Connect with us

Art and Culture

ከመገናኛ እስከ ቢርቢርሳ ጓሮ

Published

on

ከመገናኛ እስከ ቢርቢርሳ ጓሮ | አሳዬ ደርቤ

ከመገናኛ እስከ ቢርቢርሳ ጓሮ | አሳዬ ደርቤ

ወደ ፒያሳ የሚያደርሰኝ ታክሲ በማጣቴ የተነሳ መገናኛ ላይ ቁሜ አካባቢውን እቃኛለሁ፡፡
ህገ-ወጥ ደንብ አስከባሪዎች ህገ-ወጥ ነጋዴዎችን ያሯሩጣሉ፡፡

የአካል ጉዳት እንጂ የገንዘብ እጥረት የሌለባቸው የኔ-ቢጤዎች ከድሃው ህብረተሰብ ላይ ምጽዋት ይሰበስባሉ፡፡
‹‹ጩኻችሁ ብሉ›› ተብለው የተረገሙ ወያላዎች የአዲስ አበባን ሰፈሮች ይዘረዝራሉ፡፡

‹‹ዘርፋችሁ ኑሩ›› የተባሉ ሌቦች የሰው ኪስ ይመለከታሉ፡፡ መንገደኞቹ ደግሞ ኪሳቸውን አስር ጊዜ እየዳበሱ በፍጥነት አልፈው ይሄዳሉ……

‹‹ፒያሳ›› የሚል ታፔላ የተለጠፈበት ታክሲ እየተንፏቀቀ መጥቶ ከአጠገባችን ከመቆሙ መዓት ተሳፋሪ ከበበው፡፡
ወያላው የታክሲውን በር ለመክፈት እየታገለ ሳለ ‹‹ወንድም ፒያሳ ነህ?›› በማለት የሚጠይቁት በዙ፡፡

‹‹አይደለሁም ቢርቢርሳ ጓሮ ነኝ!›› የሚል መልስ ሲሰጣቸው ‹‹ቢርቢርሳ ጓሮ ደግሞ የት ነው?›› እየተባባሉ ወደ ኋላ አፈገፈጉ፡፡

በዚህን ጊዜም ይህችን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ተንደርድሬ ጋቢና ከገባሁ በኋላ… በታላቅ የአዋቂነት ስሜት ውስጥ ሆኜ ‹‹ቢርቢርሳ ጓሮ ማለት ፒያሳ መሆኑን አታውቁም›› ስላቸው… ታክሲዋ በራሷ ጊዜ ጥሩንባዋን አንባርቃ እንግልቷን እንድትገልጽ ያደረገ ግፊያና ትርምስ ተከሰተ፡፡

ወንበሬ ላይ ፈልሰስ ብዬ ‹‹አፋን-ኦሮሞ ተጨማሪ የፌደራል ቋንቋ‹‹ ይሆን ዘንዳ ይሁንታዬን እየሰጠሁ እንዳለ አንዲት ሞልቃቃ ድምጽ ያላት ኮረዳ የጋቢናው በር ከፍታ ‹‹እባክክን ጠጋ ትልልኝ›› በማለት በህይወቴ የማልወደውን ጥያቄ ጠየቀችኝ፡፡

‹‹ለሁለት ሰው አይበቃም›› ልላት አንገቴን ዞር ሳደርግ ለድንጋጤ የሚዳርግ ፈገግታ ጠበቀኝ፡፡

እናም ጠጋ ከማለትም አልፌ ‹‹ልውረድልህ እንዴ?›› እስኪለኝ ድረስ የሹፌሩን ወንበር ለሁለት ተጋርቼ መሪውን ጨበጥኩ፡፡

በጉዟችን መሃከል ልጂቱን እንጂ ጎዳናውን መመልከቱን ትቼው ነበር፡፡

ለቁንጅና ውድድር ብትቀርብ ተክለ-ሰውነቷና ውስጣዊ ውበቷ ሳይጨመር በራሳቸው ብቻ የወርቅ አክሊል ሊያመጡ የሚችሉ ዘጠኝ ጣቶች በመዳፏ ላይ አንጠልጥላለች፡፡ አንደኛው ጣቷ ግን የጋብቻ ቀለበት ያጠለቀ በመሆኑ ልቆጥረው ቀርቶ ቢለዋ ቢኖረኝ ኑሮ ብቆርጠው ደስ ይለኝ ነበር፡፡

ወያላው አንገቱን አስግጎ ‹‹ሂሳብ›› በማለት ሲጠይቅ ለቆንጆዋ ከፍዬ ሹፌሩን መዝለሉ የአገራችንን አንድነት የሚበታትን መስሎ ስለታየኝ ከሱሪዬ ኪስ አስራ አምስት ብር አውጥቼ የሶስት ሰው ሂሳብ ከፈልኩኝ፡፡

በዚህ ሁኔታ መነሻውን ከእንቡጥ ገላ ላይ ያደረገ ጥኡም መአዛ እየሳብኩኝ ፒያሳ ስደርስ በእግረኞች መንገዷ ላይ ከኮብል ስቶን በተጨማሪ መጽሔትና ጋዜጣዋን አንጥፋ ተቀበለችኝ፡፡ እናም ከታክሲው ስወርድ የጃዋርን እና የእስክንድርን ፎቶዎች የያዙ መጽሔቶችን እንዳልረግጥ መጠንቀቅ ነበረብኝ፡፡

የጉዞዬ ዓላማ በዋናነት የህትመት ውጤቶችን ለማንበብ በመሆኑ፣ የጀበና ቡና ወደሚሸጥበት ታዛ ከመሄዴ በፊት የተወሰኑ መጽሔቶችን መራርጬ ገዛሁ፡፡ ያው የሁሉም መጽሔቶች ይዘት ተመሳሳይ ስለሆነ መረጣውን ያካሄድኩት በምስል ድምቀትና በስም ላይ ተመርኩዤ መሆኑን ልነግራችሁ እፈልጋለሁ፡፡

ከዚያም በቅርብ ካገኘሁት ካፍቴሪያ በረንዳ ላይ ተቀምጬ መጽሔቶቹን አገላብጥ ጀመር፡፡

ቅኝቴን ከሽፋኑ ስጀምር… ባንድ ወቅት በሞደሊስትና በአርቲስት ቁጥጥር ስር ውሎ የነበረው መጽሔታችን አሁን በፖለቲካ ተንታኝና በአክቲቪስት የተያዘ ሁኗል፡፡

ሞደሎቻችን ሞንዳላ ጭናቸውንና የጡት ክፋያቸውን ገለጥ አድርገው በሚወጡበት የሽፋን ገጽ ላይ ጨለምተኛ አስተሳሰባቸው ፊታቸው ላይ የሚነበብ አክቲቪስቶቻችን ሰፍረውበታል፡፡

‹‹የአገሬን ባህላዊ አልባሳት የማስተዋወቅ ህልም አለኝ›› በሚለው የእህቶቻችን ንግግር ፈንታ ‹‹የዚች አገር ስጋት አክራሪ ብሔርተኝነት ወይስ አሃዳዊ ስርዓት›› በሚል አረፍተ-ነገር ተተክቷል፡፡

ሽፋኑን በዚህ መልክ ታዝቤ ወደ ውስጡ ስገባ…. በአንድ የዩኒቨርስቲ ሙህር ‹‹በአዲስ አበባ ዙሪያ ስላንዣበበው አየር›› የቀረበውን ትንታኔ በትኩስ ቡና እያጣጣምኩ ‹‹ወደ ገጽ አራት ዙሯል›› እስከሚለው ማሳሰቢያ ድረስ ተመስጬ ሳነብ ቆየሁ፡፡ ሆኖም ግን ጽሑፉ የሚያስተላልፈው መልዕክት ለስጋት የሚዳርግ በመሆኑ… ወደ ገጽ አራት የዞረውን ጽሑፍ ገልጨ በማንበብ ፈንታ አንገቴን ወደ አራቱም አቅጣጫ እየጠመዘዝኩ የምሁሩ ስጋት ምድሩ ላይ አለመኖሩን ማጣራት ግድ ብሎኝ ነበር፡፡

ከዚህ ባለፈ ግን ብእሩ ሁሉ ምድር ላይ ያለውን ክስተት የሚለፈልፍ እንጂ የጎደለውን ነገር የሚያስተላልፍ ባለመሆኑ መጽሔቶቹ ላይ አዲስ ነገር ማግኘት አይቻልም፡፡ በአንድ አንቀጽ የሚገለጸው ነገር በሶስት ገጽ ከመቅረቡ ውጭ ያው ‹‹ሶሻል-ሚዲያ›› ማለት ነው፡፡

ስለሆነም መጽሔቶቹን አጣጥፌ ወደ ቅኝቴ ስመለስ… ከፊት ለፊቴ ባንድ ወቅት ትልቅ ህንጻ ይሰሩበት ዘንዳ ለሼህ አላሙዲን ተሰጥቶ ከነበረው መሬት ላይ ዐይኔ አረፈ፡፡ ባለሃብቱም ቦታውን ከተረከቡ በኋላ በህንጻው ፈንታ ዲዛይኑን ለጥፈው ‹‹ከዛሬ ነገ እሰራዋለሁ›› እያሉ ቀን ሲያራዝሙ እሳቸውን የሚያሳስርና ህውሓትን የሚቀይር ዘመን ተከሰተ፡፡

ከለውጡ ጋር ወደ ሥልጣን የመጡት የመዲናችን ከንቲባም የሹመት ደብዳቤያቸውን በተቀበሉ ማግስት ይሄንን ቦታ በመውረስና አጥሩን በማፍረስ ሥራቸውን ጀመሩ፡፡

አሁን ታዲያ ከብዙ ወራቶች ቆይታ በኋላ ይሄንን ‹‹ባዶህን ቅር›› ተብሎ የተረገመ መሬት ሳስተውለው አንድ ነገር ብቻ ተቀይሮ አየሁ፡፡

((የህንጻው ዲዛይን ተሰቅሎበት ከነበረው ሰሌዳ ላይ ከኦዴፓ 28ኛ ዓመት የድል በዓል ጋር ተያይዞ የከንቲባውን ፎቶ የያዘ ባነር ተሰቅሎበታል፡፡))

 

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close