Connect with us

Art and Culture

ከአርቲስት ደበበ አድናቆት የዶክተር በድሉ ትችት ጣፍጦ የተገኘበት ዝግጅት

Published

on

ከአርቲስት ደበበ አድናቆት የዶክተር በድሉ ትችት ጣፍጦ የተገኘበት ዝግጅት | አሳዬ ደርቤ@DireTube

ከአርቲስት ደበበ አድናቆት የዶክተር በድሉ ትችት ጣፍጦ የተገኘበት ዝግጅት | አሳዬ ደርቤ@DireTube

በሚሊኒዬም አዳራሽ የተሰናዳው የጠቅላይ ሚኒስትራችን አንደኛ ዓመት ሲመት በዓል በጣም ብዙ ጉድለቶች የታዩበት ነበሩ፡፡ ዝግጅቱን ያዘጋጀው የጠቅላይ ሚኒስቴሩ ጽ/ቤት ሆን ብሎም ይሁን በግደለሽነት ከፕሮግራሙ ጀርባ ሌሎች መልዕክቶች እንዲተላለፉ መደረጉ ተገቢነት አልነበረም፡፡

ጥቂቶቹንም ለመጠቃቀስ ያህል፡-

1. ምንም የማያዉቁ ህጻናትን ለፖለቲካዊ ዓላማ ማዋል፡-

ህጻን ሴኔት እጅግ ፈጣን ጭንቅላት ያላትና ዘርፉ ቢለያይም ከእነ ህጻን ሮቤል ባምላክ ተርታ ልትሰፍር የምትችል ናት፡፡ ሆኖም ግን ህጻኗ በተፈጥሮ ባገኘችው ሰፊ ጭንቅላቷ የተፈጠረችበትን ዓላማ እንድታሳካ አልተፈቀደላትም፡፡

እናም ይች እንቦቃቅላ ህጻን መድረክ ላይ ወጥታ ስትፈነጭ እኔ መረዳት የቻልኩት በራሷ ሰፊ አዕምሮ የራሷን ሃሳብ እንድታስብ በማድረግ ፈንታ በእነሱ ጭንቅላት ልክ የሆነ አስተሳሰብ እንድታራምድ መገደዷን ነው፡፡

ይሄም ሆኖ ግን ህጻኗ የተሰጣትን ሃሳብ ይዛ ስትመጣ የፕሮግራሙ አዘጋጆች ግጥሙን ገመግምው በማስተካከል ፈንታ እንደ ወረደ እንድታቀርብ ማድረግ አልነበረባቸውም፡፡ ምናልባት ይሄን ያደረጉት ሃሳቡን ስለሚጋሩት ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም የፕሮግራሙን ዓላማና ተመልካቹን ግምት ውስጥ በማስገባት የተወሰነ እርማት ማድረግ ነበረባቸው፡፡

2. የአርቲስት ደበበ እሸቱ መድረክ መሪነት፡-

አርቲስት ደበበ እሸቱ እድሜና ጤና የምንመኝላቸው አንጋፋ አርቲስት ናቸው፡፡ በፖለቲካው ላይም የግላቸውን ተሳትፎ አድርገው ለእስር ተዳርገዋል፡፡ ሆኖም ገዥው ፓርቲ አዲስ አበባን አኬልዳማ የሚል ዶክመንተሪ ላይ እንዲተውኑ አድርጎ ከእስር ከፈታቸው በኋላ ከፖለቲካው ሊርቁ ችለዋል፡፡

ይሄን ብየ ወደ ፕሮግራሙ ስመጣ ጋሽ ደበበ የተመረጡበት ምክንያት ግልጽ ካለመሆኑም በላይ መድረኩን ሲመሩት የነበረው ለእራሳቸውም ሆነ ለተመልካቹ በማይመጥን ሁኔታ ነበር፡፡ አብራቸው መድረኩን ስትመራ እንደነበረችው ሴት በተገቢው ሁኔታ ፕሮግራሙን በማስተዋወቅ ፈንታ በግላቸው ሙገሳና ወቀሳ መጠመዳቸው መድረኩን አሰቃቂ አድርጎት ነበር፡፡ ከእሳቸው በማይጠበቅ መልኩ የሶሻል ሚዲያ ተጠቃሚውን ማህበረሰብ ‹‹አረቄውን እየጠጣ›› በማለት ሲወርፉ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ደግሞ ከእግዜሩ ጋር ሊያመሳስሉት መሞከራቸው አስገራሚ ነበር፡፡

3. የመድረኩ አግላይነት፡-

እንደ እኔ አተያይ የሚሊኒየሙ ዝግጅት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ይልቅ ‹‹የለውጡ አንደኛ ዓመት›› ተብሎ ቢከበር ጥሩ ይሆን ነበር ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህ ከሆነ እንኳን ሙገሳው ሁሉንም የለውጥ ሃይሎች የሚያቅፍ መሆን ነበረበት፡፡

ከመድረክ መሪዎቹ አንስቶ እስከ አቅራቢዎቹ ድረስ የለውጡን መሪዎች ሲዘረዝሩ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን የተቀመጡትን ምክትል ጠቅላይ-ሚኒስትርን እረስተዋቸው ነበር፡፡

4. ‹‹ታላቁን መሳሪያ አደረግነው ፋራ›› የሚል ግጥም መቅረቡ

የታገል ሰይፉ ግጥሞች እንደ ዘመነኞቹ ገጣሚያን በትንሽ ቃላት ብዙ መልዕክት ባያስተላልፉም እንኳን የሚያዝናኑ በመሆናቸው ይታወሳሉ፡፡ በተለይ ደግሞ በምስል አቀናብሮ ሲለቃቸው የነበሩት ግጥሞቹ ከህጻናት ጭንቅላት ውስጥ የሚጠፉ አይደሉም፡፡

ሆኖም ታገል ሚሊኒየም አዳራሽ ላይ ያቀረበው ግጥም ግን በመልክቱም ሆነ በቤት ዓመታቱ እጅግ ደካማ ነበር፡፡ ምክንያቱም ገጣሚ ማለት የተፈረጀውንም ሆነ የተባረከውን ነገር በራሱ ዓይን መርምሮ ሌሎች ባላሰቡት መንገድ የሚከስት እንጂ በስድ ንባብ የሚወራውን በስንኝ ሰድሮ የሚያቀርብ አይደለም፡፡ ታገል ግን በግጥሙ ቤት አስመትቶ ያቀረበው የህውሓትን ስሞታ እንደወረደ ነበር፡፡ እሱ ሚሊኒየም አዳራሽ ለተገኘበት ለውጥ የፌስቡክ ሚና ከፍተኛ ቢሆንም ገጣሚው እዚያ ያሉትን ባለሥልጣናት ለማስደሰት ሲል እዚህ ያለውን ሁሉ አጠልሽቶ ማቅረቡ ሶሻል ሚዲያን ሳይሆን አስተሳሰቡን የገለጠ ሁኖ አልፏል፡፡

እናም በአጠቃላይ የሚሊኒየሙ ዝግጅት ‹‹የፊንፊኔ ኬኛ›› እና ‹‹የአዲስ አበባ ቤቴ›› ፉክክር ነግሶበት ሲታይ ፕሮግራሙ በፌስቡክ አክቲቪስቶች የተዘጋጀ የሚመስል ነበር፡፡

ይሄም ሆኖ ግን የዶክተር በድሉ ዋቅጅራ እና የዶክተር አቢይ ንግግሮች ከባላገሩ ባንድ ሙዚቃ ተጨዋቾች ጋር የሚደነቁ ሆነው አግኝተናቸዋል፡፡ በተለይ ደግሞ ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ ያለምንም መርመጥመጥ በውብ ብዕሩ እንደ ማህበረሰብ የገባንበትን ዝቅጠት ተንትኖ ሁሉም ባለሥልጣናት ባሉበት ማቅረቡ የሚያስመሰግነው ነው፡፡ ለመንግስታችንም ሆነ ለአገራችንም ቢሆን የሚጠቅመው ከዶክተር በድሉ አይነት እውነተኛ ሰዎች የሚሰነዘር ትችት እንጂ የአርቲስት ደበበ አይነት ከጊዜ ጋር የሚራመድ አድናቆት አይደለም፡፡

የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ

ኢትዮ ጵያን የተመለከቱ የተለያዩ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዘኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close