡፡ እናም እንዲህ ያለው ግንኙነት ህዝብን መሠረት ቢያደርግ፤ እንዲህ ያለው ግንኙነት ዓላማው የፓርቲዎችን የምርጫ አሸናፊነት ማረጋገጫ ሳይሆን ጠንካራ ሀገር መገንባት አድርጎ የሚሰራ ቢሆን ይመረጣል፡፡

አምቦ ያስተናገደችው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ድግስ በመንፈስ ደረጃ ጥሩ ነው፤ ህዝቦች በጋራ ለመኖር ወዳጅነታቸውን የሚያጠናክሩባቸው መድረኮች ሁሌም መልካም ጎናቸው ጎልቶ ሊታየን ይገባል፡፡ ዘላቂና ስኬታማ እንዲሆኑ ግን በየጅረቱ ከመማማል የሚያወጣን ህዝባዊ መሠረት እንዲይዙ ማድረግ ነው፡፡ ኦሮ አማራ የፓርቲዎች ሳይኾን የህዝቦች ጉዳይ ነው፡፡ ህዝቦች መክረው ህዝቦች ቃል ተገባብተው ህዝቦች መተሳሰራቸውን አምነው የሚያጠነክሩት ቃል ኪዳን መሆን አለበት፡፡

ኦዴፓ እና አዴፓ እንደ እግር ኳስ በየሜዳቸው የመልስ ጨዋታ እያደረጉ ድግስ ሲመላለሱ ቢኖሩ ውጤቱ ብዙም አጥጋቢ አይሆንም፡፡ ውጤቱን ለማሳመር ህዝቡን ማሳተፍና ህዝቡን ባለቤት ማድረግ ነው፡፡ ህዝብ ማለት ሹመኞች የሚፈልጉት፣ ለመሪዎች የቀረበ ሳይሆን ህዝቡ የሚያደምጠው ህዝብ የኔ የሚለው መሆን አለበት፡፡ አማራና ኦሮሞ ኢህአዴግ የሚያለያያቸው ኢህአዴግ የሚያስታርቃቸው አይደሉም፡፡ አማራና ኦሮሞ ትናንትም ጠንካራ መሠረት ያለው ግንኙነት የፈጠራቸው አንድ ህዝቦች ናቸው፡፡ ነገም ይሄው ይቀጥላል፡፡ ይሄንን ማየት የሚፈልግ መንግሥት ጥሩ አድርጎ የሚመራት ሀገር ካለች ይህ እውነት ያለ ችግር ይኖራል፡፡

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close