Connect with us

Ethiopia

ስንኖር ዋስትና የሌለን ስንሞት ዜና የሆነን ምስኪን ኢትዮጵያውያን

Published

on

ስንኖር ዋስትና የሌለን ስንሞት ዜና የሆነን ምስኪን ኢትዮጵያውያን፤

የክልሉም የዞኑም የጸጥታ አመራሮች ስጋቱን ኦነግ እንደፈጸመው ሲገልጹ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ግን አጥፊውን እከሌ ከማለት ተቆጥበዋል፡፡

ስንኖር ዋስትና የሌለን ስንሞት ዜና የሆነን ምስኪን ኢትዮጵያውያን፤
ከስናፍቅሽ አዲስ

የእኛ መንግስት ጥላቻ ላይ የጮህውን ያክል ገዳይ ላይ ዘራፍ ብሎ ቢሆን ይሄ ሁሉ አይፈጸምም ነበር፡፡ እርግጥ ነው የሃያ ሰባት ዓመት ቆሻሻ የዘር ፖለቲካ ውጤት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሃያ ሰባት ዓመታት ቆሻሻ የዘር ፖለቲካ ቢናኝም በስልጣን ላይ ያለው መንግሥት ልጓሙን የመሳብ፣ ቀበጡን የመቀንጠስ፣ ጉልቤውን ተው የማለት አቅም ነበረው፡፡

ሰሞነኛው የከሚሴ ክስተት፣ በማግስቱ የተከተለው የአጣዬና የማጀቴ ጦርነት መንግስት አለን ብለን ደጋግመን እንድንጠይቅ ያስገድደናል፡፡ የሟች ቁጥር የሚያሰላ መንግስት ባይኖር ምን ይቀራል ቢኖር ምን ይጠቅማል ያስባለን በየቀኑ ሞት ረክሶ ነው፡፡ በወለጋ የሞት ዜና፣ በአማሮ የሞት ዜና፣ በጭልጋ የሞት ዜና፣ በመተማ የሞት ዜና፣ በምንጃር የሞት ዜና፣ በከሚሴ የሞት ዜና፤ ዜና የሚያውጅ መንግስት ለመርዶ ነጋሪነቱ ከዜጎቹ ግብር ይሰበስባል፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ እስከ ዛሬ “መንግስትነትህ ቅጥ አጣ” ሲባል ነበር የምንሰማው፤ አሁን ደግሞ “መንግስት ሁን ድፈር ጎብዝ” እያልነው በየቀኑ ትግስቴ አልቋል ብሎ ያስጨረሰን መንግስት ዜጎች ሆነናል፡፡ የከሚሴው ችግር የሚያሳዝን ነው፡፡ አጣዬና ማጀቴን የጦር አውድማ ያደረገው ምክንያት መንግስት ባለበት ሀገር መፈጸም ያልነበረበት ነው፡፡

የአማራ ክልል የጸጥታ ሃላፊ ችግሩን ኦነግ እንደፈጠረው ገልጸዋል፡፡ የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር የጸጥታ ሃላፊም የሚጋሩት ይሄንኑ ነው፡፡ የተደራጀው ቡድን ኦነግ እንደሆነ ነበር ለአማራ ቴሌቨዥን በስልክ የገለጹት፡፡ ምሽቱን መግለጫ የሰጡት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው ጥፋቱ ያደረሰውን ጉዳት ኮንነው፣ ለሞተ አዝነው፣ ችግሩን ለመፍታት እየሰሩ መሆናቸውን በመግለጽ የችግሩ ፈጣሪ የሆነውን አካል እከሌ ነው ከማለት ተቆጥበዋል፡፡

እርግጥ ነው ዶክተር አምባቸው ለወንበሩ አዲስ ናቸው፡፡ ባለፉት አንድ ዓመታት ባልተረጋጋ ሃለፊነት የቆዩ ሰው ናቸው፡፡ የመጨረሻዎቹን ወራት ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ነበሩ፡፡ ስር ሰዷል በተባለው ችግር የሚወቀሱበት አግባብ አይኖር ይሆናል፡፡ የክልሉና የፌዴራል መንግስቱ ግን ከተጠያቂነት አያመልጡም፡፡

የአማራ ክልል ከዚህ ቀደም ህወሃት ያደራጀብኝ ሃይል ቅማንት ማህል መሽጎ የጦር ማሰልጠኛ ጭምር ከፍቶ ነበር አለን፤ ሰው በቤቱ እንዲህ ሆኖ ደርስኩበት ለማለት መጀመሪያ ጉዳዩ ሲፈጸም የት ሄዶ ነበር ያስብላል፡፡ የከሚሴውም ችግር እንዲሁ ነው፡፡ በብሔረሰብ ዞኑ የተለየ ቡድን ገብቶ ራሱን እያደራጀ የጦር ማሰልጠኛ ከከፈተ ቆየ ሪፖርት አድርገናል የሚሉ የአካባቢው የስራ ሃላፊዎች ተደምጠዋል፡፡ የክልሉ መንግስት ጣቱን ወደ ህወሃት ሲቀስር ዓይኑን መቀሌ አድርጎ ሲያጉረጠርጥ አጠገቡ እንዲህ ያለ አደጋ ሲፈጠር የማንን ጎፈሬ ሲያበጥር ነበር፡፡

እሺ የአማራ ክልል ሹማምንት ክልላቸውን ለመጠበቅ ህዝባቸውን ለመታደግ አቅምም ጉልበትም መንፈስም አይኑራቸው፡፡ እነሱ ሃላፊነት ባይሰማቸው እንኳን ለሀገር ደህንነት ሲባል መሃል ሀገር እንዲህ ያለ ህገ ወጥ ተግባር ሲፈጸም ህገ መንግስታዊ ባልሆነ አግባብ ቡድን ሲደራጅ የፌዴራሉ መንግስት የጸጥታ መዋቅር፣ ፌዴራል ፖሊስና አልፎ መከላከያ ምን ሲሰሩ ነበር?

አሁን ሰላማዊ የምንለው በዘፈን ፍቅሩን ሲገልጽልን የኖረው አብሮ የመኖሩ ማሳያ ቀጠኛችን የጦር አውድማ ሆኖ ውሎ ሲያድር ከተፍ የሚል ሃይል ከሌለን ነገስ ዋስትናችን ምንድን ነው? ስንኖር ዋስትና የሌለን ስንሞት ዜና የሆነን ምስኪን ኢትዮጵያውያን፤
እርግጥ እንዲህ ያለውን ዜና ተለማምደነው በችግሩ ማግስት ኮሚቴ ማቋቋም ተፈናቃይ መርዳት ሟች መቅበር ባህላችን ሆኖ መጥቷል፡፡ ቀጥሎ ስለሚሆነው እንጂ ስለሆነው መደንገጥ ቀንሷል፡፡ ግን ቀጥሎ የሚሆነውም የሰው ህይወት የሚነጥቅ ክፉ ተግባር ሲሆን እያየን ነው፡፡ ቀጥሎ የሚሆነውን መልካም ያድርግልን፤

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** የተለያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዝኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close