Connect with us

Ethiopia

በአንድ አክቲቪስት ትንፋሽ ከሚፈርሰው ኦሮ-ማራ ይልቅ ኢትዮጵያ ትቅደም

Published

on

በአንድ አክቲቪስት ትንፋሽ ከሚፈርሰው ኦሮ-ማራ ይልቅ ኢትዮጵያ ትቅደም

አሳዬ ደርቤ | በአንድ አክቲቪስት ትንፋሽ ከሚፈርሰው ኦሮ-ማራ ይልቅ ኢትዮጵያ ትቅደም 

የኢህአዴግ ምክር ቤት ስብሰባውን ካደረገ በኋላ ያወጣው መግለጫ ያው እንደ ወትሮው በትርኪምርኪ ቃላት የተሞላ መስሎ ቢታይም ከዚያ በኋላ ግን እየታዩ ያሉት ነገሮች በተወሰነ መልኩም ቢሆን ተስማማቶ መውጣቱን የሚያመላክቱ ሆነዋል፡፡

ለማስረጃም ያህል የለውጡ መንግስት ወደ ሥልጣን ከመጣበት ጊዜ አንስቶ ኢህአዴግን በግላጭ ሲተቹት የነበሩት ዶክተር ደብረ-ጽዮን በአቶ ለማ መሸኛ ላይ የተናገሩትን ማስታወስ ይቻላል፡፡ የንግግራቸውን መግቢያ በኢፌዲሪም ጀመሩት በኢህዲሪ….

ዶክተሩ በዚያ መድረክ ላይ ያሰሙት ንግግር በቅንነት የተሞላና ተስፋን የሚሰጥ ነው፡፡ እንደ ከዚያ ቀደሙ መንግስት የሰራቸውን ህጸጾች እያጣቀሱ ጠቅላይ ሚኒስቴሩን ከመጣጣል ይልቅ ‹‹የተፈጠሩት ችግሮች በየትኛውም ለውጥ ውስጥ የሚከሰቱ መሆናቸውን አምነው… ‹‹መግባባታችንን እና አንድነታችን አጠናክረን እንፈታቸዋለን›› ሲሉ መሰማታቸው ፍሬያማ ስብሰባ እንዳካሄዱ የሚገልጽ ሁኗል፡፡

ሲቀጥል ደግሞ የራሱን እያሳረረ የጎረቤቱን ሲያማስል የከረመው ‹‹ኢህአዴግ›› በኦዴፓ አማካኝነት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶችን የሚያጠናክሩ መድረኮችን በአምቦ ከተማ ለመጀመር ማሰቡም ተጨማሪ መገለጫ ሊሆን የሚችል ነው፡፡

እንደሚታወቀው የዶክተር አቢይ አመራር ወደ ሥልጣን ከመጣበት ጊዜ አንስቶ አንድ ዓመት ያለፈው ቢሆንም ከአገር ይልቅ የራሱን ስብዕና ለመገንባት ሲል ሕዝቡን በትኖ ቀጠናውን ለማስተሳሰር ሲሯሯጥ ነው የከረመው፡፡

በክልሎች መሃከል የጦርነት ነጋሪት እየተጎሰመ… በምስራቅ አፍሪካ ጉዳይ ላይ ሲፈተፍት ብዙ ጊዜዎችን አባክኗል፡፡ በዚህም ሳቢያ በብሔር ብሔረሰቦች መሃከል ያለው ልዩነት ከመቼውም ጊዜ በላይ አድጎ እለታዊ ዜናዎቻችን በግጭትና በስደት ሲሞሉ ሰንብተዋል፡፡

ስለሆነም ኢህአዴግ በስብሰባው ላይ ይሄንን ችግር አይቶ የህዝብ ለህዝብ መድረኮችን ማሰናዳት መጀመሩ ልናበረታታው የሚገባ በጎ ተግባር ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

ሆኖም ግን መድረኩ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ላይ ተወስኖ ሌላውን የሚያገል እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ የመድረኮቹ የመጨረሻ ግብም ታላቋን ኢትዮጵያን የሚያስቀጥል እንጂ በጃዋር ትንፋሽ ሊደመሰስ የሚችለው ኦሮማራን የሚመልስ መሆን የለበትም፡፡

ምክንያቱም በዚህ ዘመን ሙሉ ባልሆነ ህብረት ሙሉ የሆነች አገር ማስተዳደር አይቻልም፡፡ ኦሮሞ ብቻውን እርስ በእርሱ ቢተባበር ኦሮሚያን እንጂ ኢትዮጵያን ማስተዳደር አይችልም፡፡ በኦሮ-ማራ ጥምረትም አማራ እና ኦሮሚያን እንጂ ትግራይንና ቤኒሻንጉልን መግዛት አይቻልም፡፡ የኢትዮጵያን አንድነት ማስቀጠል የሚቻለው ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በአገራዊ ስሜት ማደራጀትና ማስተሳሰር ሲቻል ብቻ ነው፡፡

ለዚህ ደግሞ አምቦ ላይ ሊጀመር የታሰበው መድረክ አድማሱን አስፍቶ በሁሉም አካባቢዎች መድረስ አለበት፡፡

አማራ እና ኦሮሚያ፣ አምቦና ጎንደር ላይ ቁጭ ብለው ሊመክሩ…. ትግራይና አማራ ደግሞ መቀሌና ባህር-ዳር ላይ ተገናኝተው ችግራቸውን ሊፈቱ ይገባል፡፡ ከዚህም አልፎ እንደ ብሔር ብሔረሰቦች ቀን ለይምሰል ሳይሆን ችግሮቻችንን አውርተን እርቅ የምንፈጽምባቸው መድረኮች በሁሉም የክልል ከተሞች ላይ መደረግ ይኖርበታል፡፡ ዋነኛ አገራዊ ችግሮቻችንን ለመፍታት የሚባክን ጊዜና በጀት ጥቅም ላይ እንደዋለ እንጂ በከንቱ እንደጠፋ የሚቆጠር ስላልሆነ እውነተኛ ውይይቶች በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች ከተሞች ላይ ሊዘጋጁ ይገባል፡፡

በሌላ መልኩ ደግሞ የፌደራል መንግስቱም ሆነ የክልል መንግስታት ለዓመታት የተገነባ አንድነት በትንሽ ድርጊት ሊደመሰስ እንደሚችል ተገንዝበው ራሳቸውን ከራስ-ወዳድነትና ከስግብግብነት ማቀብ አለባቸው፡፡ ‹‹ባለጊዜ ነኝ›› ወይንም ደግሞ ‹‹ሰፊ ህዝብ አለኝ›› በሚል ስሜት የሚተላለፉ ውሳኔዎች ከትርፋቸው ይልቅ ኪሳራቸው እንደሚያመዝን ለማወቅ ያሳለፍነውን አንድ ዓመት ብቻ መመልከት በቂ ነው›› እላለሁ፡፡

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close