Connect with us

Ethiopia

ነገርን ሁሉ በልክ እናድርግ

Published

on

ነገርን ሁሉ በልክ እናድርግ

ነገርን ሁሉ በልክ እናድርግ  | ዕዝራ ኃ/ማርያም መኮንን

በሕንድ የነጻነት ታጋይ አመራሮች መሐከል ግጭት በመፈጠሩ ማሐተማ ጋንዲ ብርቱ ችግር አጋጠመው፡፡ መደማመጥ አልተቻለም፣እንዳሻቸው መጓዝ ሆነ፡፡ የጋንዲ ዓላማ ሲጨናገፍ አመራሮቹን ጠርቶ መፍትሔ ፍለጋ ውይይት ይጀምራሉ፡፡ የችግሩ መንስሔና መፍትሔ ላይ አልተማመኑም፡፡ አንዱ ሌላውን ይከሳል፤ የፍቅር ባለአርአያው ጋንዲ ሁሉንም ሰምቶ በምሳሌ እንዲህ አለ፡፡

በርካታ መነኮሳት በሚኖሩበት አንድ የክርስትና ገዳም ውስጥ መነኮሳቱ ስለአልተግባቡ አብሮ መኖር አቃታቸው፡፡ ሥራቸው መወነጃጅል ሆነ፡፡ ለግድያም ይፈላለጉ ነበር፡፡ እንደ እግዚአብሔር አገልጋይ ሳይሆን እንደ አባት ገዳይ ጠላት ይፈላለጋሉ፡፡ የገዳሙ አበምኔት መነኮሳቱን ሁሉ ሰብስቦ መፍትሔ ፍለጋ ተቀመጠ፡፡ ለያዥ ለገናዥ (ለገላጋይ) አስቸገሩ፡፡ እንደምንም ተራ በተራ ቢናገሩም መቀራረብ አልቻሉም፡፡ “አንድ መነኩሴ ተነስቶ ከዚያ ተራራ ማዶ አንድ ብልህ የአይሁድ ራቢ (rabbi) ስላለ ችግራችንን እንንገረውና መፍትሔ ይሰጠናል” ብሎ ሀሳብ አቀረበ፡፡ ስለአይሁዱ ራቢ ሰምተው ስለነበር መፍትሔ ፍለጋ አበምኔቱ ተላከ፡፡

አበምኔቱ ከአይሁድ ራቢ ዘንድ ሄዶ ችግሩን ገልጾ መድኃኒቱን ጠየቀ፡፡ “ተፋጅተን ማለቃችን ነው” አለ፡፡ ራቢው ተከዘና “እግዜር እያመለከተኝ ለብዙ ችግር መፍትሔ ስሰጥ ኖሬያለሁ፡፡ የናንተ የከፋ ቢሆንም አንተ ያመጣኸው ዓይነት ችግር እኛም መሐል አለ” በማለት ተናገረ፡፡ አያይዞም “በተከታታይ ትጠፋላችሁ እንጂ ችግራችሁ መቼም አይፈታም፡፡ ደኅና ሁን” ብሎ አበምኔቱን አሰናበተው፡፡ አበምኔቱ መፍትሔ በማጣቱ እየተከዘና “እናንተ ትጠፋላችሁ እንጂ ችግራችሁ አይጠፋም” የሚለውን እያመሰኳ ወደ ገዳሙ ሲቃረብ ከራቢው ዘንድ አንድ መልእክተኛ እየሮጠ መጣ፡፡ ይዞትም ተመለሰ፡፡

ራቢው አበምኔቱን በደስታ ተቀበለው፡፡ “አንተ ከሔድክ በኋላ እግዚአብሔር አነጋገረኝ፣ እንዲህም አለኝ፡፡ ከዚያ የካቶሊክ ገዳም ከሚገኙት መነኮሳት መካከል አንደኛው ቅዱስ (Saint) ይሆናል፡፡ ስለዚህ ሁሉም መነኩሴ ሊያከብረውና ሊወደው ይገባል፡፡ ይህ የእግዚአብሔር ትእዛዝ ነው” አለው፡፡ አበምኔቱ ወደ ገዳሙ ተመልሶ መነኮሳቱን ሁሉ ሰብስቦ ይህንኑ ሲናገር “ይህ ቅዱስ መነኩሴ ማን ይሆን?” በመባባል ሁሉም አጠገቡ ያለውን በመጠርጠር፣ ተጠርጣሪው ሌላውን በመጠርጠር፣መከባበር ጀመሩ፡፡ ሌላው ለአንዱ ቅዱስ ሆኖ ታየው፡፡ የሕንድ የነጻነት አባት ይህን ምሳሌ በማምጣት በመካከላቸው ፍቅርና መከባበር እንዲፈጠር አደረገ፡፡ ይህን ማለፊያ ምሳሌ ያገኘሁት፣ጸጋዬ ገብረ መድኅን አርአያ በጦቢያ 6ኛ ዓመት ቁጥር 6 መጽሔት ካቀረቡት መጣጥፍ ላይ ነው::

ማንም ቅን ዜጋ ስለሀገራችን መጻኢ ጊዜ ሲያስብ ቀድሞ በአእምሮው የሚመላለሰው ቅርጹን እየቀያየረ እንደ ችግኝ በመፍላት ላይ የሚገኘው ዘረኝነት ነው፡፡ ለ27 ዓመታት የመንግስት ፖሊሲና ስትራቴጂ ሁኖ የቆየው ዘረኝነትን ምክንያት አድርጎ የተነሳው የጋኔን መንፈስ በአንዳንዶች ደም ውስጥ ጠልቆ ገብቷል፡፡ በዘረኝነት መሐንዲሶች በየቦታው የሚለኮሰው ግድያ፣ መፈናቀልና ዘረፋ፣ የእለት ተእለት ዋና ዜና ሁኗል፡፡ ሀገራችን ያጋጠማት ችግር ጋንዲን ካጋጠመው የባሰ ነው፡፡ አንዱ ወገን አባቶቻችንን መላእክት ሲያደርግ አንጻራዊው ደግሞ ጨካኝ የሰይጣን ቁራጭ ያደርጋቸዋል፡፡ አባቶቻችን እንደ ሰው ተሳስተውም ሆነ በጎ ታሪክ ሰርተው መልካም ቅርስና ሀገር አስረክበውናል፡፡

ነገራችን ሁሉ ጽንፋዊ በመሆኑ ልከኛና ምክንያታዊ አይደለንም፡፡ “ወይ ከእኔ! አልያ ከእሱ! ሚናህን ለይ!” የአብዮተኛ አቋም ዛሬም አለቀቀንም፡፡ ስናወድስ መልአክ ስናወግዝ ሰይጣን አድርገን ነው፡፡ ስንክብ በአንዴ ሰማይ ላይ፣ ስናወርድ ደግሞ አንዴ እንጦርጦስ ማውረድና ማፍረጥ ነው፡፡ ጧት የካብነውን ለመናድ እስከ ምሳ ሰዓት እንኳ አንቆይም፡፡ እስከ ዛሬ ለፖለቲካ ሕመማችን መድኃኒት የሚያዙልን እራሳቸው መድኃኒት የሚያስፈልጋቸው ደፋር የአእምሮ ሕሙማን እንጂ በሰከነ ፖለቲካ የሚመሩ አስተዋዮች አይደሉም፡፡ በዚህም የተነሳ ለበሽታችን የምንወስደው የሕመም ማስታገሻን እንጂ የተውሳኩን ጠንቅ ከስሩ የሚያጠፋ አይደለም፡፡

ስለ ልከኝነት አንድ ነገር ልበል፡፡ መድኃኒት ሲያንስ ከበሽታው ጋር ይለማመድና ስር ሰዶ ለፈውስ ያስቸግራል፡፡ ከልክ በላይ ሲወሰድም ወደ መርዝነት ይለወጣል፡፡ መድኃኒት የሚፈውሰው በልኩ ሲሆን ነው፡፡ ምግብ ሲያንስ ለበሽታ ሲበዛ ለቁንጣን ይዳርጋል፡፡ ሲበቃን መመገባችንን እንድናቆም ሰውነታችን ይጠቁመናል፡፡ እውቀት ሲያንስ ለማይምነት፣ ለጥራዝ ነጠቅነትና ለሞኝ ድፍረት ሲዳርግ በአግባቡ ካልተቀሰመና በወጉ ጥቅም ላይ ካልዋለ ጎጂ ይሆናል፤ሊያጃጅልም ይችላል፡፡ ሚዛን ለመጠበቅ በሁሉም ነገር ልከኛ መሆን ጠቃሚ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ሁለተኛ ጢሞቲዎስ ምዕራፍ ፬ ቁጥር ፭ ላይ ሐዋሪያው ጳውሎስ ለወጣቱ መጋቢ ጢሞቲዎስ “አንተ ግን ነገርን ሁሉ በልክ አድርግ” ብሎ መክሮታል::

ከሀገራችን የፖለቲካ መሰረታዊ ችግሮች አንዱ የልከኝነት ወይም የሚዛን መዛባት ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ለዚህም የሀገራችንን ፖለቲካ ጽንፋዊነት መመልከቱ ተገቢ ነው፡፡ በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ኮሙኒዝምን እንደ ጋኔን መንፈስ ትመለከት የነበረችዋ ኢትዮጵያ የአሜሪካ ጥብቅ ወዳጅ ነበረች፡፡ ደርግ ኮሙኒዝም ሆነ፡፡ ኮሙኒዝም በወደቀበት ዘመን እንኳ “ከቄሱ ደቀ መዝሙሩ” እንዲሉ ኢትዮጵያ ከሶቪየት ሕብረት ብሳ ተገኘች፡፡

በሀገራችን ትናንት፣ ዛሬና ነገ ኅብርና ስሙር ሆነው አያውቁም፡፡ ኢሕአዲግ በትግል ላይ እያለ በዓለም የተገለለው የአልባንያ ኮሙኒስት ተከታይ በመሆን ሶቪየት ኅብረትንና ቻይናን እውነተኛ ኮሙኒስቶች አይደሉም ብሎ ይከስ ነበር፡፡ ቤተ መንግሥት እንደገባም ወዲያው አልተለወጠም፡፡ ኤርሚያስ ለገሠ (በየትኛው መጽሐፉ እንደገለጸው ብዘነጋም) አንዲት ታጋይ ሦስት ፓንት ገዝታ ሁለቱን ለጓዶችዋ ባለመስጠትዋ በራስ ወዳድነት ተገምግማለች፡፡ ዛሬ እነዚህ ታጋዮች በፕራዶ መኪና የሚንፈላሰሱ፣ የቪላ ቤት ጌቶች፣በሕክምና ሰበብ አውሮፓና ዱባይ የሚዘባነኑና ልጆቻቸውን አሜሪካና አውሮፓ የሚያስተምሩ ሆነዋል፡፡

ቀውሶች፣ አብዮቶችና ጦርነቶች የኅብረተሰብ ቅራኔዎችን ከማወሳሰብና ከማፋጠን ውጭ መፍትሔ አያመጡም፡፡ የፖለቲካ ጥያቄ ጦር በመማዘዝ አይፈታም፡፡ በፍቅር፣ በአንድነትና በመተሳሰብ ለዘመናት አስተሳስረው ያኖሩን ማኅበራዊ ድሮች እንዲበጣጠሱ ሌት ተቀን የሚሠሩ አንዳንድ ልዒቃን ይህን ክፉ ጊዜ አምጥተውብናል፡፡ የሕዝብ ድጋፍ ያላቸውን ፓርቲዎችን አፍርሶ በሙሉጌታ ሉሌ አገላለጽ የኢሕአዲግ “ትርፍ አንጀት” የሆኑ ፓርቲዎችን ማቋቋም ለኢሕአዲግ መፍትሔ አላመጣለትም፡፡ በድሀነታችን ላይ ዘረፋ፣ ግድያና መፈናቀል ሲጨምር ምን እንደሚከተል አስቡ፡፡ በሀገራችን አንዳንድ ቦታዎች በማንነት ላይ የተፈጠረው ግድያ፣ዘረፋና መፈናቀል የታሪካችን አሳፋሪ ገጽታ ከመሆኑም በላይ በአጭሩ ካልተቀጨ “ነገ”ያችንን ያበላሻል፡፡ ይህ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ የኅሊና ደወል ነው፡፡

የስቃይና የጭንቀት ጽዋችን ሞልቶ እየፈሰሰ ነው፡፡ ትናንሽ ጭንቅላቶች ትናንሹን እያጋነኑ በተፈጠረው መፈናቀል፣ ግድያ፣ ችጋር፣ ግጭት፣… የሰርኩን ዜና የሚሻማው የመርዶ ሪፖርት በመሆኑ መደነቁንም የተዉን ይመስለኛል፡፡

ቢቢሲ የአማርኛው ድረ ገጽ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅትን (አይ ኦ ኤም) ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ በምዕራብ ጉጂና በጌዲዮ አዋሳኝ አካባቢዎች በተቀሰቀሰው ግጭት 970 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች ተፈናቅለዋል፡፡ ከሙታን ወይም ከሕያዋን ተራ ለመመደብ የሚከብዱትን ቆዳ፣ አጥንትና ነፍስ የተዋሐዱበትን የጌዴዮ ተፈናቃዮችን ምስል ማየት ይዘገንናል፡፡ የእርዳታ እህሉ በ”ሞት ነጋዴዎች” በአየር ላይ ሳይቀለብ እንዳልቀረ ተፈናቃዮቹ ጥርጣሬያቸውን ገልጸዋል፡፡

እንደ ሀገር ውስጥና የውጭ ሚዲያዎች መረጃ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች 3.1 ሚሊዮን ሕዝብ ተፈናቅሏል፡፡ በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥርም በዓለም ቀዳሚ ሆነናል፡፡ በአራቱም አቅጣጫ የምንሰማው የመፈናቀልና የሞት መርዶ ነው፡፡ በሐዋሳ ከተማ ለቀናት ሰዉ ከቤት እንዳይወጣ ተደርጓል፡፡ ፌዴራል መንግሥቱ በክልሎች ላይ ያለው ጉልበት ተበርክርኳል፡፡ ሕግ በጎጥ ጉልበተኞች እየተዳጠ ነው፡፡ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ፣ በድሀነታችን ላይ ይህ ሁሉ መዓት ወርዶብን ምን ልንሆን ነው? እንዲህ ሆነን እስከ መቼ እንቀጥላልን? በመንፈስም በቅርስም ትልቅ ሆነን ሳለ እንዴት ወደ ንዑስነት ለመለወጠ እንተጋለን? የመንግሥት ልበ ሰፊነትና ትዕግስት ከገደቡ አልፎ ወደ ዳተኛነት እየተቀየረ ነው፡፡ “መንግሥት ሆይ የት ነህ? ወዴት ነህ?” ብለን ለመጠየቅ እንገደዳለን፡፡

በትናንሾች መካከል ትልቅ መሆን የሚፈልጉ የጎጥ ጎበዝ አለቆች በሚፈጥሩት ችግር እንደ ባቢሎን ግንብ ዘመን ሰዎች ቋንቋችን ተደበላልቋል፡፡ የልከኝነት መጥፋት ሚዛናችንን አስቶናል፡፡ ንትርካችንም በጠላትነት ለመጠቋቋም እንጂ የደፈረሰውን የጎሣ ፖለቲካ መንስዔ ከመሰረቱ አጥንተን መፍትሔ ለመስጠት አይደለም፡፡ ሀገራችን ታማለች፤ሕመሟም ፈውሷም እኛው ነን፡፡ “ለሀገሬ ፈውስ ተዘጋጅቻለሁኝን?”፣ “ካንሰር ከሆነው ዘረኝነት የነጻሁ ነኝን?”፣ “የእኔ ድርሻ ምንድን ነው?” ብለን እራሳችንን መጠየቅ ይገባናል፡፡ ለሁላችን ኅሊና የሚቀርብ ጥያቄ ነው፡፡

በዚህም አንጻር እንደ ሰብአ ሰገል (ከምሥራቅ የመጡ ብልህ ሰዎች) የክፉ ቀን በጎዎች፣የጨለማ ቀን ብርሃኖች ሊኖሩን ይገባል፡፡ የተከበሩ የሕዝብ ፍቅርን እና ታማኝነትን ያተረፉ እንደ ብልሁ የአይሁድ ራቢ ያሉ ታላላቅ ሰዎች በየሙያው፣በየመስሪያ ቤቱ፣በቤተ ሃይማኖቶች እና በአካባቢያችን ሁሉ ያስፈልጉናል፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close