Connect with us

Ethiopia

የአንጋፋው ፖለቲከኛ ተማጽኖ

Published

on

የአንጋፋው ፖለቲከኛ ተማጽኖ | ያሬድ ጥበቡ (የአዴፓ የቀድሞ ታጋይ)

የአንጋፋው ፖለቲከኛ ተማጽኖ
ያሬድ ጥበቡ (የአዴፓ የቀድሞ ታጋይ)

የአቶ ለማ መገርሳን ሙሉ ቃል እነሆ! ከታች ከተያያዘው ፋይል አንብቡት ። ዶክተር አብርሃም ዓለሙን ለትርጉሙ እጅግ እናመሰግናለን ። የአቶ ለማ መገርሳን ሙሉ ቃል አንብቤ የተሰማኝ እንደሚከተለው ነው ። ይህ የፖለቲካ ዲስኩር አይደለም፣ የአንድ አቅመቢስ ዜጋ ተማፅኖ ነው።

ምን ቢተማመኑ ይሆን አቶ ለማ ዐይናቸውን ጨፍነው በድፍረት ሊዋሹን የጨከኑት? ከዚህ በኋላ እንዴት አድርገው ዐይናችንን ሊያዩ ይሆን? በአደባባይ የተናገሩትን እንዲህ ከሸመጠጡ፣ ከአደባባይ የተደበቀውን እንዴት ሊያደርጉት ይሆን? እንዴትስ ከዚህ በኋላ አምነናቸው “የለውጡ አራማጅና መሪዎች” ብለን ልንቀበላቸው እንችላለን?

ዶክተር አቢይስ ቢሆኑ፣ በምን ስሌት ነው እርሳቸው ባሉበት የተነገረውን “ከአውድ ውጪ ተወስዶብኝ ነው፣ እኔ እደዚያ አላልኩም” ሲሉ፣ “ለማ በህዝብ መድረክ የተናገርከውን ዋሽተህማ እንዴት በሥልጣን መቀጠል ትችላለህ?” ብለው፣ ሥራቸውን እንዲለቁ ወይም እንደገና ቀርበው የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ እንዲጠይቁ አለማድረጋቸው የሚያስተዛዝብ ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያችን ምን እጅ ላይ ወደቀች ወይም ጣልናት ብለን እንድንቆጭና እንድናለቅስ የሚያደርግ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአንድ ዓመት የሥልጣን ዘመናቸውን ለማክበር በነገው ዕለት በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ይገኙ ይሆናል። ነገም ተጨማሪ ውሸት ሊያሰሙን ቆርጠዋል፣ ወይስ ለተደረገው አሳፋሪ ነገር መውጫ መንገድ ይፈልጉለት ይሆን? የኢትዮጵያ ህዝብ ጨዋ ነው፣ መሃሪ ነው፣ አርቆ አሳቢ ነው። የማርያም መንገድ ለመስጠት ፈቃደኛ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብሮ የሚያኖር መላ ከመፈለግ ግን፣ በበለጠ ውሸትና በፕሮፓጋንዳ ጭነት ከተማመኑ የሽግግሩ ሥርአተ ቀብር ተፈፀመ ማለት ነው።

ለምን ሽግግሩን በስግብግብ ግቦች እንፈትነዋለን? ለምን አደብ መግዛት አይቻለንም? ለምን በተሳከሩ ጠባብ ብሄርተኛ ፍላጎቶች ሽግግሩን እንጠልፈዋለን? የኦሮሞ ህዝብ የታገለው ለእኩልነት እንጂ ለልዩ ተጠቃሚነትና የበላይነት አይደለም። አሁን ሽግግሩን ዴሞክራሲያዊ በሆነ ተስፋ የማጠናቀቅ እድል በእጃችን እያለ፣ እንዴት ኢትዮጵያን ጠንቅቀው ለማያውቁ ጥቂት አክራሪ ብሄርተኞች በመንበርከክ የኢትዮጵያ ህዝብ የጣለባችሁን አደራ መወጣት ያቅታችኋል? ከፀጋዬ አራርሳና ጃዋር ይልቅ ኢትዮጵያን ብትመርጡ አይሻላችሁምን?

ዶክተር አቢይ በነገው እለት በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ፊት ቆመህ ለመናገር አቅድ ከሌለህም፣ የአንደኛ ዓመት የሲመት በዓልህን ምክንያት አድርገህ ከገባችሁበት የሃሰት መረብ በጣጥሶ የሚያወጣ መላ ፈልግ። ህዝብህን ከህሊናህ በሚፈልቅ እውነት ለማናገር ቁረጥ ። ተሳስተን ነበር፣ ለመታረም ወስነናል፣ ሆኖም ደፍረን መናገር ያቃተን የሃገሪቱ ሁኔታ አስጨንቆን ነው በል። አንድ የሆነ መውጫ መንገድ ፈልግ ። መታረቂያ መላ ፍጠር ።

ምንም ይሁን ምን ግን እውነቱን ከመጋፈጥ ይልቅ፣ ለሃቅ የቆሙትን ወህኒ እየወረወርኩና እየገደልኩ መሄድ እችላለሁ ብለህ አታስብ። እንዲህ በደም አበላ የተዘፈቀ የኦሮሞ የበላይነት ዘመን እንዲመጣ አትስራ። ኦሮሞ ከቁመናው የሚመጥን ቦታ በኢትዮጵየ ውስጥ እስካገኘ ድረስ፣ የግድ ዛሬና አሁን የበላይ ካልሆንኩ ብሎ ያዙኝ ልቀቁኝ የሚል ህዝብ እንዳልሆነ እናውቃለን።

አንዳንድ በኢትዮጵያ ጥላቻ የተሞሉ “ጊዜው የኛ ነው” ባዮች የሆኑትን ኤሊቶቻችሁን ሳይሆን፣ የሰፊውን የኦሮሞ ህዝብ ልቦና አድምጡ። እባካችሁ ተለመኑ። የእብሪትና የማንአለብኝነት መንገድ ለወያኔም አልበጀው። ያ የውድቀት ጎዳና ነው። ከወደቁት ተማሩ ።

ለልጆቻችሁ ኩራትን እንጂ ሃፍረትን አታውርሱ። እባካችሁ! ይህ ልመናና ተማፅኖ እንጂ የፖለቲካ ዲስኩር አይደለም። አደገኛ ቁልቁለት ላይ ስትከንፉ እያየሁ ዝም ማለት ስላላስቻለኝ ነው እግራችሁ ሥር ተንበርክኬ የምለምናችሁ። ኮሌጅ እንደገባሁ ብወልድ ኖሮ ለማን የሚያህል ልጅ ይኖረኝ ነበር። ሁለታችሁንም ለመውለድ የሚያስችለኝ የዘመን እርቀት ላይ ነኝ። በስስት ዐይን በማየት ለሁለታችሁም ያለኝን ወደር የሌለው ፍቅር ለብዙ ወራት ስገልፅ ቆይቻለሁ። ቃላችሁን እወደዋለሁ። የመደመርና ይቅርታ መልእክታችሁም አድናቂ ነበርኩ። ሆኖም ከጥቂት ወራት ወዲህ በተግባራችሁ ወይም በዝምታችሁ አቆሰላችሁኝ። ከብጤዎቼ ጋር ሆነን ተነጋግረንና ተደራጅተን ሳይሆን ተነጣጥለንና ለየብቻ ቆመን ልንመክራችሁም ብንሞክር አንድ በመቶ ያበዱ ስላሉ አማኑኤል እናስገባቸዋለን ብላችሁ በአደባባይ ተናገራችሁ ። አዲስ አበባ ለዜግነት መብቱ ለመቆም መንቀሳቀስ ቢሞክር ጦርነት አወጃችሁ።

ሰሞኑን በየመድረኩ ላሰማችሁዋቸው ግማሽ እውነቶች፣ ሃሰቶችና፣ እብሪቶች መመለስ ቀላል ነበር። ሆኖም በበኩሌ ዝምታን መረጥኩ። የማርያም መንገድ ለመስጠት በማሰብ ነበር። ሆኖም ልባችሁ የተደፈነ ይመስላል። እባካችሁ የጥጋቡን መንገድ ተውት! አይጠቅማችሁም። እኛንም በስተርጅና እንቅልፍ አትንሱን! አቦ እንረፍበት! ሃሎ ይሰማል?

(ማስታወሻ፡-ይህ መጣጥፍ ከአቶ ያሬድ ጥበቡ ገጽ የተወሰደ ሲሆን የጹሑፉ ይዘት የሚወክለው የጸሐፊውን አቋም እንጂ የድሬቲዩብን አይደለም፡፡)

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close