Connect with us

Ethiopia

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአወዛጋቢው የሊዝ አዋጅ ማሻሻያ ላይ ተወያየ

Published

on

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአወዛጋቢው የሊዝ አዋጅ ማሻሻያ ላይ ተወያየ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የካቲት 10 ቀን 2011 ዓ.ም የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ የወጣው አዋጅ ቁጥር 721/2004 ማሻሻያ የመጨረሻ ረቂቅ ሰነድ ላይ ውይይት ማካሄዱን ከከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የደረሰን ዜና ጠቆመ፡፡ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ይፈታል ተብለው የሚታሰበው ሊዝ አዋጅ 721/2004 ማሻሻያ ሰነድ አሁን በሥራ ላይ ባለው ህግ ያጋጠሙ የሕግ ክፍተቶችን ለማስተካከልና ሌሎች የሊዝ ሥርዓቱን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የሚችሉ አስፋላጊ ነገሮችን ያካተተ ሕግ ነው ተብሏል፡፡ የሊዝ አዋጁ የሀገሪቱ የዕድገት ደረጃ ባገናዘበ መልኩ ቀጣይነት ያለው ልማትና ለማረጋገጥና ለኪራይ ሰብሳቢነት የሚያጋልጡ ክፍተቶችን ከመዝጋት አንጻር እንዲሁም የህብረተሰቡን ፍትሃዊ የሐብት ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ አኳያ የተሸሻለው የሊዝ አዋጅ ወሣኝ ነው ተብሏል፡፡

አዋጅ ቁጥር 721/2004 የሊዝ አዋጅ ድንጋጌዎች በዝርዝር ሲፈተሹ በርካታ የአፈጻጸም ክፍተቶች ተስተውለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር አዋጁ ያልመለሳቸው ጉዳዮች ጎልተው ወጥተዋል ሲል ሪፖርተር ጋዜጣ በአንድ ወቅት ዘግቧል፡፡

ይሻሻሉ ተብለው ከሚጠበቁት መካከል ልዩ አገራዊ ፋይዳ ላላቸው ፕሮጀክቶች መሬት የሚቀርብበት መንገድ፣ የግል ይዞታና የመንግሥት ቤት በአንድ ግቢ ውስጥ መኖራቸው የፈጠረው ችግርና የማስፋፊያ መሬት ጥያቄዎች መስተናገድ አለመቻላቸው ይገኙበታል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ሥሪት ባለሙያዎች የሊዝ አዋጁ፣ ለማስፈጸም ከወጡ መመርያዎችና ደንቦች ጋር የሚቃረን በመሆኑ የትልልቅ ፕሮጀክቶችን የመሬት ጥያቄ ለማስተናገድ እንደተቸገሩ ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ የፀረ ሙስና ኮሚሽንም ሕግጋቱ መጣጣም እንዳለባቸው ለመንግሥት ሐሳብ አቅርቧል፡፡

የሊዝ አዋጁ አገራዊ ፋይዳ ያላቸው ፕሮጀክቶች መስተንግዶ መመርያ ቁጥር 15/2005፣ የከተማ መሬት ሊዝ ደንብ 2004 ዓ.ም. እና የሊዝ አዋጅ 721/2004 ዓ.ም. እንደሚቃረን የሚከራከሩ አሉ፡፡

የፀረ ሙስና ኮሚሽን የሕግጋቶቹን ተቃርኖ በሚመለከት በ2005 ዓ.ም. ባወጣው ሪፖርት እንደገለጸው፣ የመመርያው አንዳንድ አንቀንጾች በአፈጻጸም ወቅት አሻሚ ትርጉም እንዳይሰጣቸው ከሊዝ አዋጅ ጋር ተዛማጅ የሆኑ አንቀጾችን በማጣቀስ፣ ለትርጉም የሚዳርጉ የመመርያው አንቀጾች በሊዝ አዋጅ ውስጥ ካሉ ድንጋጌዎች መሠረታዊ ዓላማ ጋር መጣጣም አለባቸው፡፡

አዋጁን እንዴት እንደሚያስፈጽም የተቸገረው የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽሕፈት ቤት በየካቲት 2006 ዓ.ም. መመርያ እንዲሰጠው ጠይቆ ነበር፡፡

ጽሕፈት ቤቱ በወቅቱ እንደገለጸው፣ በርካታ የውጭና የአገር ውስጥ ግዙፍ ኩባንያዎች ማኅበራዊ አገልግሎቶች ለሆኑት ለሆቴል፣ ለሆስፒታል፣ ለሞልና ለግዙፍ ሪል ስቴት ግንባታዎች የሚውሉ ቦዎች እንዲሰጣቸው ለከንቲባ ጽሕፈት ቤትና ለመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

የከንቲባ ጽሕፈት ቤትና ቢሮውም የመሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽሕፈት ቤት የውሳኔ ሐሳብ እንዲያቀርብ ይጠይቃሉ፡፡ ጽሕፈት ቤቱ እንደገለጸው፣ የባለሀብቶቹ ጥያቄ በልዩ አገራዊ ፋይዳ ባላቸው ፕሮጀክቶች ይስተናገዱ ቢባል እንኳ በሊዝ አዋጅ አንቀጽ 2 እና በአገራዊ ፋይዳ መመርያ ቁጥር 15/2005 ላይ በግልጽ እንዳሰፈረው፣ ‹‹ልዩ አገራዊ ፋይዳ ያላቸው ፕሮጀክቶች ለኢትዮጵያ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ከፍተኛ ለውጥ የሚያመጡ የልማት ፕሮጀክቶች ወይም የትብብር መስኮች፣ አገሪቱ ከሌሎች አገሮች ጋር ለሚኖራት የተሻለ ግንኙነት መሠረት እንዲጥሉ የታቀዱና የተወሰኑ ፕሮጀክቶች ናቸው፤›› የሚል በመሆኑና ከሊዝ አዋጁ ጋር የሚጋጭ ስለሆነ ለአልሚዎች የቦታ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት መቸገሩን ገልጿል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የሊዝ አዋጁን ተከትሎ የወጣው የሊዝ አፈጻጸም መመርያ ቁጥር 11/2004 አነቀጽ 32 ንዑስ አንቀጽ 2 በግልጽ እንደተደነገገው ከላይ የተጠቀሱት የአገልግሎት ዘርፎች የሚስተናዱት በልዩ ጨረታ እንደሆነ፣ በሊዝ አፈጻጸም መመርያው መሠረት በከንቲባው አማካይነት ለካቢኔ ለሚመሩ ልዩ አገራዊ ፋይዳ ላላቸው ፕሮጀክቶች የሚውሉ ቦታዎች የሚስተናገዱበት መመርያ ቁጥር 15/2005 ቢወጣም፣ መመርያው ከሊዝ አዋጁ ጋር ይጣረሳል ሲል ይተነትናል፡፡

በእነዚህ መሠረታዊ ምክንያቶች አዲስ አበባ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለማስተናገድ አልቻለችም፡፡ ይህ ችግር በክልል ከተሞች የተለያየ ትርጉም እየተጠሰው አድሎአዊ አሠራር እንዲሰፍን ማድረጉ ተመልክቷል፡፡

ሌላው ችግር በተለይ በከተሞች ውስጥ የቀበሌ ቤት ከግል ይዞታዎች ጋር ተደባልቀው የሚገኙበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ በዚህ ክስተት ምክንያት ባለይዞታዎች፣ የግላቸውን ይዞታ መሸጥና መለወጥ እንዳይችሉ ያደርጋቸዋል፡፡ በዚህ ሒደት በርካታ ቅሬታዎች እየቀረቡ ሲሆን፣ የሊዝ አዋጁ ይህንን ቅሬታ ለመመለስ አንቀጾችን ባለማካተቱ በማሻሻያው ላይ ይካተታል ተብሏል፡፡

ሌላኛው ችግር የማስፋፊያ ቦታዎች አቅርቦት ነው፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት አንድ ፕሮጀክት ለመስፋፋት ቢፈልግ በአቅራቢያው የሚገኝ ቦታ በድርድር ማግኘት ይቻላል፡፡ ነገር ግን በሊዝ አዋጁ መሬት በጨረታና በምደባ ብቻ የሚቀርብ በመሆኑ፣ ለማስፋፊያ ፕሮጀክት ቦታ ማግኘት አለመቻሉ ከፍተኛ ችግር መፍጠሩ ተጠቁሟል፡፡ ይህ የማስፋፊያ ቦታ አቅርቦት ችግርም ከሚሻሻሉት መካከል እንደሆነ ተገልጿል፡፡

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close