Connect with us

Ethiopia

ታሪካዊው አጃና ሚካኤል፤

Published

on

ታሪካዊው አጃና ሚካኤል፤

ታሪካዊው አጃና ሚካኤል፤
አዲሱ አራት ሺ የሚይዘውን የዋሻ ውስጥ ውቅር ቤተ ክርስቲያን ገባሁ፡፡

ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ወደ ሰሜን ሸዋ ይዞን ተጉዞ ቆይታውን እያካፈለን ነው፡፡ ታሪካዊ በኾነው አጃና ሚካኤል የተሰራውንና ግዙፉን የዋሻ ውስጥ ውቅር ቤተ ክርስቶያን ጎበኘሁ ሲል የተመለከተውን እንዲህ ይተርክልናል፡፡ | ሄኖክ ስዩም በድሬቲዮብ

ቁልቁለቱን እየወረድሁ ነው፡፡ አጭር ቢሆንም ያንደረድራል፡፡ ወደ ታች ብንወርድም ከፍ ወደአለው ስፍራ እየሄድን ነው፡፡ እዚህ ይኽ ትውልድ አዲስ ራዕይ አይቶ አዲስ ታሪክ ሰርቷል፡፡ አጃና ሚካኤል ቤተክርስቲያን ታየኝ፡፡ ግዙፉ የሾላ ዛፍ የቤተክርስቲያኑን ጣሪያ በግማሽ ሸፈኖታል፡፡ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለም የተቀባው የቤተ ክርስቲያኑ ጣሪያ በድንብ ሲታየኝ የፏፏቴውን ድምጽ መስማት ጀመርሁ፡፡

ሰሜን ሸዋ ዞን ነኝ፡፡ ሞጃና ወደራ ወረዳ ሰላ ድንጋይ አቅራቢያ እገኛለሁ፡፡ እዚህ አካባቢ ጻድቃኔ ማርያም አለች፡፡ እኔ ወደ አጃና ሚካኤል እየወረድሁ ነው፡፡ ሸለቆው ስር በምትገኘው ትንሽ ሜዳ ይህ ታላቅ ስፍራ አርፏል፡፡ የፏፏቴው ድምጽ ጎልቶ መሰማት ጀመረ፡፡ ቀና ብዬ አየሁ ከግዙፉ ዐለት አናት የሚወርደው የአጃና ሚካኤል ጠበል ነበር፡፡ ይኽ ቀስተ ደመና የሚሰራው፡፡ በፈዋሽነቱ ስሙ የገነነው ጠበል ነው፡፡

አዲስ እየተሰራ የሚገኘው የዋሻ ውስጥ ውቅር ቤተ ክርስቲያን በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ተጎበኘ

ሸዋ ጻድቃኔ ማርያም አካባቢ በሚገኘው አጃና ሚካኤል አዲስ እየተሰራ የሚገኘው የዋሻ ውስጥ ውቅር ቤተ ክርስቲያን በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ተጎበኘ፡፡

ብዙ ሰው ነበር፡፡ በስተግራ ባለው ጠበል ለመግባት የተሰለፈው ሰው በርካታ ነው፡፡ በስተቀኝ ባለችዋ መግቢያ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ገባሁ፡፡ ሁለት ክብ ቤተ ክርስቲያኖች አጠገብ ላጠገብ አሉ፡፡ መጀመሪያ ያገኘኋት የማርያም ቤተ ክርስቲያን መሆኗን ነገሩኝ፡፡ ጣሪያዋ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለም ተቀብቷል፡፡ ነጭ ቀለም ነው የተቀባችው፡፡ በመጠኗ አነስ ያለች ናት፡፡ በሮቿ፣ መስኮቶቿና የበረንዳ ምሰሶዎቿ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለም አሸብርቀዋል፡፡

እልፍ ብሎ ትልቁ ቤተ ክርስቲያን አለ፡፡ አጃና ሚካኤል፤ በግንብ የተሰራ ድንቅ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ብዙ ሰው እመለከታለሁ፡፡ ብዙ ሰው ለጸበል የሚመጣበት ስፍራ ነው፡፡ ያረፈበት መልከዓ ምድር ውብና ማራኪ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያኑ ጀርባ በጋ የማይደርቀው ወንዝ ሲወርድ አየሁ፡፡

ግዙፉ የሾላው ዛፍ ጥላ አየሩን ጭምር ቅዝቅዝ አድርጎታል፡፡ የሾላው ፍሬ ሲረግፍ መሬት ሳይነካ ቀብ አድርገው የሚበሉት ሰዎች ፍጥነት አስደንቆኛል፡፡ የሾላው ፍሬ እንደ እምነት ይቆጠራል፡፡ መንፈሳዊ ትርጉም ስለሚሰጠው ብዙ ምዕመናን ምግብ በልተው አይበሉትም፡፡ በጸበሉ ስፍራ ሆነው የሚጮኹ ሰዎች ድምጽ ያለሁበት ድረስ ይሰማኛል፡፡ ኡኡታው ከገደሉ አናት የሚወርደውን የጸበሉን ድምጽ ውጦታል፡፡ አጃና ሚካኤል ልዩ ነው የሚባለው አንድም ጠበሉ መነሻው የት እንደሆነ አለመታወቁና በቀስተ ደመና መታጀቡ ነው፡፡

አንድ ስፍራ የተሰቀለውን ታፔላ ቆም ብዬ አነበብኩት በስፍራው ቆይታ ለሚያደርጉ ሰዎች መረጃ ይሰጣል፡፡ ድምጽን ከፍ አድርጎ መነጋገር እንደሌለብን ይነግረናል፡፡ ንጹህ ቅጥር ነው፡፡ አልኮል ጠጥቶ መግባት በጥብቅ ይከለከላል፡፡ ጥብቅ ሥርዓት እንዳለው ከማንበብም በላይ እያየሁ ነው፡፡

ካህናቱ ልብሰ ተክህኗቸውን ለብሰዋል፡፡ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ እየተጠበቁ ነው፡፡ ዛሬ ድንቅ የኾነው የዋሻ ውቅር ቤተ ክርስቲያን ይጎበኛል፡፡ ዋሻው ያለበትን ስፍራ አሻግሬ አየሁት፡፡ ግዙፍ የተራራ ዐለት ደጀን ኾኖ በግርማ ሞገስ ተኮፍሷል፡፡ በዚህ ትውልድ የተሰራውን ድንቅ ስራ ለመመልከት ልቤ ቋምጧል፡፡ አጃና ሚካኤል ነኝ፡፡ ጳጳሱ እንደደረሱ አብረን ወደ ውቅር ዋሻው እንጓዛለን፡፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** የተለያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዝኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close