Connect with us

Ethiopia

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የደቡቡን ድል በሰሜን ለመድገም ለምን ተሳናቸው?

Published

on

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የደቡቡን ድል በሰሜን ለመድገም ለምን ተሳናቸው? | በሬሞንድ ኃይሉ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የደቡቡን ድል በሰሜን ለመድገም ለምን ተሳናቸው? በሬሞንድ ኃይሉ

ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመሩት ኢህአዴግ ለውጥ ውስጥ መሆኑ ተደጋግሞ ተነግሯል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ ወቅቶች እንዳረጋገጡትም በታሪኩ ታይቶ የማይታወቅ የአንድነት መንፈስ ውስጥ ይገኛል፡፡ የገዥው ፓርቲ አንድ ሁኗል ትርክት ግማሽ እውነት ግማሽ ውሸት የሚባል ዓይነት ነው፡፡ በርግጥ የድርጅቱ እህትና አጋር ፓርቲዎች ለውጡን ተከትሎ የአመራር ለውጥ አድርገዋል፡፡ በግንባሩ ውስጥ ከፍተኛ ህዝብ የሚወክሉት ኦህዴድና ብአዴንም ስማቸውን ለውጠዋል፡፡ ኢሶዴፓም ከዚህ በኋላ ሶዴፓ እባላለሁ ብሎ እንደ አዲስ ተዋውቆናል፡፡ የኢህአዴግ ጠቅላላ ጉባኤ በሚካሄድበት ወቅት ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ፓርቲውን እንዲመሩ የተሰጣቸው ድምፅም በድርጅቱ ውስጥ ከሞላ ጎደል የሁሉም ስምምነት መኖሩን ይጠቁማል፡፡ ታዲያ እንዲህ ከሆነ በታሪክ “እንዳሁኑ ተዋህደን አናውቅም ”የሚለው አስተያየት ስህተቱ ምን ላይ ነው?

የኢህአዴግ ወቅታዊ ሁኔታ ተቃርኗዊ ነው፡፡ ዛሬ ወዳጅነታቸውን ያየነው እህት ድርጅቶች በነጋታው ልዩነት ውስጥ ይገባሉ፡፡ ተራራቁ ያልናቸው ፓርቲዎች ዳግም ፍቅራቸውን ያድሳሉ፡፡ በዚህ ሁሉ ሂደት ግን የህወሓትን አቋም ለመገመት አዳጋች አልነበረም፡፡

የገዥው ፓርቲ አስኳል ሆኖ ከሁለት አስርታት በላይ የዘለቀው ይህ ድርጅት ከግንባሩ ሊቀመንበር ጋር በተለያዩ ወቅቶች የቃላት ጦርነት ውስጥ ሲገባ ታይቷል፡፡ የኢህአዴጉ ሊቀመንበር የለውጥ መገለጫ አድርገው የሚያነሷቸው ሀሳቦች ላይ ተቃውሞዎችን አሰምቷል፡፡

የህወሓት ሰዎች በተደጋጋሚ የእህት ድርጅቶቹ የስም ለውጥ እርባና ቢስ መሆኑን አሳይተዋል፡፡ ደብረፂዎን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ከወራት በፊት አቶ ጌታቸው ረዳ በዋልታ ቴሌቨዠን በቅርብ የአባል ድርጅቶች ስም ለውጥ ጉንጭ አልፋ መሆኑን በአደባባይ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ከፍ ሲልም የተጀመረው ለውጥ አቅጣጫውን መሳቱን አብራርተዋል፡፡ የሀገሪቱም ህልውና አደጋ ላይ ነው ማለትንም ተክነዋል፡፡

በኢህአዴግ ውስጥ የተካሄደውን የለውጥ እንቅስቃሴ ተከትሎ ህወሓት ባለፉት 12 ወራት በርከት ያሉ የተቃውሞ ሃሳቦችን አንስቷል፡፡ እነዚህ ሃሳቦች መጀመሪያ ለውጥ አደናቃፊ ተብለው ሲፈረጁ በኋላ ላይ በኢህአዴግ ውስጥ ያለው ውስጠ ዴሞክራሲ ማሳያ ናቸው ተብሎ በገዥው ፓርቲ ሊቀመንበር ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ በሁለቱም አገላለፆች ውስጥ ግን አንድ ጥያቄ ይነሳል፡፡ የዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ለውጥ ለምን ህወሓት ወደ ራሱ መሳብ አቃተው?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በባዕለ ሲመታቸው ማግስት ጉብኝት ካደረጉባቸው አከባቢዎች መካከል መቐሌ ተጠቃሽ ናት፡፡ በጊዜው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡ እሳቸውም የትግራይ ህዝብ የኢትዮጵያ ሞተር ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ በዕለቱ ከምሳ በኋላ በነበራቸው ቆይታም የትግራይ የጦር አካል ጉዳተኞችን ሰብስበው የልፋታችሁን ያህል ሀገር ያልካሳችሁ ጀግኖች ናቸው ብለዋቸዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲህ ያለ ንግግር በአንድ በኩል አዕላፍት ልጆቹን በትግል ወቅት ለገበረው የትግራይ ህዝብ ደስታን የፈጠረ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ስልጣን የያዙት የህወሓት ሰዎች አልሰሩላችሁም የሚል መልዕክት ነበረው፡፡

ይህ መልዕክት ደግሞ ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ህወሓትን ለመቀየር የሞከሩበትን የመጀመሪያ ሙከራ የተሸከመ ነው፡፡ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ከምንም በላይ ሊከስም አልያም ሊታደስ የሚችለው የትግራይ ህዝብ በሚያደርገው ግፊት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የትግራይን ህዝብ በፍቅር ለመያዝ ሲሞክሩ ልጆቻችሁ የተሰውለት ትግል እናንተን አልጠቀመም ሲሉ ከህወሓት ጎራ ለመኮብለል የማይነሳሳ ትግራወይ የሚኖር አይመስሉም ፡፡ በዛው ሰሞን ወደ መቐሌ ለስራ ስሄድ የተመለከትኩት ሀቅም ይህንኑ ያረጋግጣል፡፡

የከተማዋ ወጣቶች እንዳጫወቱኝ ህወሓት አይደለም ለእኛ ለታገለላት አካል ጉዳተኛም ያደረገችው ነገር የለም ይሉ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ቃላቸውን ከጠበቁ ህወሓት ያላት ድጋፍ መክሰሙ የሚቀር እንዳልነበር ያመላክታል፡፡

ይሁን እንጅ ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ይህን የመሰለውን ትልቅ ተስፋ የሰጡበትን ዕድል ሊጠቀሙበት አልቻሉም፡፡ ለዚህ ደግሞ በርካታ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው ጠቅላዩ በአሜሪካ በነበራቸው ቆይታ ከትግራይ ተወላጆች የሚነሳላቸውን ጥያቄ በቅንነት አልተመለከቱም ከሚለው ይቀዳል፡፡ ሌላው ከኤርትራ ጋር ያለው የሰላም ስምምነት ፖለቲካ ትግራይን ከማግለሉ ይመነጫል፡፡ የፕሬዘዳንት ኢሳይያስ ጉብኝት ከመቐሌ ይልቅ ባህርዳርና ሀዋሳ ማስበለጡም ለዚህ ዋቢ የሚሆን ነው፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩና የትግራ ህዝብ የነበራቸው ወዳጅነት እንዲሻክር በማድረጉ በኩል የፈደራል መንግሰቱ የሚያስተዳድራቸው መንገዶች ተዘግተው ወደ ትግራይ ዕህል እንዳይገባ መደረጉም የማይናቅ አስተዋጽኦ ነበረ ፡፡ ባለፈው አመራር የተከሰቱ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን የሚያሳይ ዘጋቢ ፊልም ለዕይታ ሲበቃም ትግራይን በተለየ ሁኔታ መጠቀሱም በብሄር ተኮር ግጭት ልጆቿን እያጣች ለነበረችው ትግራይ የሚዋጥ አልሆነም፡፡ ከዚሁ ሁሉ በላይ ደግሞ ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) ህገ-መንግሰቱ ላይ ያላቸው አቋም ለዘብተኛ መሆን መቐሌን ደስታ ነስቷታል፡፡

እናም ለህወሓት ጀርባውን ይሠጣል የተባለው የትግራይ ህዝብ መስጠቱን አንገራገረ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በህዝባዊ ጫና ህወሓትን የሚቀይሩበትን ዕድል አበላሹ፡፡ በደቡብ ያገኙትን የፓርቲያቸውን ድልም በሰሜን መድገም ተሳናቸው፡፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ

** ኢትዮ ጵያን የተመለከቱ የተለያዩ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዘኛ ለማንበብ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close