Connect with us

Ethiopia

ርኅርቷ ንግሥት: የንግሥት ዘውዲቱ የ 89 ዓመት ሕልፈተ ዝክር፣

Published

on

ርኅርቷ ንግሥት: የንግሥት ዘውዲቱ የ 89 ዓመት ሕልፈተ ዝክር፣

ርኅርቷ ንግሥት
የንግሥት ዘውዲቱ የ 89 ዓመት ሕልፈተ ዝክር፣
በዕዝራ ኃይለ ማርያም
የሀገሬ የኢትዮጵያ ሰው
መኳንንቱም ሊቃውንቱም ሠራዊቱም
ስሙኝ ልንገራችሁ፣

ስንኳን በዚህ ፍጡር በሚያዝንበት ዓለምና በወዲያኛውም እግዚአብሔር እንደ ሥራ፣እንደ ሥራው ከሚያወርሰው መንግሥት ከመገፋቴና በመከራዬ ጽናት የተነሣ ገርነት ቸርነት ገንዘቡ የሚሆን ፈጣሪዬን ተጠራጥሬው ነበር፡፡ አሁን ግን እግዚአብሔር በደጉ ጊዜ በኢትዮጵያ ሕዝብ በእናንተ አድሮ በምሕረቱ ከጎበኘኝ ከመከራዬና ከግፌ ጥቂት ጥቂት አመለክታለሁ፡፡ እንኳን ኢትዮጵያን የሠጠ አባትና ሰው የገደለውን ቢሆን ቅጠል ከላዩ ሳይጥል የሚሄድ ማነው? ከሞተስ በኋላ በዓለም በኖረበት ቦታ ፍታት ተከልክሎ ስሙ ሳይጠራ የቀረ ክርስቲያን ማነው? በአሠሩዋቸው አብያተ ክርስቲያናት ስማቸው እንዳይጠራ ሆኖ ነበር፡፡ የጌታችሁ የአጼ ምኒልክ ግፍ ይህ ነው፡፡

ደግሞ የአባትዋን ሬሳ ታቅፋ ስንኳን ፪ ዓመት ከ፫ ወር ፪ ቀን ያደረች ማን ናት? በኀዘንዋስ ጊዜ የሚያጽናኑዋት ዘመዶቿ ተከልክለውባት ብቻዋን ያዘነች ማነች? ደግሞም በዚህ ሁሉ መከራዬ ላይ የአባቴን ሬሳ ታቅፌ እያለቀስሁ በኖርኩ ምን አድርጉልኝ ብል ከከተማ አባቴን አፈር ሳላላብስ ወጣሁ፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር በናንተ አድሮ ሥራውን ሰራ፡፡አሁንም ሃይማኖታችሁንና አገራችሁን መንግሥታችሁን ለመጠበቅ የጌታችሁን ስም እንደ አባቶቻቸው ለማስጠራት አነሳስቷችኋልና በሰው ግፍ ቢሠራ የማይወድ እግዚአብሔር አይለያችሁ ብዬ ተስፋ አለኝ፡፡ …

ይህ መልእክት፣ልጅ ኢያሱ ተሽረው ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ በአባታቸው በአጼ ምኒሊክ አልጋ እንደተቀመጡ መስከረም 22 ቀን 1922 ዓ.ም ለሕዝቡ በይፋ ከተነበበ ቃላቸው ውስጥ የተወሰዱ አንቀጾች ናቸው፡፡ መልእክቱ ከዚህ ቀደም የደረሰባቸውን ግፍና አበሳ የሚያመለክት ነበር፡፡ ቃሉ የሚያሳዝን ስለነበረ ሲነበብ የአጼ ምኒሊክ አሽከሮች አብዛኞቹ ያለቅሱ እንደነበር መርስኄ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ “የሐያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ” በሚለው መጽሐፍ ጠቅሰውታል፡፡

እነሆ ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ካረፉ ዛሬ 89 ዓመት ሞላቸው፡፡ ይህ መጣጥፍ በውጣ ውረድና በኀዘን የተሞላውን የግርማዊት ንግሥትን፣የራስ ጉግሳ ወሌን እና የአንቺም ጦርነትን በአጭሩ ይመለከታል፡፡

ለዳግማዊ ምኒልክ ሦስተኛ ልጅ የሆኑት ወይዘሮ ዘውዲቱ ሚያዝያ 22 ቀን 1868 ዓ.ም በወቅቱ የሸዋ ንጉሥ ከነበሩት ምኒልክና ከወሎዋ ባላባት ከወይዘሮ አብቺው በእነዋሪ ከተማ ከተማ ተወለዱ፡፡ በዚያን ዘመን የነበረው ጋብቻ ለድሀው “ትውልድን ማስቀጠያና መጦሪያ” ሲሆን ለነገሥታትና ለባላባቶች ደግሞ የኃይል ሚዛንን ማስጠበቂያ “የፖለቲካ ጋብቻ” ነበር፡፡ ወይዘሮ ዘውዲቱም በስድስት ዓመት ከስድስት ወር ዕድሜያቸው የ12 ዓመት ዕድሜ የነበራቸውን የአጼ ዮሐንስን ልጅ ራስ አርአያ ሥላሴን ጥቅምት 13 ቀን 1875 ዓ.ም ወረኢሉ ላይ በተክሊልና በቁርባን አገቡ፡፡ ራስ አርአያ ሥላሴ ሰኔ 19 ቀን 1880 ዓ.ም አረፉ፡፡

ከላይ በተለጸው መጽሐፍ ላይ እንደተጠቀሰው ከሆነ ወይዘሮ ዘውዲቱ ከደጃዝማች ጓንጉል ዘገየ አንዲት ሴት ልጅ ቢወልዱም ሕጻንዋ በ2 ዓመትዋ ሞታ በአዲስ አበባ ሥላሴ ተቀብራለች፡፡ በኋላም ለደጃዝማች ውቤ አጥናፍ ሰገድ ተድረው ከአራት ዓመት በኋላ ተፋተዋል፡፡

ወይዘሮ ዘውዲቱ በ1893 ዓ.ም የእቴጌ ጣይቱ ወንድም ልጅ የሆኑትን የበጌ ምድሩን ገዥ ራስ ጉግሣ ወሌን አገቡ፡፡ ዘውዲቱ “የፖለቲካ ጋብቻ” መስዋዕት ሆነው ከአንድ በላይ ጋብቻ በመመስረት “ሲዳሩና ሲኳሉ” ቢቆዩም በሁለት ዓመቷ ከሞተችው ሕጻን በስተቀር ወልደው ለመሳም አልበቁም፡፡ ንግሥተ ነገሥታት ከሆኑ በኋላም ከሚወዷቸው ባለቤታቸው ከራስ ጉግሣ ወሌ ጋር እንኳ አብረው እንዲኖሩ አልተፈቀደላቸውም፡፡

ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ዳግማዊ ምኒሊክ በ1901 በታመሙ ጊዜ ከባላቸው ጋር ከሚኖሩበት ደብረ ታቦር ትዳራቸውን ትተው አዲስ አበባ በመቆየት አባታቸውን አስታመዋል፡፡ ዳግማዊ ምንሊክ ወንድ ልጅ ስላልነበራቸው በአዋጅ አልጋ ወራሽ ያደረጓቸው ከልጃቸው ከወይዘሮ ሸዋ ረገድ እና ከወሎው ንጉሥ የሚወለዱትን የልጅ ልጃቸውን አቤቶ ኢያሱ ሚካኤልን ነበር፡፡ዳግማዊ ምኒልክ ታኅሳስ 03 ቀን 1906 ዓ.ም አረፉ፡፡ ኢትዮጵያ ብልሁ መሪዋን ካጣች በኋላ ያጋጠማት መሪ ልጅነቱን ያልጨረሰ በዚህ ዘመን ቋንቋ “ፍንዳታ” ነበር፡፡ ከአጼ ምኒሊክ ሕመምና እረፍት በኋላ የመሸጋገሪያ ዘመን በመሆኑ የሥልጣን ሽኩቻ በዛ፡፡አጼ ምንሊክ በጥበብና በፍቅር የያዟቸውን ትላልቅ ባለሥልጣናት ልጅ ኢያሱ ተገቢ ክብር ባለመስጠት፣በመሻርና በማግለል በሁለንተናዊ ስብእናቸው የቀድሞዎችን የማይተኩ ሹማምንትን ሰበሰቡ፡፡ ጠላትን ማብዛትና የወዳጅን ቁጥር መቀነስ የሰርክ ተግባራቸው አደረጉ፡፡ብዙውን ጊዜ የመንግሥቱን ሥራ በመተው በየሀገሩ ይዞሩ ነበር፡፡

የአባታቸው ዳግማዊ ምኒሊክ ማረፍ ከማንም በላይ የጎዳው ንግሥት ዘውዲቱን እና እቴጌ ጣይቱን ነበር፡፡ ልጅ ኢያሱ እቴጌ ጣይቱን ከቤተ መንግሥት አስወጥተው በእንጦጦ ማርያም፤ ወይዘሮ ዘውዲቱን ደግሞ ፋሌ በሚገኘው እርስታቸው ላይ ግዞተኛ አደረጓቸው፡፡ ራስ ጉግሣ ወሌም ከአፍቀራ መጥተው ፋሌ ላይ ከባለቤታቸው ከወይዘሮ ዘውዲቱ ጋር እንዲቀመጡ ስለተፈቀደላቸው ከባላቸው ራስ ጉግሣ ወሌ ጋር ተገልለው እስከ ንግሥናቸው ጊዜ ተቀምጠዋል፡፡

ልጅ ኢያሱ በመናፍቅነት፣በአንደኛው የዓለም ጦርነት የሚዋጉትን ጀርመንና ቱርክን የመደገፍ አዝማሚያ አሳይተዋል፣የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ሚዛንን አልጠበቁም፣ በጊዜው የነበረውን የመሪነት ሥነ ምግባር አልጠበቁም እና ለዘወዱ ግርማ ሞገስ አልሆኑም ተብለው ተከሰሱ፡፡ ትኩረት ግን አልሰጡም፡፡ በዚያን ዘመን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የነበራትን የአንጋሽና የሻሪነት ኃይልና ሚናን በቅጡ ያልተገነዘቡት ልጅ ኢያሱ ለጠላቶቻቸው ጥቃት ተመቹ፡፡ የልጅ ኢያሱን አልጋ ለመገልበጥ በሸዋ በሕቡእ ሲካሔድ የቆየው አድማ ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ የሆነው የመስቀል ደመራ ዕለት በ1909 ዓ.ም ነው፡፡ “የውልቃትና የስብራት እንጂ የሰባራ ስም ወጌሻ የለውም” እንዲሉ ልጅ ኢያሱ በራሳቸው ድካም ጭምር በሴራ ፖለቲካ ተጠልፈው ወደቁ ፡፡

ዘውዲቱ የአባታቸውን አልጋ በኃይል ለመውረስ ፍላጐት አልነበራቸውም፡፡ መስከረም 17 ቀን 1909 ዓ.ም የሸዋ መኳንንት ተሰብስበው ልጅ ኢያሱን ከመንግሥት መሪነት ሻሩ፡፡ በጊዜው በሕይወት ያሉት የዳግማዊ ምኒልክ ልጅ፣ ዘውዲቱ ብቻ ስለነበሩ የመኳንንቱና የሚንስትሮቹ ምርጫ በእሳቸው ላይ ሆነ፡፡ወይዘሮ ዘውዲቱን ከባለቤታቸው ራስ ጉግሣ ጋር በግዞት ከሚኖሩበት ግንደ በረት አካባቢ ከሚገኘው ከፋሌ አስመጥተው፤ንግሥተ ነገሥታት አሰኝተው በዳግማዊ ምኒሊክ ዙፋን አስቀመጡዋቸው፡፡ዕድሜያቸው 41 ነበር፡፡ ደጃዝማች ተፈሪ መኮንንን ራስ ተብለው የኢትዮጵያ መንግሥት አልጋ ወራሽና እንደራሴ ሆኑ፡፡ በአባታቸው አልጋ እንዲነግሡ መመረጣቸውን እንኳ አልሰሙም ነበር፡፡ወሬውን የነገሯቸውን ሰዎች “ሐሰተኛ ወሬ” ነው ብለው አሳስረዋል፡፡ ያረጋገጡትም፣ ሰው አዲስ አበባ ልከው አዋጁ ከታወጀ ከሁለት ቀናት በኋላ ነው፡፡

መጋቢት 24 ቀን 2007 ዓ.ም በሸገር ራዲዮ እንደቀረበው በሀገራችን ታሪክ በ10ኛ ክፍለ ዘመን ከነገሠችው ዮዲት ቀጥሎ ዘውዲቱ፣ ለኢትዮጵያ መሪ የሆኑ የመጀመሪያዋ ሴት ንግሥተ ነገሥታት ናቸው፡፡ ባለሙሉ ስልጣን እንደራሴውና አልጋ ወራሽ ተፈሪ ስልጣናቸውን ሲሸራርፉ “በዘመኔ ሀገሬን፣የርስ በርስ ጦርነት ተፈጥሮ ደም ከሚፈስና በዚህ ሰበብም የውጭ ወራሪ ከሚገዛት የተጠየቅሁትን ስልጣን ለቅቄ ብኖር ይሻለኛል” ይሉ ነበር፡፡ የዳግማዊ ምኒልክ ጎምቱ የጦር አዛዦችና መኳንንት መድከምና መሞት ለንጉሥ ተፈሪ መጠናከር ጠቅሟል፡፡ ተፈሪ መኮንን በ1921 ዓ.ም “ንጉሥ” የሚለውን ማዕረግ ወስደው የንግሥትን ስልጣን አዳክመዋል፡፡

ንግስተ ነገሥታት ዘውዲቱ፣ የግል ዝናን ስለማይፈልጉ፣ የመስሪያ ቤቱ ስራ ሁሉ የሚካሄደው በአፄ ምኒልክ ስም ነበር፡፡ በመልካቸው የተቀረፀውን ሳንቲም ለመታሰቢያ ብቻ እንዲታተም አድርገው፣ የአባታቸው ምስል፣ ያሉባቸው ሳንቲሞች በመገበያያነት እንዲቀጥሉ አድርገዋል፡፡

ባለቤታቸው ራስ ጉግሣ ወሌ የንግሥቲቱ የዘውድ ሥልጣን ተካፋይ ሆነው ከደጃዝማች ተፈሪ መኮንን (በኋላ አጼ ኃይለ ሥላሴ) ጋር በሥልጣን እንዳይጋጩ በመስጋት የአማራ ሳይንት ግዛትን ተሾሙ፡፡ ወይዘሮ ዘውዲቱ ንግሥተ ነገሥታት ቢሆኑም የሚወዷቸውን ባለቤታቸውን አጠገባቸው ማስቀረት አልቻሉም፡፡ ራስ ጉግሣም ወደ ተሾሙበት ግዛት እንዲሄዱ በመታዘዛቸው የካቲት 04 ቀን 1922 ዓ.ም በተደረገው የንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ የንግሥ በዓል ላይ በመገኘት የደስታቸው ተካፋይ አልሆኑም፡፡ ይህም ራስ ጉግሣን ቅር አሰኝቷል፡፡

ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ በባሕርያቸው ጭምት፣መንፈሳዊ፣ ቅንና ርኅርት በመሆናቸው ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት በጾም፣ በጸሎትና በግብረ ሠናይ ነበር፡፡ ራስ ጉግሣ ወሌ የቀድሞ ግዛታቸው በጌ ምድር ተመልሶላቸው ለ10 ዓመት ደብረ ታቦር ከተማ በገዥነት ኖረዋል፡፡ ከራስ ተፈሪ ጋር ያላቸው ቅራኔ ከእለት እለት እየሰፋ መጥቷል፡፡ ራስ ወሌ ጉግሣ መንፈሳዊ፣የአባቶች ወግ፣ ልማድና እድር መጠበቅ አለበት ብለው የሚያምኑ ወግ አጥባቂ ሲሆኑ ተፈሪ መኮንን ለዘመናዊ ሥልጣኔ ክፍት፣ንቁና በሴራ ፖለቲካ የተካኑ ናቸው፡፡ በዚህም የተነሳ የተፊሪ መከንንን ትእዛዝ በጥርጣሬ በመመልከት አይታዘዙም ነበር፡፡

ገና ከጅምሩ የአልጋ ወራሽ ተፈሪን አመራር የሚቃወሙትና ያቄሙት ራስ ጉግሣ በአልጋ ወራሹ ላይ የሚሰሙት ነገር በላዩ በላዩ እየተጨማመረ ልባቸው ከመንግሥት ሸፈተ፡፡ ‹‹ዘውዲቱን ሥልጣን አልባ አድርገዋቸዋል›› የሚል እምነት ነበራቸው፡፡ “ራስ ተፈሪ መኮንን ካቶሊክ ሆነው ሃይማኖታቸውን ለውጠዋል፣ በአዲስ አበባ ውሻና አህያ ታረደ፣ በሥላሴ ቤተ ክርስቲያንም የውሻ መስዋዕት ተሠዋበት” የሚል ወሬ ሰምተው አዝነዋል፡፡ ወሬውን በጎንደር ከተማ ያለው ዴላውሮ የሚባለው የኢጣሊያ ቆንስልና ባልደረቦቹ ቀምመው በማቅረብ በኩል አልሰነፉም፡፡ ራስ ጉግሣ በዚህ ወሬ “ሃይማኖታችን ሊጠፋ ነውና ለሃይማኖታችን እንዋጋ” ብለው ሕዝብን ቀስቅሰው ለጦርነት አሰልፈዋል፡፡

ነገሩ እንዲህ ነው፡፡አንድ የውጭ አገር ሰው የውሻ ቆዳ አልፍቶ ለንግድ ለማዋል ከአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ፈቃድ ወሰደ፡፡ በሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አቅራቢያ ያለውን የአቶ ከበረ ኃይለ ሥላሴን ቤት ተከራይቶ ፋብሪካ ተከለ፡፡ አቶ ከበረ በዚሁ ደብር እየተማረ ያደገ የድጓ አስተማሪው የአለቃ ኃይለ ሥላሴ ልጅ ነው፡፡ ሚያዝያ 7 ቀን 1921 ዓ.ም ግርማዊ ንጉሥ ተፈሪ የሥላሴን ቤተ ክርስቲያን ለመሳም ሄደው ሳሉ የደብሩ ካህናት በድጓ አስተማሪው ቦታ ውሻ ታረደበት፣ደብራችን ተደፈረ ብለው ጉዳዩን ወደ ሃይማኖታዊ ጉድለት በማዞር አቤቱታ አቀረቡ፡፡ የፋብሪካው ሥራም ተከለከለ፡፡

አቶ ከበረም የማዘጋጃ ቤት ክፍል ሹም ነበረና ለጥቅሙ ሲል ያደረገው ነው ተብሎ ተጠርጥሮ ታሰረ፡፡ ቦታውና ቤቱም በውርስ ተያዘበት፡፡ ወሬው የተለያየ ቅርጽ እየያዘ ተሰራጨ፡፡”በሥላሴ ደብር የውሻ መሥዋዕት ተሰዋ” እስከ መባል ደርሶ በተለይ ትላልቆቹን መኳንንትና ሕዝብ አስከፋ፡፡

ንጉሥ ተፈሪ በ1921 ዓ.ም ከንግሥና በዓላቸው በኋላ ወደ ወረኢሉና ወደ ደሴ ለመሔድ አስበው ራስ ጉግሳን ወረ ኢሉ መጥተህ ላግኘህ ቢሏቸው ምክንያት እየፈጠሩ መገናኘት አልፈለጉም፡፡ በኋላም ደሴ ድረስ እንዲመጡ ቢያዟቸውም ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ ለጦርነት ይዘጋጁ ነበር፡፡ ከጎጃሙ ገዥ ከራስ ኃይሉ ጋር ተላልከው ለውጊያ እንዲረዳዱ የውስጥ ስምምነት አደረጉ፡፡ ራስ ኃይሉም ብዙ ጥይት እንደላኩላቸውና በሐሳብ እያበረታቱ እንደ ገፋፉዋቸው ይነገራል፡፡ ከጎንደሩ የኢጣሊያ ቆንስል ዴላውሮ ጋር ግንኙነትና ምክር አደረጉ፡፡ ሕዝቡንም “ለሃይማኖትህ ስትል ተጋደል” እያሉና በሌላም መደለያ ለጦርነት ያደራጁ ነበር፡፡ መንግሥትም ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ የክተት ሥራ ማካሄድ ጀመረ፡፡

በራስ ጉግሣና በንጉሥ ተፈሪ መካከል በተፈጠረው ግጭት ጭንቅ ውስጥ የገቡት ንግሥት ዘውዲቱ ናቸው፡፡ ጦርነት እንዳይፈጠር ብርቱ ጥረት አድርገዋል፡፡ለራስ ጉግሣ ወሌ አንጀት የሚበላ የስልክ መልእክትና ደብዳቤ ሳይሠለቹ ይልኩ ነበር፡፡

እስቲ ንግሥት ለራስ ጉግሣ ከላኳቸው በርካታ መልእክቶች ውስጥ ጥር 29 እና የካቲት 09/ 1922 ዓ.ም የላኳቸው ሁለቱን እንመልክት

ይድረስ ለራስ ጉግሣ ወሌ

ባንተ ላይ የምንሰማው ነገር ሁሉ ቢያስቸግረኝ እነ ፊታውራሪ ወልደ ሚካኤል በቶሎ ይምጡ ብዬ ከዚህ ቀደም በስልክ ልኬብሃለሁ፡፡ እኔ ግን የምሰማውን ነገር ሁሉ ታደርገዋለህ ብዬ አልጠራጠርም፡፡ ሰው እያገነነ ሲያወራው ጊዜ ቢቸግረኝ ነው፡፡
የተከፋህበትስ ነገር ቢኖር እንደዚህ ያለ ተቀይሜአለሁ፡፡ ይህን አድርጉልኝ ብለህ ሳትልክብኝ ሌላ አሳብ ታስባለህ አልልም፡፡

አሁን እኔ ይህን ሁሉ ነገር መጻፌ የሚከፋብህን ነገር የሚነግሩህ እናትህ እቴጌ ጣይቱ፣ አባትህ ራስ ወሌ የሉምና እንደ እናትም እንደ አባትም እንደ ዘመድም ሆኜ በመንግሥቴ ስም ሳይሆን በተለየ ዝምድናዬ ነው፡፡

አሁንም ንጉሥ ተፈሪ ወደ ደሴ ሊነሳ ነውና ያልዘመተውን ሰው ይዤ ንጉሥ ተፈሪ በመጡ ጊዜ እመጣለሁ ብለህ አንተው እንደ ላከው ቃል በዚህ ቀን እንገናኝ ብሎ በላከብህ ጊዜ አንተም በዚያው ቀን ተነስተህ እንድትመጣ ይሁን፡፡
የሚል ነው፡፡ ራስ ጉግሣ ምላሽ ባለመስጠታቸው የካቲት 09 ቀን 1922 ዓ.ም እንደገና ሌላ መልእክት ላኩ፡፡

ይድረስ ለራስ ጉግሣ ወሌ
ከዚህ ቀደም ይህን ያልሆነ ወሬ እንደ ሰማሁ በጥር 29 ቀን በስልክ ልኬብህ ነበር፡፡ አልደረህምን፡፡ አሁንም ያንኑ የላኩብህን ቃል በውል ተመለክተህ ይህን ያልሆነ ክፉ አሳብ ከልቦናህ አጥፍተህ አንተም ባልሆነ ነገር እንዳትጠፋ እኔም ባላሰብኩት ባልተነጋገርነው ነገር ንግሥት ልከውበት ነው ይህ ሁሉ ነገር የተነሳው እየተባለ ሰው ሁሉ ነገር ያወራብኛል፡፡ አንተስ በዚህ የተነሳ ከሞት ስፍራ ብትደርስና ተዋርደህ ብትወድቅ ምንድንነው ጥቅምህ፡፡

አሁንም በአባትህ በወዳጅህ በአጼ ምኒሊክና በእናትህ በእቴጌ ጣይቱ በአባትህም በራስ ወሌ ዐፅም ብለህ እንደዚሁ እንደ ላክሁብህ ቃል ወረኢሉ ድረስ ቀደም ብለህ ገስግሰህ እንድትመጣ ይሁን፡፡

ነገር ግን ለእጄ እፈራለሁ እታሰራለሁ እንዳትል ከዚህ ቀደም እንደ ላክሁብህ እምነትህን በእኔ ላይ አድርግ፡፡ ዋስህም ጠበቃህም እኔው ነኝና በመድኃኔ ዓለም በወዳጅህ በተሰቀለው ጌታ ብለህ እንድትመጣ ይሁን፡፡

ንግሥትም ለሚልኩት መልእክት ራስ ጉግሣ ቀጥተኛ መልስ አይሠጡም ነበር፡፡ የካቲት 30 ቀን 1922 ዓ.ም ግርማዊት ንግሥት “…እንደዚህ እየተጨነቅሁ በየጊዜው ስልክብህ እንግዲህ እንደዚህ እንዳለፈው ያለ ያልተቆረጠ ነገር አትላክብኝ፡፡ እኔም ከአባቴ አልጋ ያንተ ነገር አይብስብኝም” ብለው ቁርጡን ተናገሩ፡፡ራስ ጉግሣ ወሌ ከንግሥት ምልጃና ተማጽኖ ይልቅ ለጦርነት ይዘጋጁ ጀመር፡፡

መጋቢት 22 ቀን 1922 ዓ.ም ሰኞ ማለዳ በራስ ጉግሣ ወሌና በደጃዝማች ሙሉጌታ ይገዙ በሚመራው የንጉሥ ተፈሪ መኮንን ሠራዊት መካከል ዋድላ ውስጥ አንቺም በሚባል ሜዳ ጦርነት ተካሄደ፡፡ የራስ ጉግሣ ጦር 10 ሺ ሲደርስ በደጃዝማች ሙሉጌታም በኩል 20 ሺ ነበር ይባላል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የጦር አውሮፕላን በጦርነት ላይ ዋለ፡፡ሁለት ፖቴዝ አውሮፕላኖች ቦምብ በመጣልና መትረየስ በመተኮስ ለመንግሥት ጦር እርዳታ አደረጉ፡፡ የራስ ጉግሣ ጦር አይቶና ሰምቶ በማያውቀው የሰማይ ጦር (የአውሮፕላኖች ግርማ) ደንግጦና ተሸብሮ ተበተነ፡፡ ራስ ጉግሣም በጦርነቱ በጥይት ተመትተው በ53 ዓመታቸው ሞቱ፡፡ ጦርነቱም በመንግሥት ጦር ድል አድራጊነት ተጠናቀቀ፡፡

ከአንቺም ጦርነት ጋር ተያይዞ የሚነሳው የደጃዝማች አያሌው ብሩ ታሪክ ነው፡፡ ደጃዝማቹ ከእቴጌ ጣይቱና ከዐፄ ምንሊክ ባለ ሥልጣናት ጋር ዝምድና ያላቸው በበርካታ ጦር ሜዳ የተሳተፉ ጀግና ነበሩ፡፡ ከራስ ጉግሣ ጋር በተደረገው ጦርነት ከንጉሥ ተፈሪ ወገን ሆነው ተሰልፈዋል፡፡ ንጉሥ ተፈሪ፣ ጦርነቱን በጀግንነት ተዋግተው ወሮታ ከዋሉ የራስ ማዕረግ እንደሚሰጧቸው ቃል ገብተውላቸው እንደ ነበር ይነገራል፡፡ ደጃዝማች አያሌው በተሰለፉበት ግንባር በጀግንነት ቢዋጉም የንጉሥ ተፈሪ ቃል ግን ተሰበረ፡፡ ከዚያ በኋላ በስሜን በጌ ምድር እንዲህ ተብሎ ተገጠመ፣ ተዘፈነም፡፡ አያሌዉ ሞኙ፣
ሰዉ አማኙ፣ሰው አማኙ፣
ዛሬ ድረስም አፍላ ሁኖ ይዘፈናል፡፡

ንግሥት ዘውዲቱ ጦርነቱ ሲካሄድ ሕመም ላይ ነበሩ፡፡ የራስ ጉግሣን ሞት አልሰሙም ይባላል፡፡ ጦርነት የማይወዱት ሰላማዊዋ፣ ጭምትዋና መንፈሳዊዋ ንግሥት የሚወዷቸውን ራስ ጉግሣን ወደ ጦርነት እንዳይገቡ ማድረግ አልተቻላቸውም፡፡ በመጠናቀቅ ላይ የነበረውን የአባታቸውን ሐውልት ሳይመርቁ፣ መጋቢት 24 ቀን 1922 ዓ.ም በ8 ሰዓት አረፉ፡፡ ቀብራቸው አዲስ አበባ በታዕካ ነገሥት በዓታ ቤተ ክርስቲያን በታላቅ ክብር ተፈጽሟል፡፡ ለ13 ዓመት ከስድስት ወራት የኢትዮጵያ ንግሥተ ነገሥታት ሆነዋል፡፡ በዘመነ መንግሥታቸው መጀመሪያ በ1909 ከተደረገው የሰገሌ ጦርነት እና በስልጣን መጨረሻቸው በ1922 ከተደረገው የአንቺም ጦርነት በስተቀር ሰላም ነበር፡፡

በዘመናዊ ኢትዮጵያ ታሪክ (ከአጼ ቴዎድሮስ ጀምሮ) በኢትዮጵያ የነገስታት ታሪክ በይፋና በክብር ለመቀበር የበቁ የመጀመሪያዋ መሪ ንግስት ዘውዲቱ ናቸው፡፡ ዓለም አቀፍ እውቅና ያገኙ የመጀመሪያዋ ሴት አፍሪካዊ መሪም ነበሩ፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክም ለመጀመሪያ ጊዜ የጦር አውሮፕላን በጦርነት የዋለበት የአንቺም ጦርነት ንግሥትን አስጨንቆ፣ ባለቤታቸውን በሞት ነጥቆ፣ የንግሥትን ሞት አፋጥኖ፣ ንጉሥ ተፈሪን “ሞሐ አንበሳ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ” አሰኝቶ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት አስደረገ፡፡
ለአያሌዉ ሞኙ፣
ሰዉ አማኙ፣ሰው አማኙ፣ ዘፈንም መነሻ ሆነ፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!

ይህን ጽሁፍ ለማዘጋጀት፣
Bahru Zewde, A History of Modern Ethiopian History (1848-1974),
መርስኄ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ, “የሐያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ”, ሦስተኛ እትም
መጽሐፍት በምንጭነት ተጠቅሜያለሁ፡፡

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close