Connect with us

Entertainment

ቴዲ አፍሮ እንደነብይ ሙዚቃው እንደትንቢት

Published

on

ቴዲ አፍሮ እንደነብይ ሙዚቃው እንደትንቢት

ቴዲ አፍሮ እንደነብይ ሙዚቃው እንደትንቢት፤

አምጡት ቆርጣችሁ ከሹሩባው ላይ፤
መጥቷል ሹሩባው እንዳንለያይ፤

ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም የኢትዮጵያ መንግሥት ትናንት ከእንግሊዙ የጦር ሙዚየም የተቀበለውን የዳግማዊ ቴዎድሮስ ሹሩባ ጸጉር ምክንያት አድርጎ ታዋቂው ድምጻዊ ቴዲ አፍሮ እንደ ነብይ ሙዚቃው እንደትንቢት ቀድመው ነግረውን ነበር ሲል እንዲህ ይተርከዋል፡፡ | ሄኖክ ስዩም በድሬ ቲዮብ

መይሳው ቴዎድሮስ የተባለው ከዚህ ስም ጋር የተቆራኘ ተስፋን ኢትዮጵያውያን ሙጥኝ ስላሉ ነበር፤ ይህንን ስም ይዞ የሚመጣው ንጉሥ ሰላም የሚያሰፍን ሀገር አንድ የሚያደርግ ተብሎ አስቀድሞ ተተንብዮለታል፡፡ ያ ትንቢት በእሱ እውን ይኾን ዘንድ ስሙን ስሜን ተናገረ፤ እንደ ቀዳማዊ ቴዎድሮስ ባለ ራዕይ ነበር፤ ለሀገሩ ብዙ ተመኝቶ ነበር፡፡ ዛሬም ድረስ ኢትዮጵያ ያልተሳካላትን በሥርዓት የመመራት ምኞት እውን አደርግ ብሎ ተነሳ፡፡ የሚዘርፍ ወታደር ተጠይፎ ከሚዘርፍ መሳፍንት ጋር እዋጋለሁ ብሎ ቆላ ደጋ ተንከራተተ፡፡ መጨረሻ ራዕዩን ባልተሸከመ ትውልድ መካከል የተነሳው መሪ በራዕዩ ምክንያት መስዕዋት ኾነ፡፡

ከጥቂት ዓመት በፊት ሁሉም ዝም ባለበት ወቅት ድምጻዊው ሹሩባውን አለ፡፡ ጥያቄው አንድ የመኾን ምኞት ነበር፡፡ ድምጻዊውም እንደ ንጉሡ ያለ ምኞት ነበረው፡፡ ድምጻዊውም እንደ ንጉሡ የሙዚቃ ንጉሥ ነበር፡፡ ድምጻዊውም እንደ ንጉሡ ስሙ ቴዎድሮስ ነበር፡፡ ጥበብ የዕለት ጉርስ ምክንያት በኾነችበት ዘመን ስለ ትውልድ ግድ የሚለው ከያኒ ነበር፡፡ ታሪክ ራሱን ደገመ፡፡

ቴዎድሮስ ካሳሁን እንደ ነብይ ብዙ ተንብዮዋል፡፡ ብዙ ደርሷል፡፡ ዝኆኖችን ኮንኖ መገናኘትን ሰብኮ መለያየትን ተጠይፎ ጣናና ቀይ ባህርን ቀላቅሏል፡፡ ዘጌና ዳህላክን ከናፍቆት ፈውሷል፡፡ እንዲህ ባሉ ትንቢቶቹ ከያኒውን እንደ ነብይ አየዋለሁ፡፡ ያየውን ቀድሞ ነግሮናል፡፡ ቀድሞ የነገረን ቆይቶ እውን ኾኗል፡፡

እናም ምንም ባልነበረበት ሰዓት መይሳውን ከፍ አድርጎ ተጣራ፡፡ ጎንደርን የቴዎድሮስ ሀገር ሲል የቴዎድሮስ ሀገር መሆን የአንዲት ኢትዮጵያ ዋልታና ማገርነት መሆኑን ተናገረ፡፡ ይሄንን ሲያዜም ህመም ነበረው፡፡ “እህ” ይል ነበረ፡፡ መንገሽገሽ ነበረው፡፡ “ኽ….ረ…ረ…ረ” ይል ነበር፡፡

የመበተን ስጋት፣ የመለያየት ጠኔ፣ የልዩነት ናፍቆት፣ የግለኝነት መገንገንን ተጠየፈው፡፡ አንድ ማድረግን ሲሻ  “አምጡት ቆርጣችሁ ከሹሩባው ላይ ኪዳን እንሰር እንዳንለያይ” አለ፡፡ በዚህ ጊዜ የመቅደላን ቅርሶች ስለማስመለስ ለዘመናት የደከመችው ኢትዮጵያ የሰጧትን ለመቀበል ተዘጋጀች እንጂ ሹሩባውን ይዛ ስለመምጣት አልተሰናዳችም፡፡ ሙዚቃው እንደትንቢት ኾኖ ደረሰ፡፡ ኪዳን የምናስርበትን ሹሩባ ከእንግሊዝ ጦር ሙዚየም በክብር ተቀብለናል፡፡

ሀገር እንዳትዋረድ የሞቱ አባቶች ያቆዩዋት ሀገር ናት፡፡ በክብር ከመያዝ ይልቅ የሀገር ክብር የሚበልጥባቸው በክብር የሚሞቱ ጀግኖች ናቸው፡፡ ናፒር ቃል ገብቶ ነበር፡፡ ንግሥቴ በክብር ልትይዝዎት ዝግጁ ናት ብሎ ነበር፡፡ ሀገርን የምርኮኛ ንጉሥ ምድር አድርጎ ራስን በክብር ማስያዝ የአባቶቻችን ግብ አይደለም፡፡ እናም ሞተ፡፡ ገደሉን እንዳይሉ ግራ ቢገባቸው እንዲል ሀገርኛ ቅኔው እጅ ከምን ቢባሉ ሹሩባውም ክብር ነው ብለው ጸጉር ይዘው ሄዱ፡፡ እንግሊዝ ሙዚየም በክብር ተቀምጦ ኖረ፡፡ እንደ ድምጻዊው ቃል በክብር ሊመጣ ነው፡፡

ድምጻዊው ቴዎድሮስ ምኞታችንን አይቶልናል፡፡ ያየልንን ምንም ባልነበረበት ነግሮናል፡፡ ሲነግረን ደመና አይቶ ይዘንባል አላለንም፡፡ ይልቁንስ በሚያስፈራው ጨለማ ውስጥ ሆኖ ከሹሩባው ቆርጠን ኪዳን ስለማሰርና ስለ አለመለያየት ነገረን፡፡ አንድም እንደ ከያኒ ነገን ያየ ነብይ ነው፡፡ የከያኒው ስራም ትናንት ሆኖ ዛሬን የነገረን ትንቢት ነው፡፡

የቀረን ሹሩባውን መቀበል ነው፡፡ የቀረን በኪዳኑ አንድ መኾን ነው፡፡ የቀረን መለያየትን ድል መንሳት ነው፡፡ ተለያይተን ሞክረነዋል፡፡ መለያየት እስከ ህንድ የምትገዛውን ሀገር ባህር አልባ የየብስ ላይ አምባ አድርጓታል፡፡ መለያየት የካህኑን ዩሐንስ ሀገር የአፍሪካ የድህነት ምልክት አድርጓታል፡፡ መለያየትን ብዙ ርቀት ሄደን አይተንዋል፡፡ አንድ በኾንበት የታሪካችን ምዕራፍ ዛሬም ድረስ የምንኮራበት ክብር ተመዝግቧል፡፡ አሁንም ኪዳን እንሰር እንዳንለያይ፤

★ የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ

★ ኢትዮ ጵያን የተመለከቱ የተለያዩ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዘኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close