Connect with us

Ethiopia

አምነን ሥልጣኑን የሰጠናቸው ኦዴፓዎች ምን ነካቸው?

Published

on

አምነን ሥልጣኑን የሰጠናቸው ኦዴፓዎች ምን ነካቸው?

አምነን ሥልጣኑን የሰጠናቸው ኦዴፓዎች ምን ነካቸው? |

በሰፊ አገራዊ ተቀባይነት ወደ መሪነት ሥልጣን የመጣው ኦደፓ ለባለፉት ወራቶች አገር ከማስተዳደር በተጨማሪ ለምስራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ ትብብር ደፋ ቀና ሲል ከርሟል፡፡ እኛም እንደ መሪ ብቻ ሳይሆን እንደ መሲህ ተቀብለናቸው ሰንብተናል፡፡

ሆኖም እኒህ መሪዎች ያገኙትን ተወዳጅነት ተጠቅመው ሕዝባቸውንና አገራቸውን ወደ ፊት በማሸጋገር ፈንታ ወደ ኋላ ሲመለሱና ቃላቸውን ሲጥሱ በመታየታቸው ከሁሉም አቅጣጫ ሲሰማ የነበረው የድጋፍ ድምጽ መቀነስ ጀምሯል፡፡ ከዚህ ባለፈም ካለው ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት ‹‹ኦዴፓ አገር መምራት አልቻለም ወይንም ደግሞ አልፈለገም›› የሚሉ ዜጎችም አሉ፡፡ አብዛኛው ህዝብ ግን አሁንም ቢሆን በትዕግስት ሆኖ ስልጣን ላይ ያሉት ሰዎች አገራችንን ከአሮንቃ የሚያወጡበትን ቀን በመጠባበቅ ላይ ይገኛል፡፡

በሌላ መልኩ ግን ኦዴፓ ይሄንን እውነታ ተረድቶ ህብረተሰቡ የሚፈልገውን ለውጥ ማምጣት ይቅርና በኃላፊነት የተሞላ መግለጫ ማውጣት አቅቶት አንዱን ዘመድ ሌላውን ባዕድ ሲያደርግ እያየነው ነው፡፡

ይሄንንም ለማብራራት የክልሉ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ በሆኑት በአቶ አድማሱ በኩል የቀረቡትን ሁለት መግለጫዎች መመልከት ይበቃል፡፡

ከአስር ቀናት በፊት ከኮንዶሚንየም እጣ ጋር ተያይዞ በመላው ኦሮሚያና በአዲስ አበባ ዙሪያ ድምጽ-አልባ ጦር መሳሪያ ይዘው በመውጣት ከተቃውሟቸው ጋር ዛቻቸውን ያስተላለፉ ወጣቶችን፣ ጥያቄያቸውን ባይቃወም እንኳን የቀረበበትን መንገድ ያወግዘዋል ብለን ስንጠብቅ ‹‹ጨዋዎች›› ብሎ ሲያሞግሳቸው ተሰምቷል፡፡

ቅዳሜ ቀን ደግሞ በዚሁ ባለስልጣን አማካኝነት ‹‹የኦሮሞ ህዝብ አገር መምራት አይችልም›› እየተባለ መሆኑን ጠቅሶ ‹‹ይሄን የሚሉ ሰዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቱን›› አስታውቆ ሲያሰገርመን ውሏል፡፡ እግረ-መንገዱንም አገራችንን እየመራ ያለው ኢህአዴግ ሳይሆን ኦዴፓ መሆኑን ገልፆልናል፡፡

ባለሥልጣኑ እንዳለው ቢሆን እንኳን… ከኦሮሚያ ክልል በሚበልጥ ሁኔታ የመደመር ሰልፍ አዘጋጅተን፣ ምድሩ ላይ ያለውን ቁስ ሁሉ በእነሱ ምስልና አባባል ሸፍነን የተቀበልነው ፓርቲ ‹‹ፈረሱም ያው፣ ሜዳውም ያው›› ሲባል መሪነቱንም ሆነ ነጂነቱን ማሳየት ሲገባው ‹‹የኦሮሞ ህዝብ መምራት አይችልም እየተባለ ነው›› ማለቱ ግራ-የሚያጋባ መግለጫ ሁኖብናል፡፡

ምክንያቱም ከክልሉ በተጨማሪ የጠቅላይ-ሚኒስትርነቱንም ቦታ ይዞ አገራችንን እንዲመራ ከሙሉ ይሁንታ ጋር ያስረከብነው ለኦሮሞ ህዝብ ሳይሆን ለኦዴፓ ነው፡፡ ታዲያ ከሕዝብ የሚወጡ መሪዎች እንጂ አንድ ሕዝብ ወደ መሪነት ሊመጣ እንደማይችል እየታወቀ ኦዴፓ ‹‹የእናቴ ቀሚስ አደናቀፈኝ›› እንዳለችው ጦጣ ‹‹ሕዝቤ መምራት አይችልም ተባለብኝ›› ማለቱ ስለምን ይሆን?

የመሪነትም ሆነ የትኛውም ዓይነት መክሊት ለአንድ ህዝብ የሚታደል፣ ለሌላ ህዝብ የሚከለከል አለመሆኑን ማንኛውም ተራ ሰው የሚያውቀው ሃቅ ሆኖ ሳለ…. እንደ ድርጅት የቀረበን ትችት ለህዝብ መስጠት ምን የሚሉት አካሄድ ነው?

የራሴን ጥያቄ እራሴ ስመልሰው… ኦዴፓ በማይመራው ክልል ፈንታ የሚመራው ክልል ውስጥ የሚኖረው ህዝብ እሱን ትቶ ሌላ ድርጅት ላይ ተስፋውን ሳያስድርበት አልቀረም፡፡ ስለሆነም ‹‹የኦሮሚያ ህዝብ አገር መምራት አይችልም እየተባለ ነው›› በሚል ሙሾ እንደ አገር ያገኘውን ተቀባይነት በመደምሰስ በክልሉ ያጣውን ተቀባይነት ለመሸመት ፈለገ፡፡ እናም በበታችነት ስሜት የሚፈጠረውን ቁጭት ተሳፍሮ እራሱን ወደ ከፍታ ለማውጣት ሲል ይሄንን አስጸያፊ ሃሳብ ሊጠቀመው ቻለ፡፡

ኦዴፓ ይህችን ስልት ከህውሓት የወረሳት አስተምህሮት ስትሆን…. እንደሚታወቀው ፖለቲከኞች ተቀባይነታቸው እያነሰ ሲመጣ ወይንም ደግሞ በላያቸው ላይ የሆነ ስጋት ሲያንዣብብ መዳኛቸው ብሔራቸውና ሐይማኖታቸው ውስጥ መደበቅ ነው፡፡

የአገራችንን አንድነት አስጠብቆ ወደ ዲሞክራሲ ያሸጋግረናል በሚል እምነት ከሊቅ እስከ ደቂቅ ባለው ህዝብ ግዙፍ ተስፋ ከተጣለበት ድርጅት እንዲህ ያለ ድርጊት አይጠበቅም፡፡ ሌላ ውስጣዊ ዓላማ ከሌለው በቀር እንደ አገር ያለውን ተቀባይነት በመናድ በክልሉ ህዝብ ለመወደድ መሞከርም የከንቱ ከንቱ ይመስለኛል፡፡

እናም ሃሳቤን ጠቅለል ሳደርገው በኦሮሚያ ክልል መንግስት ኮሚኒኬሽን ባለስልጣን አማካኝነት ኦዴፓ ያወጣው መግለጫ ከራሱ ልብ አፍልቆ ለራሱ ህዝብ ያስተላለፈው የጥላቻ መልእክት መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ ምክንያቱም ማንኛውም ኢትዮጵያዊ መወቀስ ያለበት አሁን ስልጣን ላይ ያለውን ጠቅላይ ሚኒስትር እና ቲም-ለማን እንደ ማንኛውም መሪ መቀበል ሲገባው… ‹‹አገር ይታደጉ ዘንዳ ከሰማየ-ሰማያት ተልከው፣ ከኦሮሚያ ተወልደው፣ ወደ ስልጣን እንደመጡ መሲሆች›› በመቁጠሩ ብቻ ነው፡፡

ያልታደለው ኦዴፓ ግን ‹‹ከግዙፍ ህዝባዊ ድጋፍ ጋር የጣልንበትን አገር የመምራት አመኔታ ለኦሮሞ ህዝብ በማስተላለፍ ወንድማማችነታችንን ያሳድግበታል›› ብለን ስናሰብ…. የራሱን አሉባልታ ፈጥሮ ወደ ህዝብ በማውረድ በጥላቻ እንዲንተያይ ማድረግን መርጧል፡፡

በአጋር ድርጅቶች ትብብርና በብዙ ወጣቶች ትግል የተሰጠውን ኃላፊነት ተቀብሎ ብቃቱን እንደማሳየት፣ ካቃተው ደግሞ ‹‹አልቻልኩም›› እንደማለት አለመቻሉን ‹‹ተባልን›› የሚል ካባ በማልበስ ህዝብና ህዝብን እያለያየ መሰንበትን ምርጫው አድርጓል፡፡

ከዚህ ባለፈ ደግሞ እንዲህ ያለው ውዳቂ ሃሳብ በግለሰብ ደረጃ ቢንጸባረቅ እንኳን የሰውዬውን የማሰብ አቅም ከማሳየት አልፎ መግለጫ ውስጥ ለመካተት የሚበቃ አለመሆኑ ግልጽ ሆኖ ሳለ…. ኦዴፓ ግን ራሱን ያፈለቀውን ሃሳብ ለሌላ አካል በማስረከብ የራሱን ሕዝብ ከተሳደበበት በኋላ፣ በመግለጫው ማጠቃለያ ‹‹ይሄን በሚሉ ሐይሎች ላይ አስፈላጊውን እርምጃ እወስዳለሁ›› በማለት ዝቷል፡፡

እኔ ደግሞ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ የራሴን መግለጫ ሳወጣ ‹‹በዚህ ጉዳይ ላይ ኦዴፓዎች ተጠያቂ እንጂ ጠያቂ ሊሆኑ አይችሉም›› እላለሁ፡፡

(ከአዘጋጁ፡- ይህ ነጻ አስተያየት የጸሐፊውን እንጂ የድሬቲዩብን ኤዲቶሪያል አቋም አያሳይም)

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close