Connect with us

Entertainment

ኦነግ እና አብን ፓርላማ ከመግባታቸው በፊት፣ በወለጋ እና በባህር-ዳር ስቴዲየሞች ላይ የወዳጅነት ቢጫወቱ…

Published

on

ኦነግ እና አብን ፓርላማ ከመግባታቸው በፊት፣ በወለጋ እና በባህር-ዳር ስቴዲየሞች ላይ የወዳጅነት ቢጫወቱ..

ኦነግ እና አብን ፓርላማ ከመግባታቸው በፊት፣ በወለጋ እና በባህር-ዳር ስቴዲየሞች ላይ የወዳጅነት ቢጫወቱ.. | ከአሳዬ ደርቤ

ዝናቡ ማካፋት ሲጀምር መብራት እንደሚጠፋ እርግጠኛ ሆኜ ሻማ ለኮስኩ፡፡

እንዳልኩትም ከአፍታ ቆይታ በኋላ አምፖሉ ጠፋ፡፡ እዚህ ሀገር የሆነ ነገር ሲመጣ ያለውን ነገር አጉድሎ ነው፡፡

ዝናቡ ሲመጣ መብራታችን፣ ጸሐይ ስትወጣ ደግሞ ውሃችን ይሄዳል፡፡ በረከት አልባው ደሞዛችን ሲወጣ ደስታችን ይነጥፋል፡፡

ይሄንንም ሁኔታ እኔ ከInflation ጋር ሳገናኘው፣ አንዲት የሥራ ባልደረባዬ ደግሞ ‹‹ብሩ መቅኖ ያጣው ይሄ ATM የሚባል ሰላቢ ማሽን ከመጣ ጊዜ አንስቶ ነው›› የሚል አቋም አላት፡፡

የለኮስኩት ሻማ ፎርጅድ ነው መሰል ብርሐን በመፈንጠቅ ፈንታ የለውጡን ያህል እንኳን ጭላንጭል መፍጠር አቅቶት ይቅለጠለጥ ይዟል፡፡ ቴሌቪዥን ላይ አይኑን ተክሎ ‹‹ኢትዮጲስን›› ሲመለከት የነበረው ብላቴና ትዕይንቱ ሲቋረጥበት ሱሪዬን እየገተተ ማልቀስ ጀመረ፡፡ በጨዋ ቋንቋ ‹‹እይውልህ ባባዬ ቴሌቪዥኑ የጠፋው መብራት ስለሄደ እንጂ እኔ ስላጠፋሁት አይደለም›› በማለት ላስረዳው ብሞክርም… በለቅሶው ውስጥ ‹‹ምንም አይነት ማስተባበያ አልፈልግም›› የሚል መልዕክት ማስተላለፉን ቀጥሎበታል፡፡

በእኔ በኩል ግን የዝናቡ መጣል ካጠፋው መብራት ይልቅ፣ የሚያመጣው በረከት እልፍ አዕላፍ መሆኑን ስለምረዳ ሰማዩን አልረገምኩትም፡፡ ይልቅስ ለገበሬው ብላጊውን፣ ለከብቶቹ ጨሌውን፣ ለሸማቹ መረጋጋትን የሚለግስ በመሆኑ ሊበረታታ ይገባዋል፡፡

ባይሆን ‹‹እብድና ዝናብ ከተማ ይወዳል›› እንደሚባለው አዲስ አበባ አስፓልቶች ላይ በከንቱ የሚያለቅሰው ሰማይ ቦታውን ቀይሮ ሰሜን ተራሮች ላይ ቢያንዠቀዥቀው መልካም ነበረ፡፡

የሚያላዝነውን ልጄን ትቼ ወደ መኝታ-ቤቴ በመግባት ፌስቡኬን ስከፍተው የእለቱ ዜናዎች ሶስት ሆነው አገኘኋቸው፡፡

የመጀመሪያው ዜና ፓርኩ ላይ የተያያዘው እሳት ከእጽዋቶቹ አልፎ ብርቅዬ አራዊነቶቹን እያቃጠለ መሆኑን የሚገልጽ ሲሆን… በሄሊኮፕተርም ሆነ በሆነ ተዓምር እሳቱን መቆጣጠር ካልተቻለ… ዋሊያወቹን መመልከት የምንችለው እንደ ዶክተር አቢይ ስቴዲየም ውስጥ ብቻ ስንገባ ብቻ መሆኑ አይቀርም፡፡

ይሄን ብዬ ወደ ሁለተኛው ዜና ስሸጋገር ጠቅላያችን ከአቶ ለማ ጋር ኳስ ሲጫወቱ የሚያሳይ ምስል ሶሻል ሚዲያውን አጥለቅልቆታል፡፡ ከምስሉ ተነስተን የተሰማንን ስንገልጽ ከዶከተር አቢይ ይልቅ አቶ ለማ ኳስ አያያዝ የሚያውቁ ይመስላሉ፡፡ (ሥልጣን አያያዙን በተመለከተ ሌላ ጊዜ እመጣበታለሁ!)

ሆኖም ግን ኦዴፓዎች ወለጋ ድረስ ከሄዱ አይቀር ኦነጎችን ቢገጥሟቸው ጥሩ ነበር፡፡ መቼም እንደኔ ግምት ኦነግ በራሱ ሜዳና በደጋፊው ፊት ነጥብ የሚጥል አይመስለኝም፡፡ ይህ ቢሆን እንኳን ኦቦ ዳውድ ኢብሳ ‹‹ባንድ አገር ላይ እየኖርን ‹እከሌ አሸናፊ፣ እከሌ ተሸናፊ› የሚለው ነገር Sensetive issue ስለሆነ አልቀበለውም›› ብሎ ክላሹን ያነሳል እንጂ ውጤቱን የሚስማማበት አይመስለኝም፡፡

ግን ግን ጓዶች… ገዥውን ፓርቲ እንተወውና አብን እና ኦነግ ፓርላማ ውስጥ ከመገናኘታቸው በፊት በባህር-ዳር እና በወለጋ ስቴዲየሞች የወዳጅነት ጨዋታ ማድረግ የለባቸው ትላላችሁ? ባይሆን አዴፓና ኦዴፓ ጨዋታው በዝግ ስቴዲየም እንዲሆንና የወያኔ አመራሮችም በዳኝነቱ/በአራጋቢነቱ ላይ እንዲሳተፉ ቢያደርጉ›› የሚል አስተያየት አለኝ፡፡ እናም ዳኞቹም ሆኑ ተጨዋቾቹ ተስማምተው ጨዋታውን በሰላም መጨረስ ከቻሉ እሰየው! ይህ ካልሆነ ደግሞ ህዝብና ህዝብ ከሚያጫርሱ እዚያው እርስ በእርሳቸው ቢጫረሱ የተሻለ ስለሚሆን መንግስት ይህችን ምክሬን ተቀብሎ ተግባራዊ ቢያደርጋት ጥሩ ነው እላለሁ፡፡

ሌላውና ሶስተኛው የሶሻል ሚዲያው አጀንዳ ‹‹ሰላሳ ዓመት ሥልጣን ላይ ተወዝፎ የኖረው የአልበሽር መንግስት ልክ እንደ ወንድሞቹ ሁሉ በወታደሩ መገልበጡን›› የሚያበስር ነው፡፡ መቼም ይሄንን ዜና ኢሳያስ አፈ-ወርቂ ሲሰማ ወታደሮቹን ትጥቅ ያስፈታል እንጂ ሥልጣኑን በሰላማዊ መንገድ ለመልቀቅ ያስባል ተብሎ አይገመትም፡፡

አንዳንድ ጊዜ እኒህ የአፍሪካ መሪዎችን ከወንበር ላይ እንዲያረጁ የሚያደርጋቸው ምክንያት ከሥልጣን ጥማት በተጨማሪ በንግስና ዘመናቸው የሚፈጽሙት ጥፋት ‹‹ከወረድን በኋላ መኖር አንችልም›› ብለው እንዲያስቡ ስለሚያደርጋቸው ይመስለኛል፡፡

ማለትም በመሪነት ቦታ ላይ ሲቀመጡ ከታሪካቸው ይልቅ ለሥልጣናቸው ሲሉ ብዙ እኩይ ተግባራትን ይፈጽማሉ፡፡ በመጨረሻም ከዙፋናቸው በተፈነገሉ ማግስት እድለኛ ከሆኑ ወደ እስር-ቤት ወይም ደግሞ ወደ መቃብር-ቤት ይወረወሩና የህይወት ታሪካቸው ይደመደማል፡፡

የእኛውንም ኢህአዴግ እንደ ስርዓት ስናስበው አንድ ጊዜ እየበሰበሰ፣ ሌላ ጊዜ እየታደሰ ከአልበሽር እድሜ ባልተናነሰ መልኩ ለሶስት አስርት ዓመታት ወንበሩን ተቆጣጥሮ ኑሯል፡፡ በእነዚህ ዓመታትም ሶስት መሪዎች አስተናግደን… አንዱ በሞት፣ ሌለኛው በህይወት ከወንበሩ ላይ የተነሱ ሲሆኑ.. ያረፈውን እንተወውና በህይወት ሳሉ ያለምንም ማመንታት ሥልጣናቸውን በመልቀቅ አጨራረሳቸውን ያሳመሩትን ጠቅላይ-ሚኒስቴር አለማመስገን አይቻልም፡፡ ያለፍላጎታቸው የተጫነባቸውን ሥልጣን በፍላጎታቸው በመልቀቃቸው በግሌ አመሰግናቸዋለሁ፡፡

በሁለቱ መሪዎች ተንደርድሬ ወደ ሶስተኛው ጠቅላይ ሚኒስቴር ስመጣ… ኢትዮጵያ ከእሳቸው መዳፍ ሰላማዊ የሆነ የስርዓት ለውጥ ትፈልጋለች፡፡ ይሄንንም አገራዊ ፍላጎት እሳቸው የሚጋሩት ከሆነ…. አጨራረሳቸው ያምር ዘንዳ በመሪነት ዘመናቸው ‹‹ከሹመት ብቻ ሳይሆን ከህይወትም እንደሚወገዱ›› እያሰቡ መኖር ያስፈልጋል፡፡ በእያንዳንዷ ቀን እንደ ሙርሲ-በእስራት፣ እንደ መንጌ-በስደት፣ እንደ ጋዳፊ-በሞት የተሰናበቱ የሃገር መሪዎችን እያስታወሱ ‹‹አንዲህ አይነት ፍጻሜ እንዲኖረኝ አልፈልግም›› እያሉ መወሰንን ይጠይቃል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ይህችን ግጥም ቢሸመድዷት ጥሩ ነው፡፡

ከእለታት ባንድ እለት-በቀደመው ዘመን
‹‹ዱላ ቅብብል ነው የጨበጥነው ስልጣን››
ብለው ባሉን ማግስት- ከትራክ ውስጥ ገብተን፣
ዱላ ለመቀበል- መዳፍ ስናፍታታ
ገምሰውን ሄደዋል- በማቀበል ፈንታ፡፡
እናም ይሄን በትር…
እናም ይሄን ዱላ…
‹ንጠቁኝ› ሳይሉ- ከሰጡት ለሌላ
ካንቱ ‘ምንጠብቀው ይሄው በመሆኑ
እድሜና ቃልዎን ቆመው ይመጥኑ፡፡

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close