Connect with us

Ethiopia

ኢህአዴግ ይጠገን ይሆን?  | በማዕረግ ጌታቸው

Published

on

ኢህአዴግ ይጠገን ይሆን?  | በማዕረግ ጌታቸው

ኢህአዴግ ይጠገን ይሆን?  | በማዕረግ ጌታቸው

ፎርቹን ጋዜጣ በቅርቡ ባወጣው ዘገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከህወሓት አመራሮች ጋር በመሀላቸው ያለውን ልዩነት ስለመፍታት መምከራቸውን ገልፆል፡፡ ይህ የሁለቱ ፓርቲዎች ውይይት በግንባሩ ውስጥ ያለውን ሽኩቻ ለማርገብ የጎላ ሚና እንደሚኖረው ይጠበቃል፡፡ ከኢህአዴግ ቤት በዚህ ሳምንት የተሰማው ወሬ ግን ከላይ ያነሳነው ብቻ አይደለም፡፡ በኦዲፒና አዴፓ መካካል አለመግባባት ተፍጥሯል የሚለው የማኅበራዊ ድረ-ገጾች ሀሜት ውሸት መሆኑን አዴፓ አስተውቋል፡፡ ደኢህዴንም ለውጡ ግቡን እንዲመታ ከመቼውም ጊዜ በላይ ቁርጠኛ መሆኑን ገልፆል፡፡ የእነዚህ ነገሮች ድምር ውጤት አንድ ጥያቄ እንድናነሳ ዕድል ይፈጥራል ፡፡ ኢህአዴግ ይጠገን ይሆን ? የሚል፡፡ የዚህ ሀሳብ መዳረሻ የግንባሩ እህት ድርጅቶች እንደሚሄዱበት መንገድ ይለያያል፡፡ ምላሹም አዎም፣ አይሆንም ይሆናል፡፡

ኢህአዴግ በአሁኑ ወቅት በውስጣዊም በውጫዊም ችግሮች የተተበተበ ፓርቲ መሆኑ የሚያከራክር አይደለም፡፡ ከህወሃት ውጭ ሁሉም የግንባሩ እህት ድርጅቶች በየክልላቸው ከባድ የሚባል ፍትጊያ ላያ ናቸው፡፡ አዴፓን የያዘችው መርከብ አማራ ክልል ላይ በአብን እየተናወጠች ነው፡፡ ኦዲፒም ከኦነግ ጋር ያለው አተካራ አልከሰመም፡፡ ደኢህአዴን በክልሉ ያለው የብሄርተኞ እንቅስቃሴ የስብሰባ አዳራሽ እንኳን ነፍጎታል፡፡ ከዚህ እውነት አንፃር በኢህአዴግ ጥላ ስር የተጠቃለሉ ድርጅቶች እንደቀደመው አብረው መስራት ካልቻሉ የአንዳቸው ውድቀት ለሌላው ውደቀት መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡

ከወቅታዊው የሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ቀጣዩ ምርጫ አንድ አውራ ፓርቲ በሰፊ ልዩነት የሚያሸንፍበት ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ይህ ደግሞ የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች በተበጣጠሰ መልክ የሚያገኙትን የምክር ቤት መቀመጫ ይዘው መደመር ካልቻሉ የፌደራል መንግስት የመመስረት ውጥናቸው በአጭር እንዲቀጭ ያደርጋል ፡፡ ይህ ደግሞ የኦዲፒ አልያም አዴፓ ኪሳራ የህወሓትም የደኢህዴንም ኪሳራ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ ከዚህ አንጻር የድርጅቱ ሊቀመንበር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ለሀገር ይበጃል የሚሉት የመደመር ፍለስፍና ከምንም በላይ ለሚመሩት ግንባር አስፈላጊ ሆኖ ይስተዋላል፡፡

ኢህአዴግ ውስጥ ያሉ ድርጅቶች አብሮ የመስራት ጉዳይ አትራፊ መሆኑ አያከራክርም፡፡ ይሁን እንጅ አብረው ሊዘልቁ የሚችሉት እንዴት ነው ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል ፡፡ግንባሩ ወደ ቀደመ አንድነቱ ለመመለስ ከምንም ነገር በላይ የጠራ ርዕዮተ- ዓለም ያስፈልገዋል ፡፡አሁን ከሚሰተዋልበት መዋለልም በፍጥነት ወጥቶ የጠራ መስመሩ ምን እንደሆነ በተግባር ሊያሳይ ይገባዋል፡፡ ድርጅቱ አሁንም ድረስ የአብዮታዊ ዴሞክራሲን መስመሩን በይፋ ባይቀይርም በተግባር የሚታየው ግን ከዚህ የማፈንገጥ ዝንባሌ ነው፡፡ እንደ ፕሮፌሰር እንድርያስ እሽቴ ያሉት ምሁራን እንደውም የዛሬው ኢህአዴግ ሌበራል ዴሞክራሲን እየተከተለ ያለ መሆኑን በበርካታ ማስረጃዎች ያረጋግጣሉ፡፡ ግዙፍ የመንግስት ድርጅቶችን ወደ ግል ማዞር ከሚለው አስተሳስብ ጀምሮ የዓለም ባንክን ምክር ሀሳብ በመስማት አዳዲስ የልማት ፕሮጀክቶችን ለጊዜው ማቋረጡም ለዚህ ዋቢ ሆኖ ይጠቀሳል፡፡ ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ ከሰሞኑን እንደገለጹት ደግሞ መንግስት የገብያ ጉድለት እሞላለሁ የሚል ስሌት ይዞ መጓዙ ችግር እንደፈጠረ ተናግረዋል፡፡ ይህ አሰተያየታቸው ደግሞ የድርጅቱ ሊቀመንበር የልማታዊ ዴሞክራሲ ምሰሶ ላይ ጥያቄ እንዳላቸው ያረጋግጣል፡፡ እነዚህን መሰል ንግግሮችና ተግባራትም ገዥው ፓርቲ አብዮታዊ ዴሞክራሲን ወረቀት ላይ እንደተወው ያሳያሉ፡፡

ይህ ደግሞ ድርጅቱ የቀድሞው አንድነቱን እንዳያረጋግጥ እክል ፈጥሮበታል፡፡ የህወሓት አመራሮች ግንባሩ አብዮታዊ ዴሞክራሲን መተው የለበትም የሚል አቋም የሚያራምዱ ሲሆን የለውጥ ኃይሎች የሚባሉት ወገኖች በአንጻሩ ለሌበራል አስተሳስብ ያደላሉ፡፡ በመሆኑም ኢህአዴግ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ከተፈለገ የመጀመሪያው ነገር ርዕዮተ ዓለማዊ ልዩነቱን መፍታት መሆን ይኖርበታል፡፡

ሁለተኛው ገዥው ፓርቲ የውስጥ አንድነቱን ለማጠናከር የሚረዳው ተግባር በህገ-መንግስቱ ላይ ያለው ምልከታ ነው ፡፡ የግንባሩ እህት ድርጅቶች እኩል የሚታገሉለት ህገ-መንገስት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ አሁን በስራ ላይ ያለው ህገ-መንግስት እንዳለ መቀጠል አለመቀጠሉ ላይ ከስምምነት መድረስ ሲችሉ ነው፡፡ በዚህ በኩል የአዴፓና የቀሪዎቹ ዕህት ድርጅቶች ልዩነት ዕልባት ሊሰጠው ይገባል፡፡

ሦስት አስርታትን በአብሮነት የተጓዘው ኢህአዴግ አንዱ የጥንካሬው ምስጢር በዴሞክራሲ ማዕከላዊነት ማመኑ እንደሆነ በተለያዩ ፅሀፍት ተደጋግሞ ተጠቅሷል፡፡ ይህ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ታዲያ በብዙዎች እንደሚተቸው ከላይ ወደታች የሚውርድ አምባገነናዊ አካሄድ ሳይሆን ለመሰራተዊ የድርጅቱ መርሆች መግዛት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ባለፉት ጥቂጥ ዓመታት ገዥው ፓርቲ የገጠመውን ውስጣዊ ቀውስ ለተመለከተ ሰውም ዴሞክራሲያዊ ማእከላዊነት ግንባሩ አብሮ እንዲቀጥል አንዱ ቁልፉ ነገር እንደሆነ ያረጋግጥልናል፡፡ በዚህ ምክንያትም ድርጅቱ አብሮ ለመዝለቅ ካሰበ በህገ-መንግስቱና በርዕዮተ-ዓለሙ ላይ ከሚያደርገው ስምምነት ባለፈ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ላይ ያለውን አቋም በተግባር ሊያረጋግጥ ይገባል ፡፡ እነዚህ ከላይ የተነሱ ሦስት ጉዳዮች ኢህአዴግ እንደ ኢህአዴግ ብቻ ሳይሆን አራቱ እህት ድርጅቶች በቀጣይነት በሀገሪቱ ፖለቲካ ላይ የሚኖራቸውን ሚና የመወሰን አቅም አላቸው፡፡

ከላይ የተመለከትናቸው ኢህአዴግ የገጠሙት ችግሮች የሚጠገኑ መሆናቸው አያከራክርም፡፡ ይሁን እንጅ እህት ድርጅቶቹ ውስጥ ያሉ አመራሮች ለዚህ ያላቸው ተነሳሽነት ወሳኝ፡፡ ከመቀራረብ ይልቅ መገፋፋትን ፣ከመነጋጋር ይለቅ መጠላላትን የሚያስበልጡ አመራሮችን መያዙም ከድርጅታዊ ችግሮቹ ይልቅ ግለሰባዊ አለመግባባቱ ትልቅ ፈተና እንዲሆንበት አድርጎታል፡፡ ስለሆነም ግንባሩ ወደ አንድነት መምጣት ከፈለገ ድርጅታቸውን ምሽግ አድርገው የሚታኮሱ አመራሮች ለፓርቲያቸው ጥቅም ወደ መታገል መምጣት አለባቸው፡፡ ያኔ ቢያንስ ኢህአዴግ በግማሽ ተጠግኖ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል፡፡ በመሰረታዊ ልዩነቶቹ ላይ ከመከርም የቀደመ አንድነቱን የመመለስ ዕድሉ ዝግ አይሆንም፡፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** የተለያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዝኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close