Connect with us

Ethiopia

ርሃቡን የሚቀሰቅሰው ሳለ እርዳታ የሚሰበስበው ሶሻል-ሚዲያ በስጋት የሚታየው ለምን ይሆን?

Published

on

ርሃቡን የሚቀሰቅሰው ሳለ እርዳታ የሚሰበስበው ሶሻል-ሚዲያ በስጋት የሚታየው ለምን ይሆን? | አሳዬ ደርቤ

ርሃቡን የሚቀሰቅሰው ሳለ እርዳታ የሚሰበስበው ሶሻል-ሚዲያ በስጋት የሚታየው ለምን ይሆን? | አሳዬ ደርቤ@DireTube

ለባለፉት ዓመታት አገራችን ላይ ሰፍኖ የነበረው ስርዓት ከውስጡ ሆነው የመልካም አስተዳደር ጥሰት እና የሙስና ድርጊት እየፈጸሙ ስርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥሉ አመራሮቹን በማስተካከል ፈንታ መረጃውንና ሚዲያውን ለማፈን የተቻለውን ያህል ሲባትል ነበር፡፡

የበሰበሰ ስርዓቱ በተንገዳገዴ ቁጥር ‹‹አገር ተንገዳገደች›› እያለ ሚዲያዎችን ሲዘጋና ጋዜጠኞችን ‹‹አሸባሪ›› በሚል ክስ ሲያስር ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሄን በማድረግ ችግሩን ማስቆም አልተቻለውም፡፡

የሚቃወሙትን ቻናሎችና ጋዜጣዎች ከምድሩና ከአየሩ ላይ ሲያጠፋቸው ሶሻል ሚዲያው ብቸኛ የመረጃ ምንጭ ሆኖ አረፈ፡፡ በድርጅቶች እጅ የነበረውም መረጃ በግለሰቦች ቁጥጥር ስር ዋለ፡፡

የፈሪ መዳፉን ሶሻል ሚዲያው ላይ መሳረፍ ሲጀምር ደግሞ በትክክለኛ ማንነታቸው መረጃ ሲያሰራጩ የነበሩ ዜጎች የሃሰት አካውንት እያወጡ ስርዓቱን መቃወማቸውን ቀጠሉ፡፡ የህጉ መጠንከርም የህገ-ወጦችን ቁጥር ከመጨመር ባለፈ ፋይዳ ሳይኖረው ቀረና የመቀሌው ኢህአዴግ በዝረራ ሊሸነፍ ቻለ፡፡

ታዲያ ለዚህ ድል መምጣት ከእነ ኢሳት በላይ የETV አስተዋፆ የጎላ ነበር፡፡ እነ አዲስ ዘመን ጋዜጣም ከሶሻል ሚዲያው በላይ ለስርዓቱ መሸነፍ አበርክቶ ነበራቸው፡፡

ምክንያቱም ሶሻል ሚዲያው የስርዓቱን ህጸጾች እየዘረዘረ መንግስት ችግሮቹን ያስተካክል ዘንዳ እድሉን ሲፈጥርለት… እነ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ግን በትልልቅ ጥፋቶቹ ፈንታ ትናንሽ ልማቶቹን እያንቆለጳጰሱ ወደ ገደሉ ሲገፉት ነበር፡፡

የሚቃወሙት የቴሌቪዥን ቻናሎች ድክመቶቹን እና ብልሹ አመራሮቹን እየዘረዘሩ የእርማት እርምጃ ይወስድ ዘንድ ሲጠቁሙት…. እነ ኢቲቪ ግን በገዥው ፓርቲ የተንገፈገፈውን ብዙሐን ህዝብ ችላ ብለው ‹‹አንዳንድ የእንትና ነዋሪዎችን›› በማነጋገር ጥንካሬውንና ተወዳጁነቱን እየዘበዘቡ ስርዓቱን ወደ አሮንቃ ሲከቱት ነበር፡፡

ይሄንን እውነታ ያልተረዳው አሮጌው ኢህአዴግ ግን… ከራሱ ሚዲያዎች ከሚዘገብ አድናቆትና ሙገሳ ውጭ ምንም አይነት መረጃ መስማት የማይወድ ነበርና… የሚቃወሙትን ቻናሎች በበርካታ ሚሊዮን ብር ከአየር ላይ ማውረዱ አልበቃው ብሎ…. ከቤት ጣሪያችን ላይ የተሰቀሉ ዲሾችን በመንቀል ላይ እንዳለ ወንበሩን ተነጥቆ ስርዓተ-ቀብሩ ሊፈጸም ቻለ፡፡

ከዚህም ጋር ተያይዞ የመናገር ነጻነት በመምጣቱ በሃሰት አካውንት መንግስትን ሲነቅፉ የነበሩ ዜጎች በትክክለኛ ማንነታቸው ተገልጸው ከራሳቸው ፎቶ በተጨማሪ የዶክተር አቢይን እና የቲም ለማን ፎቶ ሲለጥፉ ሰነበቱ፡፡ የህውሓት አዝማሪዎች የነበሩ ሚዲያዎች ደግሞ ሲያወድሱት የነበረውን ስርዓት ሥም የሚያጠለሽ ዶክመንታሪ አዘጋጆች ሆነው ተከሰቱ፡፡

ተዘግተው የነበሩ ጋዜጦች፣ ታፍነው የኖሩ የቴሌቪዥን ቻናሎች፣ ተቃዋሚ የተባሉ ፓርቲዎች፣ አሸባሪ ተብለው የተፈረጁ ድርጅቶችና ግለሰቦች ሁሉ የለውጡ ደጋፊ ሆኑ፡፡ ከዚህ ባለፈም ሶሻል-ሚዲያው ላይ መንግስትን ማወደስ እንጂ አሉታዊ ሃሳብ ማንጸባረቅ ክልክል ሆነና የለውጡን መሪዎች ለመተቸት የሚሞክሩ አክቲቪስቶች በስድብ ይጥረገረጉ ጀመር፡፡

ታዲያ ይሄ ሁኔታ ሊከሰት የቻለው ሥልጣን ላይ የወጡት ሰዎች መልካም ሆነው መገኘት እንጂ የህዝቡ ወረተኝነት አልነበረም፡፡ ከአፋቸው የሚወጣው ንግግር፣ ምድር ላይ የሚታየው ተግባር ሁሉ የሚያስመሰግን ስለነበረ ነው፡፡

በዚህም መሰረት አሁን ወዳለንበት ጊዜ ስንመጣ በአዝማሪነታቸው የሚታወቁት ሚዲያዎች ‹‹የስርዓቱን ድክመት አንመለከትም›› ብለው ውዳሴያቸውን ተያይዘውታል፡፡ ለእነሱ ‹‹የሚዲያ ነጻነት›› ማለት ያለፈውን እንጂ ወንበር ላይ ያለውን መንግስት መተቸት ባለመሆኑ ትናንትን እየከሰሱ ዛሬን እያወደሱ መንጎዳቸውን ቀጥለዋል፡፡

እንደ ሁኔታውና እንደ መረጃው መልኩን የሚለዋውጠው ሶሻል-ሚዲያችን ግን ከመሪዎቹ ንግግርና ተግባር መሃከል ጥሩ ነገር ሲገኝ አድናቆቱን፣ የሆነ ሸፍጥ ሲፈጸም ደግሞ ትችቱን እየሰጠ ይገኛል፡፡

አሁን አሁን ታዲያ ከአድናቆቱ ይልቅ የትችቱ መጠን እየጎላ ሲመጣ አዲሱ ኢህአዴግ ወደ ኋላ ተመልሶ የአሮጌውን መንግስት አስተሳሰብ ይዞ በመመለስ ‹‹ፌስቡክ አገር እያፈረሰ ነው›› በሚል ሶሻል ሚዲያውን መክሰስ ጀምሯል፡፡

በበኩሌ ግን በዚህ ሃሳብ በፍጹም አልስማማም፡፡ እንደውም ሶሻል ሚዲያው አገር ሊያፈርስ ቀርቶ ለውጡንም ሆነ አገራችንን እየጠበቀ ነው የሚል አቋም አለኝ፡፡

በአገር ወዳድ ተብሎ በሙሉ ድጋፍ ወደ ስልጣን የመጣው መንግስት በአንዳንድ ወገንተኛ ሐይሎችና ሐሳቦች በሚጠለፍበት ጊዜ የሶሻል ሚዲያው ጩኸት ባይታደገው ኖሮ ከዚህ የከፋ አሮንቃ ውስጥ ሊዘፈቅ እንደሚችል ግልጽ ነው፡፡

ላለፉት ወራቶች በመንግስት ድክመትና በመንጋ ጥቃት አገራችን ላይ ብዙ አስቀያሚ ክስተቶች ታይተዋል፡፡ ለማስረጃም ያህል በርካታ ዜጎች ከሚኖሩበት አካባቢ ሲፈናቀሉ… ቤታቸው ፈርሶ ጎዳና ላይ ሲጣሉ… የሚበሉት አህል አጥተው የወገን ያለህ ሲሉ… በአዲስ አበባ የባለቤትነት ጉዳይ ላይ ትርምስ ሲፈጠር… በርካታ ባንኮች ሲዘረፉ….. አስተውለናል፡፡

ሆኖም ግን በሶሻል ሚዲያ የዜጎች ቤት እንዳይፈርስ እንጂ እንዲፈርስ ትዕዛዝ አልተላለፈም፡፡ እንደውም ‹‹ህገ-ወጥ ቤቶች እየፈረሱ ነው›› የሚል መረጃ ሲወጣ ፌስቡክ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ ባይሰማና ጠቅላይ-ሚኒስቴራችንም ባይሰሙ ኖሮ የሚፈርሰው የቤት ቁጥር ከፍተኛ ይሆን ነበር፡፡

አገራችን ላይ አንድ ሚሊዮን ህዝብ በርሃብ ሲጠቃም ሶሻል-ሚዲያው እርዳታ ለማሰባሰብና ለመለገስ አስቻለ እንጂ ርሃቡን አላመጣውም፡፡ እንደውም ይሄ መረጃ ፌስቡክ ላይ ባይለቀቅ… የክልሉም ሆነ የፌደራል መንግስቱ ትኩረት ሲዳማ ላይ በሆነበት ሁኔታ ጌድዮ ላይ በርካታ ዜጎች በርሃብ ያልቁ ነበር፡፡

በተመሳሳይ መልኩ ለውጡን የሚቀለብሱና አገር የሚያተራምሱ በርካታ ድርጊቶች ያስተናገድን ቢሆንም የሶሻል ሚዲያው ተሳትፎ ከማገዝ ይልቅ በማውገዝ ላይ የተመሰረተ እንደነበር ግልጽ ነው፡፡ ይሄን ስል ታዲያ በሶሻል ሚዲያው ላይ ምንም አይነት አፍራሽ ሃሳቦች አይንጸባረቁም እያልኩ አይደለም፡፡ እንዲህ አይነት እኩይ አስተሳሰብ ሶሻል ሚዲያው ላይ ቀርቶ ማስ-ሚዲያዎችም ላይ ሞልቷል፡፡

ከዚህ ውጭ ግን ምድሩ ቆሽሾ ሳለ ሳይበሩ ንጹህ ሊሆን አይችልም፡፡ መረጃው እድፍ ወርሶት ሳለ ሚዲያው ጠኋራ ሊሆን አይችልም፡፡ ከገዥው ፓርቲ አንስቶ እስከ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ድረስ በዘር ተደራጅተው እየተናከሱ ባሉበት ሁኔታ ሶሻል ሚዲያው ስለ አገራዊ አንድነት ሊያቀነቅን አይችልም፡፡

ስለሆነም መንግስታችን ይሄንን እውነታ ተገንዝቦ ከሚዲያው ይልቅ ራሱን ቢገመግም መልካም ይመስለኛል፡፡ ‹ለተወሰኑ ወራቶች የኢህአዴግ ፎቶ አልበም በመሆን ያገለገለው ፌስቡክ ‹‹ለምን ስጋቴ ሊሆን ቻለ?›› ብሎ ራሱን መጠየቅ አለበት፡፡

መንግስት ችግሮቹን ገምግሞ የህዝቦችን እኩልነትና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስራዎችን መስራት ሲጀምር መረጃውም ሆነ ሚዲያው ዜጎችን የሚያግባባ ይሆናል፡፡ የመከፋፈል ሁኔታ የሚታይበት ኢህአዴግ ራሱን አጥርቶ ወደ አንድነት ሲመጣ ኢንተርኔቱም ላይ ሆነ መሬቱ ላይ ያለው ህዝብ ወደ አንድ መሆን ይጀምራል፡፡

ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ግን…. ቤታችንን፣ አገራችንን፣ አንድነታችንና ሰላማችንን የሚያፈራርሱ ተግባራት እየፈጸሙ ‹‹አገር አፍራሽ›› በሚል ሰበብ ሶሻል ሚዲያውን መክሰስ ‹‹አህያውን ፈርቶ ዳውላውን›› እንደሚባለው ነው፡፡ ‹‹ያመንኩበትንና የመሰለኝን ተግባር ስፈጽም እንደ አዝማሪዎቹ ሚዲያዎች አወድሱኝ እንጂ እንቅፋት አትሁኑብኝ›› እንደማለት የሚቆጠር ነው፡፡

ስለሆነም በሰፊ ተቀባይነት ወደ ሥልጣን የመጣው ‹‹አዲሱ ኢህአዴግ›› ሚዲያንና መረጃን በአዋጅ ማፈኑ ለህውሓትም እንዳልበጀ ተረድቶ.. እንደ መላዕክት ምልዑነቱን ከሚነግሩት አዝማሪ ሚዲያዎች ፈንታ… እንደ መንግስት እየተቸ ህጸጾቹን ከሚነግረው ሶሻል-ሚዲያ ላይ ችግሮቹን እየለቀመ ራሱን ቢያስተካክል ሁሉም ነገር ወደ ትክክለኛ መስመሩ መምጣቱ አይቀርም፡፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** የተለያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዝኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close