Connect with us

Ethiopia

ችግር ፈጣሪዎቹን ትቶ ችግሩን የሚያሳድደው መንግስታችን…

Published

on

ችግር ፈጣሪዎቹን ትቶ ችግሩን የሚያሳድደው መንግስታችን…

ችግር ፈጣሪዎቹን ትቶ ችግሩን የሚያሳድደው መንግስታችን… | በአሳዬ ደርቤ

‹‹A problem well stated is a problem half solved›› የሚል አባባል አለ፡፡
ወደ እኛ አገር ስንመጣ ግን የሆነ ክልል ላይ ‹‹ችግር›› ተብሎ የተለየው ነገር… ሌላው ክልል ላይ ከመፍትሔ ዝርዝር ውስጥ ገብቶ እናገኘዋለን፡፡

ሙህራኑ ‹‹የአገራችን ችግሮች እነዚህ እነዚህ ናቸው›› ብለው የሚያቀርቧቸውን ህጸጾች…. ፖለቲከኞቹ ‹‹እነዚህማ ችግሮቻችን ሳይሆን የአንድነታችን ወሳኝ ምሰሶዎች ናቸው›› በማለት ይሰርዟቸዋል፡፡

የአንዱ ችግር ‹‹ብሔርተኝነት›› ሲሆን የሌላው ችግር ‹‹አሃዳዊነት›› ይሆናል፡፡

ያኛው የችግሩን ምንጭ ህገ-መንግስቱን ሲያደርገው ይሄኛው ደግሞ ለድርድር የማያቀርበው ዋነኛ መፍትሔው ያደርገዋል፡፡ የእንትና ክልል ነጻ አውጭ ለሌላው ክልል በሽታ አምጭ ሆኖ ያርፋል፡፡

ይሄንን ልዩነት ማስታረቅና የችግሩን ምንጭ ለይቶ ማወቅ ይገባዋል ብለን የምናስበው መንግስታችን ደግሞ ብቸኛ ችግሩን ‹‹ሶሻል ሚዲያውን›› አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

ከዚህ ባለፈ ግን ከህዝቡ ዘንድ የሚቀርቡ ችግሮችን መፍታት ቀርቶ መስማትም አይፈልግም፡፡ መስማት ቢችል እንኳን ማሽሞንሞን እንጂ ችግሩን ከስር መሰረቱ የመቅረፍ ድፍረትና ተነሳሽነት የለውም፡፡ ጫና ሲበዛበትም ምንጩን ትቶ ዥረቱን፣ ጎዳናውን ትቶ መንገደኛውን፣ ጥላቻውን ትቶ ንግግሩን፣ ችግር ፈጣሪውን ትቶ ችግሩን፣ በመንስኤው ፈንታ ውጤቱን…. ለማክሰም ነው እየተንፈራገጠ የሚገኘው፡፡

ለምሳሌ ያህል በአገራችን ብሔር ብሔረሰቦች መሃከል እየተስፋፋ ያለውን የጥላቻ መንፈስ ለማስወገድ ከተፈለገ ምንጮቹን እንጂ ንግግሩን ማስቆሙ መፍትሔ አይሆንም፡፡ ‹‹የጥላቻ ነቀርሳ ይጥፋ›› ከተባለ በምድሩ ላይ የተተከሉ የጥላቻ ሐውልቶች ቀርቶ በልብ ውስጥ የታተሙ ቁርሾዎች መወገድ አለባቸው፡፡ የተጣላውን ማስታረቅ፣ የተኳረፈውን ማስማማት ያስፈልጋል፡፡

መንግስታችን ግን ‹‹የጥላቻ ንግግሩ ከተገታ አስተሳሰቡ ይቀረፋል›› በሚል ከንቱ መላምት በጥላቻ ከተሞላ መሬት ላይ ፍቅር የሚሰብክ ኢንተርኔት እውን ለማድረግ አዋጅ እያረቀቀ ይገኛል፡፡ ከአኖሌ ሐውልት ስር መዋደድን የሚሸምቱ የአማራና የኦሮሞ ህዝቦች ሊፈጥር በመባተል ላይ ተጠምዷል፡፡ ከዚህ ባለፈም… ሁሉንም ውጥኖቹን ብንመለከት የምናገኘው እርምጃ ‹‹አህያውን ትቶ ዳውላውን›› እንደሚባለው ነው፡፡

‹‹ህገ-መንግስቱ የዚች አገር ዋስትና ነው›› በሚል አቋም… በዚህ ጉዳይ ላይ አልደራደርም ያለ መንግስት ቃሉን ተግብሮ ዋስትናችንን ሊያረጋግጥ ይገባል፡፡ ‹‹ለአገራችን ቀጣይነት ብሔርተኝነት ችግር አይሆንም›› ብሎ ካመነ ደግሞ በዜግነታችን የምንኖርባት አገር ሊፈጥር ግድ ይለዋል፡፡

እየሆነ ያለው ግን ይሄ አይደለም፡፡ በኢትዮጵያዊነት ካባ ውስጥ አክራሪ ብሔርተኝነት፣ በአንድነት ማህጸን ውስጥ ልዩነት፣ በለውጥ ማህደር ውስጥ ነውጥ፣ በመፍትሄ ከረጢት ውስጥ ችግር ነው እየተመረተ ያለው፡፡

አስቡት እስኪ…

ለባለፉት ጊዜያት ለጆሮ የሚዘገንኑ በርካታ ወንጀሎች ተፈጽመዋል፡፡ በእነዚህም ወንጀሎች በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ሲፈናቀልና በርካታ ዜጋ ሲገደል አይተናል፡፡ ሆኖም ግን በሁሉም ክስተቶች ውስጥ ሟቾቹ እንጂ ገዳዮቹ ስም የላቸውም፡፡ ተፈናቃዩ ካልሆነ በቀር አፈናቃዩ አይታወቅም፡፡ ወይም ደግሞ እንዲታወቅ አይፈለግም፡፡

በእነዚሁ ጸረ-ሰላም ሐይሎች የተነሳ የውጭም ሆኑ የእኛው ኢንቨስተሮች አገራችን ላይ መዋዕለ-ንዋያቸውን እንዳያፈሱና ዜጎቻችን በነጻነት እንዳይንቀሳቀሱ የታገዱ ቢሆንም….. መሪዎቻችን ግን ችግር ፈጣሪዎቹ ላይ እርምጃ ሊወስድ ቀርቶ በሥማቸው ጠርቶ ሊያወግዛቸው አልቻለም፡፡ እስከዚች ቀን ድረስ ለአረመኔዎቹ ‹‹አንዳንድ የታጠቁ ሐይሎች፣ አንዳንድ በእንትና ፓርቲ ስም የተደራጁ ቡድኖች፣ አንዳንድ የከሸፉ ሐይሎች…›› የሚል ሽፋን እየሰጠ እንዳሻቸው እንዲፈነጩ ፈቅዶላቸዋል፡፡

እናም በበኩሌ እነዚህንና የመሳሰሉ ነገሮች ሳሰላስል ‹‹በችግር ፈጣሪዎቹ እና በመንግስት ባለሥልጣናት መሃከል እኛ የማናውቀው የጋራ ጥቅም ይኖር ይሆን?›› የሚል ጥያቄ አነሳለሁ፡፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ

** ኢትዮ ጵያን የተመለከቱ የተለያዩ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዘኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close