Connect with us

Ethiopia

የአቶ ለማ ሽሽት? | በማዕረግ ጌታቸው

Published

on

የአቶ ለማ ሽሽት? | በማዕረግ ጌታቸው

የአቶ ለማ ሽሽት? | በማዕረግ ጌታቸው

ሰውየው የለውጥ ኃይል ከሚባለው ቡድን ውስጥ የተሻሉ ፖለቲከኛ መሆናቸው አያከራክርም፡፡ ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር)ያደመቁት የፖለቲካ ሰማይ መጠሪያው “ቲም ለማ” መሆኑም ለዚህ ምስክር ነው፡፡ ብዙ ተናጋሪ አይደሉም ይባላል፡፡ አንድ የኢህአዴግ አመራር እንዳጫወተኝ ባለፈው ዓመት በነበረው 17 ቀናት በፈጀው የድርጅቱ “ጥልቅ ታህድሶ ” ስብሰባ ላይ አብዛኛው አመራር መደማመጥ ተስኖት ሲጨቃጨቅ አቶ ለማ ትንፍሽ አላሉም፡፡ በጣት የሚቆጠሩ አስተያየቶችን የሰጡትም እሳቸውን የሚመለከቱ በመሆናቸው ተገደው ነበር፡፡ የኦቦ ለማ የፖለቲካ ዝምታ እራስን ከማግለል የሚቀዳ አይደለም ፡፡ ይልቁኑ ጨዋታን አሰቀድሞ ከመረዳት ጋር ይያዛል፡፡

ሰውየው በኢህአዴግ ሜዳ ላይ የሚካሄደው ጨዋታ የቱንም ያህል ቢከብዳቸው ውጤት ማስመዝገብ እንደሚችሉ ግን እርግጠኛ ነበሩ፡፡ ወዲህ አቶ ኃይለማሪያም አልቻሉም የሚል ግምገማ በኢህአዴግ ቤት ይደመጣል ወዲያ በጀዋር መሐመድ የሚመራው የኦሮሚያ ተቃውሞ ሀገር ሊያፈርስ ከጫፍ ደርሷል፡፡ የኦቦ ለማ ስሌት ትክክል ነበር ፡፡ኃይለማሪያምን የሚያሰናበት ህዝባዊ አመፅ ሊተካ የሚችለው ሰው የኦሮሞ ተወላጅን ብቻ ነው፡፡ ዝምተኛው ፖለቲከኛ ይህን ዕድል ለራሳቸው ሊጠቀሙበት አልፈለጉም፡፡ እራሳቸው የሚዘውሩትን ፓርቲ ስብስበው ሊቀመንበር እንመረጥ አሉ፡፡ ለምን? የሚል ጥያቄ ከበርካቶች ተነሳ፡፡ የፓርላማ አባል ስላልሆነኩ ጠቅላይ ሚኒስትር የመሆን ዕድል ሊያመልጠን ነው ሲሉ መለሱ፡፡

ቅኔው ያለው እዚህ ላይ ነው፡፡ አቶ ኃይለማሪያም ከስልጣን እንደሚወርዱ ለሚረዳ ሰው ቀጣዩ መሪ ከኦሮሚያና ኦሮሚያ ብቻ እንደሚሆን አከራካሪ አልነበረም፡፡ ለዚህ ሁለት ምክንያቶችን ብቻ መጥቀስ በቂ ነው፡፡ የመጀመሪያው ሀገሪቱን ወደ ቀደመ ሰላሟ ለመመለስ ከአምስት ክልሎች ጋር የሚዋሰነውን ኦሮሚያ ሰላም ማድረግ ምንም ጥያቄ አልነበረውም፡፡ ለዚህ ደግሞ ኦሮሞን ወደ መሪነት ማምጣት የውዴታ ግዴታ ነበር ፡፡ ሌላው ከኦሮሞ ታሪካዊ ጥያቄ ጋር የሚተሳሰር ነው፡፡

የሰሜን ኢትዮጵያ ፖለቲካ ሲዘውራት በኖረች ሀገር ኦሮሞ ሁሌም ተገዥ ነው ተብሎ እየተሰበከ ደመቀ መኮንን ጠቅላይ ሚኒሰትር ይሆናል ብሎ መጠበቅ ለጎበዝ ፖለቲከኛ የዋህነት ነው፡፡ በዚህ መነሻ ኦቦ ለማ መቶ ፐርሰንት ቀጣዩ የኢትዮጵያ መሪ ኦሮሞ እንደሚሆን እርገጠኛ ነበሩ ፡፡ የዝመተኛው መሪ ከኦህዴድ ሊቀመንበርነት መልቀቅ ሰሙ ይህ ቢሆንም ወርቁ ሌላ ነው፡፡

ኦቦ ለማ ከኦህዴድ ሊቀመንበርነት የለቀቁት የፓርላማ አባልነታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትርነት ሰለሚያግዳቸው አይመስልም ፡፡ ደብረፂዎን (ዶ/ር) የክልሉ ምክር ቤት አባል ሳይሆኑ በፓርቲያቸው ተመርጠው ትግራይን እንዲስተዳድሩ ዕድል ሲሰጣቸው ተመልከተዋል፡፡ አቶ ኃይለማሪያም የፌደራል መንግስት ሹመት ካገኙ በኋላ በማማሙያ ምርጫ ፓርላማ እንደገቡም ያውቃሉ፡፡ዝምተኛው ፖለቲከኛ ሀገር የመምራት ፍላጎት ቢኖራቸው ኑሮ የተወካዮች ምክር ቤት አባል አለመሆናቸው በኢህአዴግ ቤት ምንም ነበር ፡፡ ግን አልፈለጉም፡፡ ዐቢይ አህመድን (ዶ/ር)ከፊት አድረገው ጨዋታቸውን ቀጠሉ፡፡

መልከ መልካሙ ሰው ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሆኑ ኦቦ ለማን ቀድሞ በሽፍን መኪና ምኒሊክ ቤተ-መንግስት የደረሰ ሰው አልነበረም፡፡ ዝምተኛው ፖለቲከኛ ከዚህ በኋላ ከጅግጅጋ እስከ ሚኒሶታ ከጠቅላይ ሚኒስሩ ጋር አብረው ተጓዙ፡፡ ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) እራሳቸው እንዳረጋገጡልንም ኦቦ ለማ የቅርብ አማካሪቸውና ወንድማቸው ሆኑ፡፡ ግን ፖለቲካ የያዘው ፍቅር አይፀናም ፡፡ ዐቢይ አህመድ የሀገር መሪ ስለሆኑ ስልጣናቸው የሚመነጨው ከኢትዮጵያ ህዝብ ነው፡፡ የእሳቸው የፖለቲካ ህይወትም በዚህ ህዝብ መዳፍ ላይ ያለ መሆኑ አያከራክርም፡፡ ኦቦ ለማ በአንጻሩ የኦሮምያ ርዕሰ መስተዳደር ናቸው፡፡

የእሳቸው ፖለቲካ የሚመክነው በኦሮሞ ህዝብ ብቻና ብቻ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ዐቢይና ለማ በመስመር መለያየታቸው እውን ሆነ ፡፡የኦሮሞን ጥያቄ ከሌላው ክልል ጥያቄ ጋር ለማጣጣም አዳጋች እየሆነ ሲሄድ የአቶ ለማ ስም ማጠልሸት ጀመረ፡፡ ለዋናው የፖለቲካ መሰረታቸው የሚያወሩት ወሬ ሌላውን ኢትዮጵያዊ ያስከፋ ያዘ፡፡ ኦቦ ለማ መገርሳ ብዙዎች ተፈትነው በወደቁበት ኢትዮጵያዊና ክልላዊ ብሄርተኝት መኃል ተሰነቀሩ፡፡ የፖለቲካ ሰብዕናቸውም ጠርዝ ላይ ቆመ፡፡ ከለውጡ መሪዎች መካከል የተሻሉ የሚባሉት ኦቦ ለማ ሌላም ስጋት ገብቷቸዋል፡፡

ከዛሬ ነገ ይሻሻላል ያሉት የኢትዮጵያ ፖለቲካ በየቀኑ ወደ ውስብስብ ችግር እያመራ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሰውየውን የፖለቲካ መንገድ ፅልመት እንዲወጠው የማድረግ ኃይል አለው፡፡ እናም ኦቦ ለማ ከቆሙበት አደገኛ ጠርዝ ለመራቅም ሆነ በፖለቲካ ሰብዕናቸው ላይ ያጠላውን አጥፍቶ መጥፋት ለመሸሽ አዲስ ምሽግ አዘጋጁ ፡፡ አሉም፣ የሉም የሚባሉበትን ምቹ ስፍራ ለመያዝ ተንደረደሩ፡፡ አቶ መለስ አባዱላን ለቅጣት የላኩበትን ስፍራ ልኬ ነው አሉ፡፡ ስም አልባ ፖለቲከኞች የሚዋኙበትን ገንዳ መረጡ ፡፡ ተፈራን ዋልዋን ዘወር እናድርገው ሲባል የተዘጋጀውን ስፍራ ወደዱ፡፡ የፖለቲካ ብስለት የሌላቸው የተመደቡበት ሚኒስቴር ናፈቃቸው፡፡ እውነት ለመናገር አቶ ለማ የመከላክያ ሚኒስትር መሆናቸው አያሳስበኝም ። የሚያሳስበኝ የለውጥ ሞተር የተባሉት ሰው ከለውጡ ማፈግፈግ አንድምታው ምንድነው? የሚለው ነው ፡፡ አቶ ለማ መገርሳ የለውጥ ሞተር ከነበሩ የእሳቸው መራቅስ የሞተሩን መጥፋት ያመለክት ይሆን ? ብዙ ምላሽ የሌላቸው ጥያቄዎች አሁንም በዚችህ ሀገር ፖለቲካ ይተማሉ ፡፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ

** ኢትዮ ጵያን የተመለከቱ የተለያዩ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዘኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close