Connect with us

Ethiopia

የተፈናቃይ ወገኖቻችን ድርብ ድርብርብ ስቃይ

Published

on

የተፈናቃይ ወገኖቻችን ድርብ ድርብርብ ስቃይ | በጫሊ በላይነህ

የተፈናቃይ ወገኖቻችን ድርብ ድርብርብ ስቃይ | በጫሊ በላይነህ

የጠ/ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ የአንድ ዓመት የመደመር ጉዞ አልጋ በአልጋ አልነበረም፡፡ በአመዛኙ በኢህአዴግ ውስጥ በተፈጠረ ሽኩቻና የአክራሪ ብሔርተኝነት አጀንዳ ጣራ ነክቶ ወደማያባራ ግጭት ውስጥ ደፍቆናል፡፡ በዚህም ንጹሃን ወገኖች በማያውቁት ዕዳ የሞት ገፈት ቀማሽ ሆነዋል፡፡

አንዳንዶችም ለዓመታት ተከብረው ከኖሩበት ቀዬ በጉልበተኞች ተፈናቅለዋል፡፡ ኢትዮጵያችን በአሁን ሰዓት ከሶስት ሚሊየን በላይ ሰዎች የተፈናቀሉባት አሳዛኝ አገር ወደመሆን ተሸጋግራለች፡፡ ይህም ሆኖ መንግሥታችን እነዚህን የጥፋት ኃይሎች በስም ጠርቶ ለማውገዝ እንኳን ወኔ አላገኘም፡፡ አጥፊዎቹም አሁንም በጠራራ ጸሐይ ንጹሃን ሰዎችን ከመግደልና ከማፈናቀል አልታቀቡም፡፡ ሰሞኑን በአጣዬና አካባቢዋ ብቻ ከ58 በላይ ሰዎች መግደልና ማቁሰላቸው የቅርብ ማሳያ ነው፡፡

መረጃዎች እንደሚያሳዩት የተፈናቀሉ ዜጎችን ደህንነታቸውን አስጠብቆ ወደ ቀያቸው መልሶ በዘላቂነት ለማቋቋም ከ650 እስከ 700 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ያስፈልጋል፡፡ እስካሁን መንግሥት በራሱ አቅም መመደብ የቻለው 800 ሚሊየን ብር ብቻ መሆኑ ያስደነግጣል፡፡ እነሆ መንግሥታችንም ሊቆጣጠረው ባልቻለው ቀውስ ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመርዳት የለጋሾችን ደጅ ጥናቱን አጣጡፏል፡፡

ምናልባት የፈረንጆችን ልብ ካራራልን የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም በሶስት ምዕራፍ ተከፋፍሎ የሚካሄደው ፕሮግራም ሊሳካ ይችል ይሆናል፡፡ ካልተገኘ ምን ሊሆን እንደሚችል ራሱ መንግሥታችንም የሚያውቀው ጉዳይ አይደለም፡፡ ዜጎችን መልሶ የማቋቋሙ ሥራ በመጀመሪያ ምዕራፍ በአጠቃላይ ወደ 800 ሺህ ዜጎች ወደቀያቸው ለመመለስ ታቅዷል ፡፡ በሁለተኛው ዙር ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም እስከ ስድስት ወር የሚወስድ ሲሆን ሶስተኛው ዙር ደግሞ እስከ አንድ ዓመት ይወስዳል ተብሏል፡፡

የተፈናቃዮቻችን ሌላው መከራ ለወረሽኝና ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ተጋላጭ የመሆናቸው ጉዳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ መፈናቀሉን ተከትሎ በሀገሪቱ በርካታ በሽታዎች መጋረጣቸውን ይፋ አድርጓል፡፡ በአሁን ሰዓት በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በአፋር፣ በደቡብ ክልሎች የኩፍኝ፣ የችኩንጉኒያ ትኩሳት፣የጉድፍ በሽታ፣የወፎች ሞት፣አባሰንጋ እና የመሳሰሉ በሽታዎች ተከስተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በሀገሪቷ ያሉ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ኩፍኝ ፡- በሶማሌ ክልል፣ የችኩንጉኒያ ትኩሳት፡- አፋር ክልል፣ የጉድፍ በሽታ፡- በፌደራል የማረሚያ ቤት፣አበሰንጋ ፡-በደቡብ ጎንደር እና በቤንቺ ማጂ ዞን፣የወፎች ሞት በደቡብ ኦሞ ዞን በሃመርና በናፀማይ ወረዳዎች፣ሶማሌ ክልል ተከስቷል፡፡ ክትባት በዘመቻ በተሰጠባቸው ወረዳዎች የቀነሰ ሲሆን በሌሎች ወረዳዎች ግን እንደ አዲስ እየተከሰተ ይገኛል፡፡ ለዚህም ምለሽ የሚሆን ክትባት በአለም የጤና ድርጅት በኩል ተጠይቆ ምላሽ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል፡፡ ኦሮሚያ ክልል ተከስቶ የነበረ ሲሆን በተካሄደው የክትባት ዘመቻ የተጠቂዎች ቁጥር ቀንሷል፡፡

የችኩንጉኒያ ትኩሳት፡- አፋር ክልል አዳር ወረዳ በኢልውሃ ከተማ 991 ሰዎች በበሽታው የተጠቁ ሲሆን ለሁሉም የህክምና አገልግሎት ተሰጥቷል፡፡ ወረርሽኙንም ለመቆጣጠር የሚያስችል ስራ ከክልሉ ጋር እየተሰራ ይገኛል፡፡

የጉድፍ በሽታ፡- በፌደራል የማረሚያ ቤት የአሌሉቱ ፖሊስ ማሰልጠኛ ማዕክል 35 ሰልጣኝ ፖሊሶች በበሽታው ተይዘው የህክምና ክትትል አግኝተው 33ቱ የዳኑ ሲሆን 2ቱ ደግሞ የህክምና ክትትል ላይ ናቸው፡፡

አባሰንጋ ፡-በደቡብ ጎንደር 17 ሰዎች በበሽታው ተይዘው የነበረ ሲሆን ሙሉ በሙሉ ድነዋል፡፡ይሁንና በተሰጠው ምላሽ በሽታውን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ተችሏል፡፡

በቤንቺ ማጂ ዞን 57 ሰዎች በበሽታው ተይዘው የነበሩ ሲሆን የሁለት ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡ ይሁንና በተሰጠው ምላሽ በሽታውን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ተችሏል፡፡

የወፎች ሞት በደቡብ ኦሞ ዞን በሃመርና በናፀማይ ወረዳዎች የተከሰተ ሲሆን ክስተቱን የሚያጠናና የሚመረምር የባለሙያዎች ቡድን ወደ ስፍራው ተልኳል ፡፡

የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በሀገር ደረጃ ትኩረት ሊሰጥባቸው የሚገቡ ጉዳዮች በማለት ከዘረዘራቸው መካከል የክትባት እጥረት፣ ከፍተኛ የንጹህ ውሃ እጥረት፣ ከፍተኛ የመጸዳጃ ቤቶች እጥረት፣ የመጠለያ ችግር፣ የሰው ሃይል እጥረት፣ የደህንነት ስጋት ይገኙበታል፡፡

በአጠቃላይ የተፈናቃይ ወገኖቻችን ስቃይ ለመቀነስ እየተደረገ ያለው ጥረት ጥሩ ሆኖ ቀጣይ ተመሳሳይ መፈናቀሎችን እንዳይኖሩ የሚመለከታቸው የፖለቲካ ሃይሎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የጎሳ መሪዎች፣ ምሁራን እና ሌሎችም ቀጣይነት ያለው ሁሉ አቀፍ ውይይትና ምክክር ሊያደርጉ ይገባል፡፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ

** ኢትዮ ጵያን የተመለከቱ የተለያዩ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዘኛ ለማንበብ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close