Connect with us

Ethiopia

የኤርትራ ጩኸት ለኢትዮጵያ ምኗ ነው ? በሬሞንድ ኃይሉ

Published

on

የኤርትራ ጩኸት ለኢትዮጵያ ምኗ ነው ? በሬሞንድ ኃይሉ

የኤርትራ ጩኸት ለኢትዮጵያ ምኗ ነው ? ሬሞንድ ኃይሉ@DireTube

ኤርትራ ልብ አርጉልኝ እያለች ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር ባለኝ ወዳጅነት የቀናችው ሱዳን እየረበሸችኝ መሆኑንም እውቁልኝ ብላለች፡፡ አስመራ እንደትናንቱ ብቻዋን ከካርቱም ጋር መፋለም የፈለገች አይመስልም፡፡ አዲስ አበባን ነገሩ ውስጥ ለመክተት ማለሟም የዚህ አካል ነው፡፡ የአልበሽር ወዳጆች ግን የፕሬዘዳንት ኢሳይያስን ስሌት ነገር ፍለጋ ካልሆነ ምን ሊባል ይችላል የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ስለጉዳዩ ትናንት ረፉዱን ምላሽ የሰጠችው ካርቱም የኢትዮጵያና የኤርትራ አዲስ ወዳጅነት ለዘመናት ስናፍቀው የነበረ በመሆኑ ደስታ እንጅ ቅናት የለብኝም ስትል ተደመጣለች፡፡ ከአስመራ የተነሳው ክስ ያስቆጣት ሌላዋ ሀገር ኳታርም የአስመራ ተግባር የማይገባ ነው የሚል ምላሽ ሰጥታለች ፡፡ የውዝግቡ መዳረሻ ግን በእነዚህ መግለጫዎች ብቻ የሚታሰር አይደለም፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት የቱርኩ ፕሬዘዳንት ራሲብ ጣይብ ኤርዶጋን በአፍሪካ ያልተለመደ ጉብኝታ ሊያደርጉ ወደ ካርቱም ጎራ ብለው ነበር ፡፡ የሰውየው አመጣጥ የሀገራቱን የባህልና ኢኮኖሚ ትስስር ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ነው ቢባልም ግቡ ግን ሌላ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ካርቱም ለሳዑዲ አረብያና ግብፅ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘውን ሱአኪን የተሰኘ ደሴቷን ለአንካራ አውሳታለሁ አለች፡፡ አልበሽርና ኤርዶጋንም ወደ ስፍራው አቅንተው የጥንቱ የኦቶማን ቱርክና ሱዳን ወዳጅነት ዳግም ታድሷል ሲሉ ተደመጡ፡፡ ሁለቱ መሪዎች በዚህ ንግግራቸው የእኛ ወዳጅነት ለማንም ስጋት አይደለም ሲሉም አረጋገጡ፡፡ ይሁን እንጅ የቱርክ ሱአኪንን አፋለማለሁ ማለት ለግብፅና ሳዑዲ አርብያ የሚዋጥ አልነበረም፡፡

ወዲህ የቱርክ መንግስት የግብፁ ፕሬዘዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ በህዝብ የተመረጡትን መሀመድ ሙርሲ አውረድው የነገሱ ወታደር ናቸው በሚል እውቅና እስከዛሬ አልሰጣቸውም፡፡ ወዲያ ከሳዑዲ አረብያ ጋር ጦር ቀርሽ ፀብ ውስጥ ያለችው ኳታር የምትደገፈው በአንካራ ነው፡፡ እነዚህ ምክንያቶች ደግሞ ካይሮና ሪያድ በካርቱም ላይ ተስፋ እንዲቆርጡ አደረጉ፡፡ እንዲህ ያለው አጣብቂኝ ኤርትራንም ወደ አንዱ አሰላለፍ እንድታዘነብል የሚያስገድድ ነበር፡፡ ወዲ አፎም አላመነቱም፡፡ ከዶሃ ይልቅ ሪያድ ትበልጥብኛለች አሉ ፡፡ በኤርትራና ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት ለፕሬዘዳንት ኢሳይያስ መንግስት የጦር መሳሪያ ግዥ በገፍ ዶላር ስታቀርብ የነበርችው ኳታር በጉዳይ ተበሳጨች፡፡ ከአዲስ አበባ ጋር ተቆራርጣ ወዳጅ ባደረገቻት አስመራ መከዳቷ ኪሰራው የገንዘብ ብቻ አይደለም ፡፡ በቀጣነው ያለው ስትራቴጅዋ በሙሉ ተናጋበት፡፡

ነዳጅ የሚዛቅባት ሚጢጢየዋ ኳታር ዓለም ከሳዑዲ ጋር አብሮ እሷ ላይ በተነሳባት ስዓት ቱርክ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከጎና ተሰለፈች፡፡ የኳታር ጠላቶች የእኔም ጠላቶች ናቸው ብላ ሳዑዲ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በምስራቅ አፍሪካ የሚያደርጉትን ነገር ለመግታት ደፋ ቀና አለች፡፡ የቀይ ባህር ፖለቲካ ቱርክና ኳታርን በአንድ በኩል ሳዑዲ መራሹን ኃይል በሌላ በኩል አፋጠጠ፡፡የሪያድ ጋሻ ጃግሬ የሆነችው አስመራ ዶሃን ማስቀየሟ ሳያንስ የሳዑዲ አጋር ለሆነችው ግብፅ የጦር ሰፈር ምስረታ የሚሆን ቦታ ቆርሳ ሰጠች ፡፡የኤርትራ ሰራዊት ከሳዐውዲ ጎን ተስለፎ ሊዋጋ የመን ድረስ ገባ፡፡

ነገርየው የፖለቲካ አረቄ ተጨምሮበት ሁለቱንም መሪዎች አሰከራቸው፡፡ ኳታር በቀጠናው ያላትን ጥቅም ለማስከበር በአንድ በኩል ከቱርክ ጋር ሁና በሱማሊያ ፖለቲካ ውስጥ መፈትፈት ስትቀጥል በሌላ በኩል የሳዐውዲ አጋር ሆኖ እንቅፋት የሆነባትን የፕሬዘዳንት ኢሳይያስ አስተዳደር ከመሰረቱ ለመገርሰስ ተንቀሳቀሰች፡፡ ለዚህ ደግሞ ከእሷ በላይ የሱዳን ወዳጅ የሆነችውን ቱርክን መያዝ ነበረባት ፡፡ በቀይ ባህር ያለ ተሳትፎዋን ማሳደግ የምትፈለገው አንካራ የዶሃን ጥያቄ እንደማታንገራግርበት እሙን ነው፡፡ እዚህ ላይ የሱዳን ምለሽ ምን ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ አይመስለኝም፡፡ ፕሬዘዳንት አልበሽር ኢኮኖሚያቸው ተንኮታኩቶ ዜጎቻቸው ስራ አጥ ሁነው ዙፋናቸውን እያነቃነቁ ነው፡፡ በዚህ ምክንያትም ረብጣ ዶላር ይዘው በራቸው የቆሙትን ቱርክና ኳታር እምቢ የማለት ወኔ የላቸውም ፡፡በዛ ላይ ዶሃ በቅርቡ አልበሽር የገጠመውን የኢኮኖሚ ቀውስ ለመፍታት በርካታ ዶላር ለግሳለች፡፡ ከዚህ ከፍ ሲልም ሀሳቡ እኮ የፕሬዘዳንት ኢሳይያስን ዙፋን እንነቅንቅ፣ ከተቻለ እናውርዳቸው የሚል ነው፡፡

ይህ ደግሞ ነገሩን የፋሲካ ዶሮ ያደርገዋል፡፡ በመሆኑም የሱዳን መንግስት በኳታርና በቱርክ በይፋ እንደሚደገፍ የሚነገርለትን የኤርትራ ሙስሊም ሊግ ካርቱም ላይ ምክክር እንዲደርግ ፈቀደ፡፡ በዚህ ሳይወስንም በኤርትራ ድንበር ላይ ቡድኑ እንቅስቃሴ የሚያደርገበት መደላድል ፈጠረ፡፡ 49 በመቶ የሚሆን የእስልምና ዕምነት ተከታይ ያላትን ኤርትራ የሚመሩት ፕሬዘዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ የሶስቱ ሀገራት ጥመረት ከስልጣነ መንበራቸው እንዳያወርዳቸው ሰግተዋል፡፡ ኤርትራ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተጣለባትን ማዕቀብ እንዲነሳ ያደረገችላት ኢትዮጵያ አሁንም ድጋፍ እንድታደርግላት ትፈልጋለች፡፡ ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ ከዛሬ ጀምሮ“ አምባሳደር ” አድርጌሃለሁ ያሉት ወዳጃቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከዚህ መአት እንዲያወጣቸው ይሻሉ፡፡

ወዲ አፎም ከአዲስ አበባ የዲፕሎማሲ ብቻ ሳይሆን የአጋርነት ድጋፍም ይፈልጋሉ ፡፡ ከቱርክና ኳታር ጋር ለኢትዮጵያ ብለው የተጣሉ ይመስል ከአዲስ አበባ ጋር የፈጠርኩት ዕርቅ ጣጣ አመጣብኝ ለማለትም ቃጥቶቸዋል ፡፡ ዋናው ቁምነገር ያለው ግን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አሰተዳደር የሚሰጠው ምላሽ ላይ ነው ፡፡ ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ታላቅ ወንድሜ የሚሉት ፕሬዘዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ድረስልኝ ሲላቸው ጆሮ ዳባ ልበስ ማለት ይቻላቸዋል ? ቱርክና ኳታርን ተመስሎ የመጣው የኤርትራ የለውጥ ዕድልስ በዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ይደናቀፍ ይሆን?

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ

** ኢትዮ ጵያን የተመለከቱ የተለያዩ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዘኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close