Connect with us

Ethiopia

የኢሕአዴግ ጉባኤ አዳዲስ ጉዳዮች! | በኃይሉ ሚዴቅሳ ፍስሃጽዮን

Published

on

የኢሕአዴግ ጉባኤ አዳዲስ ጉዳዮች! | በኃይሉ ሚዴቅሳ ፍስሃጽዮን

የአገሪቱ ገዥ ፓርቲ ያወጣውን ሶስት ገጽ መግለጫ አንብብ፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ነፍስ ዘርታ፣ መደመር ይሏት ነገር ውሃ በልቷት ታገኛለህ፡፡ ይህንን መግለጫ ስታነብ ከአራት ዓመታት በፊት የነበረው ኢሕአዴግ ትዝ ይልሃል? ያ ለጥልቅ ተሃድሶ የተዳረገውን ኢሕአዴግን አስታወስከው? በቃ እርሱን ከነነፍሱ ታገኘዋለህ፡፡

‹‹ከፖለቲካዊ ስራዎች አንፃር ሰፊ ውይይት ከተካሄደባቸው ጉዳዮች መካከል የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲና የአመራር አንድነት ይገኝበታል›› የሚለው ዓረፍተ ነገር ከመግለጫው ላይ የተወሰደ ነው፡፡ ይህ ቃል የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አንጓ መሆኑን ስነግርህ ከወደድከው ፍስሃ ከጠላኸው ደግሞ ሐዘን እየተሰማኝ ነው፡፡

‹‹የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲና የአመራር አንድነት›› ማለት ምን ማለት እንደሆነ ታውቀለህ? ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ማለት ይህ ነው! ይህስ ምን ማለት እንደሆነ ታውቃለህ? ድርጅታዊ ውሳኔዎች ከላይ እስከ ታች በዝግ በረኛነት ይፈፀማሉ ማለት ነው፡፡

ይህ መግለጫ አንድም ቦታ መደመር የሚለውን ቃል አለመግለጹ ደግሞ ይህ ሊቀመንበሩ ዐቢይ አሕመድ ፣‹‹ፍልስፍና›› ሲሉ የጠሩት ነገር በኢሕአዴግ ቤት ውድቅ እንደተደረገ ወይም የፖለቲካ ነፍስ የለህም ተብሎ እንደተጣለ ያስገነዝብሃል፡፡መደመር ማትማቲክስ እንጂ ፖለቲካ አይደለም ብለው ጥለውት ይሆን እንዴ?! እንጃ! ከኢሕአዴግ ጽ/ቤት ካድሬዎች አንዱ የሆኑት አቶ ፍቃዱ ተሰማ እንኳን እኮ፣‹‹ኢሕአዴግ መርሁ መደመር ነው›› ብለው በአዲስ ዘመን ጋዜጣ የነገሩን ባሳለፍነው ሳምንት ነበር፡፡

በተቀረ ያ ‹‹ምንም ነገር አልደብቃችሁም›› ብሎ በአደባባይ የማለልን ኢሕአዴግ አሁንም ምስጢረኛ፣ ደባቂና ጓዳ ጓዳውን የሚያደርገውን የማይነግረን ሆኖ ቀጥሏል፡፡
እንዲህ ይላል፤

‹‹ምክር ቤቱ በእህት ድርጅቶችና በአመራሩ መካከል የሚታየውን መጠራጠር በመፍታት የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት ማምጣት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክሯል። ከዚህ አኳያ መታረምና መስተካከል ያለባቸው ነጥቦች ላይ መግባባት ተፈጥሯል›› የሚል አንቀጽ ታነባለህ፡፡

መጠራጠር ታይቶባቸዋል የሚባሉት የትኞቹ ድርጅቶች ናቸው ? ግለሰቦቹስ እነማን ናቸው? የመጠራጠራቸው ምክንያት ምን ነበር? በቀጣይ እንዴት ሊፈታ ተስማማችሁ? ወዘተ የሚለውን ጉዳይ ግን ድብቁ ኢሕአዴግ አያብራራልህም፡፡ ወዳጄ ከዚህ በላይ አብዮታዊ ዴሞክራትነት አለ እንዴ?!

ስለ መዋኸድ ምንም አለማለቱም አስገራሚ ነው፡፡ ኢሕአዴግ እዋኸዳለሁ ብሎ ማስወራት ከጀመረ እንደቆየ ታውቃለህ መቼም፡፡ሰሞኑን ደግሞ የባሰ ገፍቶ አምጥቶት ይህ ዓመት ሳይጠናቀቅ ለመዋኸድ መዘጋጀቱን ገልፆ እንደነበር አትዘነጋም፡፡ ግን በዚህ ጉባኤ ላይ ይህ አጀንዳ ስለመነሳቱ መግለጫው አልጠቀሰም፡፡ ምናልባት ይህንንም ደብቆህ ይሆን?!
በነገርህ ላይ የኢሕአዴግህ መግለጫ እርስበርሱ የሚናከስ ነገርም አለው፡፡

‹‹ሀገራዊ የውጪ ምንዛሬ ክምችቱን በማሳደግ በኩል ትርጉም ያለው ስራ እንደተሰራ ገምግሟል›› ይልህና እዚያው ደግሞ ‹‹ከፍተኛ የስራ አጥነት፣ የውጪ ምንዛሬ እጥረት፣ …በአግባቡ ያልተቀረፉ በመሆናቸው መዋቅራዊ መፍትሄ ለመስጠት መረባረብ እንደሚገባ ምክር ቤቱ አስምሮበታል›› ብሎ ሌላ ተቃራኒ ነገር ያወራብሃል፡፡

ቀድሞ ነገር ‹‹የውጪ ምንዛሬ ክምችቱን በማሳደግ በኩል ትርጉም ያለው ስራ ከተሰራ›› እንደገና የውጭ ምንዛሬ እጥረት በመዋቅራዊ መንገድ የሚፈታና በአግባቡ ያልተቀረፈ እንዴት ይሆናል? ተቃርኖ አንድ!

ይህ መግለጫ ‹‹የፖለቲካ ምህዳሩን ከማስፋት አኳያ የተሰሩ ዘርፈ ብዙ ስራዎች መኖራቸውን››ጉባኤው እንደተስማማበት ይገልጽልህና ‹‹በተጨማሪም ወጣቶቹ ያሏቸውን የፖለቲካ ተሳትፎ ጥያቄዎች ገና በተሟላ ሁኔታ አለመመለሳቸውን አይቷል›› ብሎ ከራሱ ጋር ይቃረንብሃል። የፖለቲካ ምህዳሩ ከሰፋ እንዴት ወጣቶች አልተሳተፉበትም የሚል ጥያቄ ብታነሳ ግን መልስ የሚሰጥህ የለም፡፡ ተቃርኖ 2

ኢሕአዴግ ባለፈው አንድ ዓመት ገበሬ ቤተሰቦቻችንን ረስቷቸው እንደከረመ መቼም ታውቃለህ፡፡ ወሬው ሁሉ ከተሜ ከተሜ የሚሸትና ለቴሌቭዥን ተመልካት የሚቀርብ እንጂ በኩራዝና በማገዶ እንጨት ኑሯቸውን የሚገፉ ገበሬዎቻችንን ረስቶ ከርሞ ነበር፡፡

እኔ በኃይሉ ሚዴቅሳም ባሳለፍነው ዓመት ‹‹የኢሕአዴግ ላባደር ማነው›› ብዬ በመፃፍ በድሬቱዩብ ያስነበብኩህ ከዚሁ ተቆርቋርነቴ አንፃር ነው፡፡ አሁን ግን ኢሕአዴግ ወደ ገበሬዎቿ ተመልሳ እንዳተኮረች በዚህ መግለጫ ተነግሮሃል፡፡ ‹‹በቀጣይ ጊዜ በተለይም ለመስኖ ልማት የሚሰጠውን ትኩረት እንደተጠበቀ ሆኖ በቀሪ ወራት በመኸር ስራ ላይ መረባረብ እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጧል›› ስትልም ኮራ ብላ መግለጫ አውጥታ ታገኛታለህ፡፡

ሌላው ደግሞ ኢሕአዴግ ወደ ቀደመው ማንነቷ ከአራት ዓመት በፊት ወደነበረው ሰብዕናዋ ተመልሳለች እንድትል የሚያስገድድህ ሚዲያ ላይ በተለይም ማኅበራዊ ድረገፆች ላይ የወሰነችውን ውሳኔ ስታነብ ነው፡፡

‹‹ ማህበራዊ ሚዲያው እየተጫወተ ያለው አዎንታዊ ሚና እንደተጠበቀ ሆኖ ዴሞክራሲውን የማቀጨጭ ሚናው እየጎላ መምጣቱን ገምግሞ ከለውጡ ጋር በተዛመደ መልኩ የሚታረምበትን አካሄድ መከተል እንደሚገባ አመላክቷል›› ይልሃል ኢሕአዴግ ነፍሴ። ፌስቡክ ሆይ እዚህ ጋር ያለውን ገደምዳሜ በደንብ ተመልከት፡፡ የኢሕአዴግን ለውጥ የማትደግፍ እና ከእርሱ ጋር ተዛምደህ የማትሔድ ከሆነ እኩይ ነገር ተደግሶልሃል፡፡

‹‹የጥላቻ ንግግሮችን በህግ አግባብ መከላከል አስፈላጊ እንደሆነም ምክር ቤቱ አምኖበታል›› የሚለው ዓረፍተነገር ደግሞ ከፈረሱ ጋሪውን አስቀድሞ ታገኘዋለህ። ቀድሞ ነገር ረቂቅ ሕግ ተዘጋጅቶ ውይይት እየተደረገበት ነው፡፡ የእስርና የገንዘብ ቅጣት የሚያስጥሉ አንቀፆችን የያዘ ባለ 10 አንቀጽ አምስት ገጽ ‹‹የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል›› በሚል አዋጅ ተረቅቆ እያለ፣ ትናንት ኢሕአዴግ መጥታ ‹‹የጥላቻ ንግግሮችን በህግ አግባብ መከላከል አስፈላጊ እንደሆነም ምክር ቤቱ አምኖበታል›› ብላ ታፌዝብሃለች፡፡ የትከርማ ነው ባክህ?!

የዚህኛው ጉባኤ ልዩ ነገር ደግሞ በድምጽ ብልጫ የውይይት ሰነዱ መጽደቁ ነው፡፡ ይህ በስምምነት ውሳኔዎችን ያሳልፍ ለነበረው ጉባኤ እንግዳ ነገር ነው፡፡ ውሳኔዎችን በአብላጫ ድምጽ መወሠን በኢሕአዴግ ቤት አዲስ ነው፡፡

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close