Connect with us

Ethiopia

ኢህአዴግ ሊሰበሰብ ነው አሉኝ!

Published

on

ኢህአዴግ ሊሰበሰብ ነው አሉኝ! | በጫሊ በላይነህ

ኢህአዴግ ሊሰበሰብ ነው አሉኝ! | በጫሊ በላይነህ

አዎ!.. ኢህአዴግ ከመጪው ሰኞ ዕለት ጀምሮ ይሰበሰባል ቢሉኝ ገረመኝ። በህይወት መኖሩ አስደመመኝ።

እንዲህ የሆንኩት ወድጄ አይምሰልህ። የምሰማውና የማየው ነገር እየተጋጨ “እውን ኢህአዴግ በህይወት አለ” ብዬ የጠየኩባቸው ጊዜያቶች በዝተውብኝ ስለነበረ ነው። በቅርቡ ጠቅላዬ “ኢህአዴጎች አብረን ነን፣ አሁንም ከአንድ መፅሀፍ እያነበብን ነው…”አለን። ይህን ያለበት ምራቅ ሳይደርቅ ከወደመቀለ ደብረፂ በተቃራኒው”ችግር አለብን” ብሎ አረዳን።

እውነት ነው፤ ጎምቱው ህወሓት “ለውጡ አልተመቸኝም” ብሎ የነገር ማዘዣ ጣብያውን ከአዲስ አበባ ወደ መቀለ ካዞረ ሁለት መንፈቅ ሊደፍን ነው።

በኦሮ- ማራ ፍቅር መቀመጫውን ገልቦ፤ ውሀ በወንፊት እንቅዳ ሲል የነበረው ብአዴን/አዴፓ ደግሞ የኦህዴድ/ኦዴፓ አካሄድ ሆድ አስብሶት “ብልጥብልጥ አካሄድ ይቁም!” እያለ ቁዘማ ውስጥ ከወደቀ ሰነበተ።

ደኢህዴን በለውጥ ሀይሉ ተማርኮ፤ ነባር አመራሩን አራግፎ ጥሎ፤ ሊቀመንበሩን በሠላም ሚኒስትርነት ባስመረጠ ማግስት ሠላም ማጣቱ የአደባባይ ሚስጢር ነው።

ኦህዴድ/ኦዴፓ በኢትዮጽያዊነት እና በኦሮሞ አክራሪ ብሄርተኝነት አጀንዳ መሀል ተቀርቅሮ እንደአሮጌ መኪና በየአውራ መንገዱ እየተበላሸ መቆም ሥራው ሆኗል። የለውጡ መሐንዲሶች ተብለው በሕዝብ የተሞካሹት ዐብይ እና ለማ የሚናገሩትና የሚተገብሩት አልተጣጣመልኝም ያለው ያው ትላንት ያጨበጨበላቸው ሕዝብ ነው።

ይሄ ምስኪን ሕዝብ ግን ምን ያድርግ?!…

ትላንት በፍፁም የዘረኝነት መንፈስ የታወሩ ጎረምሶች በቡራዩ በጠራራ ፀሐይ ሕዝብን ሲጨፈጭፉ መንግሥት ዝምታን መርጦ፤ ጭፍጨፋውን የተቃወሙ የአዲስአበባ ሠላማዊ ወጣቶች ላይ ቃታ መሳቡን፣ ለእስር ማጋዙን አይቶ፣ ሰምቶ ታዝቧል።

ዶክተር ዐብይ የሚመራው ኦዴፓ ሕገመንግሥቱን ገንድሶ በመጣል የአዲስአበባ ባለቤት የኦሮሞ ሕዝብ ነው የሚል ይፋዊ መግለጫ ባወጣ ሰሞን ዐብይ ደግሞ በተቃራኒው ከተማው የሁሉም ነው የሚል መግለጫ በመስጠት ተቃርኖውን አስመዝግቦ ሊያስጨበጭብ ሲተጋ እያየ ታዝቧል።

ይሄ ሕዝብ፤ በሕግ ማስከበር ስም የሌላ ብሄር ተወላጆች አውላላ ሜዳ ላይ ሲጣሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አፉን ሞልቶ “አላየሁም፣ አልሰማሁም” ማለቱን ታዝቧል።

ይሄ ምስኪን ሕዝብ፤ በአንድ በኩል ትላንት የህወሓት የበላይነት ነበረ በሚል እያለቃቀሰ፣ በምግባሩ ግን ጊዜው የእኛ ነውን የሚያቀነቅኑትን ደጋግሞ አይቷል፣ ታዝቧል። ይሄ ሕዝብ፤ “ኮንደሚኒየም ወይም ሞት” የሚሉ ግለሰቦች የሰፈር ጎረምሶችን ዱላ አስይዘው መንግሥትና ሕዝብን አደባባይ ወጥተው ሲያስፈራሩ፣ ሲዝቱ፤ ይህም እንደትልቅ ጀብዱ ተወስዶ በኦዴፓ የድጋፍ መግለጫ ሲሰጥ አይቷል፣ ሰምቷል፣ ታዝቧል።

ይሄ ሕዝብ በአዲስአበባ ጉዳይ ገዥው ፓርቲ የያዘውን አቋም በሠላማዊ መንገድ የተቃወሙ ግለሰቦች “ጦርነት ውስጥ እንገባለን” ተብሎ ሲዛትባቸው፣ ተራ የጋዜጣዊ መግለጫ መድረካቸው በፖሊስ ሲጨናገፍ አይቷል፣ ታዝቧል።

እናም ወገኔ፤ ደብረፂ ትክክል ብሏል። በአሁን ሰአት ኢህአዴግ አንድ አይደለም። ምናልባት ምክርቤቱ በሰኞ ስብሰባው ለምን አንድ መሆን አቃተን? የሚል አጀንዳ ቀርፃ ቢወያይ ለራሱም ቢሆን ይበጀዋል።

በእርግጥም የሚበጀው፤ ነገሮችን ፍርጥ አድርጎ መወያየት ነው። መዳኛውም እሱ ነው።…ለምንድነው ሠላም የጠፋው?

ለምንድነው ንፁሀን “ባልታወቁ ሀይሎች” የሚገደሉት፣ የሚፈናቀሉት? እነዚህ ያልታወቁ ሀይሎች እነማን ናቸው? መንግሥት ህግና ሥርዓትን ማስከበር የተሳነው ለምንድነው? ሁሉም ነገር የእኛ ነው የሚል አስተሳሰብ የተንሰራፋውና ወደከፋ ብጥብጥ እያንደረደረን ያለው ለምንድነው? ግጭትን በማባባስ፣ በማቀጣጠል ትልቅ ሚና ያላቸው ግለሰቦችና ቡድኖችን መንግስት በአንቀልባ አዝሎ እሽሩሩ የሚልበት ትክክለኛ ምክንያቱ ምንድነው? ብሎ ይጠያየቅ፣ ይገማገም፣ ይወያይ።

በተጨማሪም የሰኔ 16/2010 የመስቀል አደባባይ የፈንጅ አደጋ፣ የኢንጅነር ስመኘው ግድያ፣ የቡራዩ ግጭት፣ የባንኮች ዘረፋ፣ የማእድን ባለሀብቶች ግድያ፣ የሰሜን ጎንደር ግጭትና መፈናቀል….ወንጀል አቀነባባሪዎችና ፈፃሚዎች ጉዳይ ተድበስብሶ የቀረው ለምንድነው ብሎ ፍርጥ አድርጎ ይነጋገር። እውነቱን ያውጣ፣ ይወስን?!

አዎ!.. ኢህአዴግ በህይወት ካለ ለችግሮች ብቸኛ መፍትሄ የሚሆነው ብልጣብልጥነትን መሳቢያ ውስጥ ቆልፎ ፣ በሀቅ ተነጋግሮ በመተማመን ለመፍትሄው በጋራ አብሮ መቆም ብቻ ነው። በአሁን ሰዓት በአባል ድርጅቶችና በከፍተኛ አመራሩ መካከል በጉልህ በሚታየው የሻከረ፣ መከባበር የራቀው ግንኙነት ብዙ ርቀት እንደማያስኬድ በግልፅ ሊመክርበት ይገባል።

ከዚህ በተቃራኒው ግን ኢህአዴግ ያው እንደለመደው “ሥራዬ የተሳካ ነበር..አመርቂ ነው…አበረታች ውጤት ታይቶበታል፣ ሕዝቡ በእኔ ፍቅር ወድቋል…” ዓይነት ያረጀ ዲስኩር ላሰማ ቢል የሚስቅበት እንጂ የሚሰማው አያገኝም።

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close