Connect with us

Africa

የአል በሽር እጣፈንታ | በኃይሉ ሚዴቅሳ ፍስሃጽዮን

Published

on

የአል በሽር እጣፈንታ | በኃይሉ ሚዴቅሳ ፍስሃጽዮን

የአል በሽር እጣፈንታ | በኃይሉ ሚዴቅሳ ፍስሃጽዮን

የቀድሞው የሱዳን ሰው አል በሽር ትናንት በአንድ ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግበት እስር ቤት ውስጥ ስለመግባታቸው በዓለማቀፍ መገናኛብዙሃን ሲዘገብ ነበር፡፡ ዛሬ አናዱሉ ኤጂንሲ እንዳስነበበው ግን እኒህ የቀድሞ ፕሬዚዳንት አለመታሰራቸውን ከቤተሰቦቻቸው አረጋግጧል፡፡ እናም ይህንን ዘገባ አምነን በቀጣይ አል በሽር እጣፈንታቸው ምን ይሆናል ብለን እንጠይቅ፡፡

ለዓለማቀፍ ፍርድ ቤት እንደማይሰጡ የመከላከያ ምክርቤቱ በግልጽ ተናግሯል፡፡ በሽር በዳርፉር ሰብዓዊ ኪሳራ አድርሰዋል በሚል በዓለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድቤት በጥብቅ የሚፈለጉና ማዘዣም የወጣባቸው ሰው ናቸው፡፡ ይህንን ተንተርሶ ከፍርድቤቱ ባለሟሎች ‹የተላልፈው ይሠጡን› ጥያቄ ቢቀርብም፣ ወታደራዊው መንግሥት ግን ‹‹በአገራችን ሕግ ይዳኛሉ እንጂ አሳልፈን አንሰጥም›› ብሏል፡፡

በርግጥ የፈነቀላቸው ጦር እንዳለው ለፍርድ ያቀርባቸዋል ወይ የሚለውም ኮርኳሪ ጥያቄ ነው፡፡ ይህ መፈንቅለ መንግሥት የተከናወነው በበሽር ታማኞች ነው፡፡ እነዚህ ቤተሰባዊ ቅርርብ አላቸው የሚባሉት የፈንቃዮቹ ወገኖች ምናልባት በቀድሞ አለቃቸው ላይ ላይጨክኑ ይችላሉ፡፡ ለዚያም ይመስላል የአይሲሲን ጥያቄ ያለማመንታት ውድቅ ያደጉት፡፡

ለዚህ መፈንቅለ መንግሥት የግል ጠባቂያቸው የሆነው The Rapid Support Forces የተሰኘው ከሠራዊቱ ዕዝ ውጭ የሆነው ጦር የፍንቀላው ተባባሪ ሆኗል፡፡ ምናልባትም በሽርን በኃይል ለማውረድ እንቅፋት ይሆናል ተብሎ የነበረው ይህ 70ሺህ የሚደርስ የፕሬዚዳንቱ የግል ጠባቂ ጦር ለፍንቀላው መተባበሩ፣ሰውዬው እስር ሳይሆን እንደ ሙጋቤ ያለ ዕረፍት እንዲሰጣቸው ከስምምነት ተደርሶ ሊሆን እንደሚችል ያስጠረጥራል፡፡

ይህን የሙጋቤ ሞዴል ልንለው እንችላለን፡፡ በዚምቧብዌ ለረዥም ጊዜያት የተካሄደው ሕዝባዊ አመጽ ወታደሩ ጣልቃ ገብቶ ሙጋቤን እንዲያነሳና ምናንጋግዋን እንዲያመጣ አድርጎታል፡፡ሰውዬው የርስት ያህል የያዙትን ሥልጣን በጠብመንጃ ከተነጠቁ በኋላ ጦሩ ‹‹በጥሩ ቦታ፣በመልካም ሁኔታ ተይዘዋል›› የሚል መግለጫ አወጥቶ ነበር፡፡በመጨረሻም ሙጋቤ በፖለቲካ ጉዳይ ምንም እንዳይናገሩ ተወስኖ ጡረታቸው ተከብሮላቸው እንዲኖሩ ሆኗል፡፡(ምናልባትም በኢትዮጵያ የተከናወነውም ተመሳሳይ ይመስላል፡፡

ምንም እንኳ ወታደሩ ጣልቃ ባይገባም (የዐቢይ አሕመድን ኮሎኔልነት ከግምት ካላስገባን በስተቀር ጦሩ አልተሳተፈም) አቶ ኃይለማርያም በሕዝባዊ አመጽ ተነስተው በጡረታ እንዲኖሩ መወሰኑ ሙጋቤ ሞዴል ልንለው እንችላለን)፡፡

በሱዳንም እንዲህ ያለ ነገር ሊደገም ይችላል፡፡አልበሽር እንደ ሮበርት ሙጋቤ የጡረታ ደመወዛቸውን እየበሉ በናይል ወንዝ ዳርቻ ጁምአ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ይህ የሚሆነው ግን በተለይ ሰውዬው ለፍርድ እንዲቀርቡ የሚያስገድድ ሕዝባዊ ግፊት (በተለይም በሱዳና ባለሙያዎች ማኅበር) ካልበረታ ነው፡፡በሽር ለሕግ ይቅረቡ የሚለው ኃይል ከጎለበተ ግን እንደ ግብጹ ሙባረክ ከርቸሌ መውረዳቸው አይቀርም፡፡ወይም ይህ ወታደራዊ መንግሥት በሕዝቡ ቅቡልነትን ለማግኘትና አቅሙን ለማሳየት በሽርን ለፍትሕ አደባባይ ሊያውላቸው ይችላል፡፡ያ ካልሆነ ግን የሙጋቤ እጣ ይገጥማቸዋል፡፡ከቤን አሊና ከጋዳፊ መንገድ ግን ተርፈዋል፡፡

ጥያቄው ግን ይህ የወታደሮች ሕብረት እንዳለው በሁለት ዓመት ውስጥ ሥልጣንን ለፖለቲከኞች ያስረክባል ወይ የሚለው ነው፡፡የአፍሪቃ ሕብረት ከ14 ቀን ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ሥልጣንን ለሲቪሎች አስረክቡ፤ኢ-ሕገመንግሥታዊ ናችሁ ብሏቸዋል፡፡በርግጥ የወታደራዊ ምክርቤቱ ሰብሳቢ ጀኔራል አብደል ሲቪሎቹ ከተስማሙ በወራትም ውስጥ ቢሆን ቤተመንግሥቱን አስረክበን ወደ ካምፓችን እንመለሳለን፤ሥልጣናችንና ሥራችን ጊዜያዊ ነው ብለዋል፡፡ሆኖም ይህ በየትኛውም መፈንቅለ መንግሥት ላይ የተለመደ በመሆኑ የጀኔራሉን ቃል በጥርጣሬ የተመለከቱ አልጠፉም፡፡

በ1967 በኢትዮጵያ ንጉሳዊ ሥርዓቱን ያወረደው ደርግ ‹‹ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት›› እያለ ከ10 ዓመታት በላይ ገዝቷል፡፡በግብጽም በተመሳሳይ ግርግር ነው ኤል ሲሲ ኮከብ የደረደረውን ፋቲጋቸውን ጥለው በቤተመንግሥቱ ጸንተው የቀሩት፡፡ይባስ ብሎም የረዥም ዘመናት ፕሬዚዳንት ለመሆን ሕገመንግሥት እያሻሻሉ ነው፡፡ይህ ዓይነት ነገር በሱዳን እንዳይደገም የሰጉ ሰዎችም ጦሩን መጠራጠራቸውን ቀጥለዋል፡፡አል በሽርን ወደ ፍርድ ቤት ካቀረባቸው ግን ከግብጹ አብዮት ጋር የተመጋገበ ድርጊት ይሆናል፡፡ምክንያቱም ሙባረክንና ሙርሲን ግብጽ አስራለችና!

 

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close