Connect with us

Art and Culture

ታማኝ፤ እንደ ስሙ የሚኖር ለሀገሩ የታመነ የቁርጥ ቀን ልጅ

Published

on

ታማኝ፤ እንደ ስሙ የሚኖር ለሀገሩ የታመነ የቁርጥ ቀን ልጅ

ታማኝ፤ እንደ ስሙ የሚኖር ለሀገሩ የታመነ የቁርጥ ቀን ልጅ፤ ተፈናቃዩን ለመደገፍ እንደተጋገዝን ሁሉ፤ ማንም ሰው እንዳይፈናቀል ተባብረን የምንጠየፈውን ተግባር ከኢትዮጵያ ምድር እናስወግደው፤ **** ሄኖክ ስዩም በድሬቲዮብ

እንደ ታማኝ መኾን ለጥቂቶች የተሰጠ ጸጋ ነው፡፡ በመፈለግ ብቻ አይኮንም፡፡ መታደል ነው፡፡ ስምን መሆን ከጸጋ ሁሉ የሚበልጥ ጸጋ ነው፡፡ ያንን ጸጋ ኾኖ ኖሮታል፡፡ ለሀገር ታምኗል፡፡ ኢትዮጵያ ብሎ ጮኾ በኢትዮጵያ ደጋግሞ ተፈትኖ ደጋግሞ አሸንፎ አሳይቷል፡፡

ይልቁንስ ለሁሉም የታደለው እንዲህ ያለውን በጎ ስራ መደገፍ ነበር፡፡ እንዲህ ያለውን በጎ ስራ ማወደስ ነበር ለዚህ ሰው መኾን በቂ ነበር ለዚህ እንስሳም የማይታማበት ጉዳይ ነበር፤ ከዚህ መጉደል ከፍጥረት መጉደል ነው፡፡

የጌዴኦ ተፈናቃዮች ያሳዝናሉ፡፡ አንድም ኢትዮጵያ ውስጥ ስለኾነ ይሄ ገጠማቸው፡፡ እነኛ ህጻናት እንግሊዝ ተፈጥረው ቢሆን ኖሮ ጣሊያናውያን ቢሆኑ አሜሪካ ምድር ቢወለዱ ስካንዲቪያን እትብታቸው ቢቀበር ይሄ አይገጥማቸውም ነበር፤ ደግሞም ኢትዮጵያ ውስጥ ኾነውም የእኛ ትውልድ አባል ባይሆኑ ውጣ ከሰፈሬ በሚባልበት ዘመን ባይፈጠሩ ቢቀድሙ ወይ ቢዘገዩ ይሄ አይሆንም ነበር፡፡

ይሄ የዚህ ትውልድ ወንጀል ውጤት ነው ሊያቆመውም የሚገባው ይህ ትውልድ ነው፡፡ የትግራይ ክልል መልካም ነገር ማድረጉን ሰምተናል፡፡ ጠቅላያችንም ተጎጂዎችን ጎብኝተዋል፡፡ በዓለም ያለ ኢትዮጵያዊ ለመስጠት አልሳሳም የሚታመነውን ታማኝን አምኖ ጠብ ያደረጋት ተጠራቅማ ተአምር ሆናለች፡፡ መተጋገዝ ባህላችን እንደሆነ ታይቷል፡፡

የዚህን ትውልድ መከራ መተጋገዝ ብቻ አይፈታውም፤ ይልቁንም የተፈናቀለውን ለመርዳት ከዳር ዳር ሆ ብለን እንደተነሳነው ሁሉ የሚፈናቀል እንዳይኖርም እንዲሁ አንድ ላይ እንቁም፤ አምስት አስርና መቶ ሰዎች በሚሊዮኖች እጣ ፈንታ ሲወስኑ ምክንያታቸው ምንም ሊሆን ይችላል፤ ሚሊዮኖች ከተጋገዙ ሚሊዮኖች ድምጻቸው ከተሰማ ክፉ ሀሳብ ሲያገነግን ሁሉም ዘሬ እምነቴ ሳይል አንድ ላይ እኩይ ተግባርን ቢጠየፍ የምንጠላውን ክስተት በምድራችን አናየውም፡፡

ከማንም በክፉ ሀሳብ መተባበርን እንቢኝ ካልን ክፉዎች ብዙ አይደሉም፤ ክልል ሊመሩ ይችላሉ የክልሉ ህዝብ ግን ክፉ ስላልሆነ የክፉ ክልል መሪዎች ሀሳብ ከምናባቸው ያለፈ ጉልበት አይኖረውም፤ ሚሊዮን ሰው ሊከተላቸው ይችላል፤ የሚሰማቸው ሰው እንደ እነሱ በክፋት ሀሳብ ስላልሰከረ ክፉን እንቢ ማለት ከጀመርን ሜዳ ላይ እርቃናቸውን እናገኛቸዋለን፡፡ እናም ደግነት ያሸንፋል፡፡

ደግነት የብዙ ድካም ውጤት ነው፡፡ የሌላውን መፈለግ ቀርቶ የራስን አሳልፎ ሲሰጥ የማይሰስት ነው፡፡ ደግ የትም ሁሉን ያሸንፋል፡፡ ደግ የምንሆነው ለፍጥረት ሁሉ ቢሆን መልካም ነው፤ አሊያ ግን ተዋልደን ተጋብተን አንዳችን የሌላችንን ወዝ ተጫልፈን ብዙ መስለን አንድ ሆነን ከምንኖረው የሀገራችን ህዝብ ጋር በደግነት መተሳሰብ ሁሉን ያሸንፋል፡፡

ዛሬ የሚፈናቀሉ የመፈናቀል ፍጻሜ ሆነው ከዚህ በኋላ የተፈናቀሉ የሚለው ጆሮ እየለመደው የመጣው ሴጣን ሀሳብ ድራሹ መጥፋት አለበት፤ ክፋት ልምምድ ነው፡፡ ሰው መሰደድ ይለምድና፤ ሰው መግደል ይለመድና፤ የሰው ረሃብ የጥጋብን ያክል ጆሮ የማይሰጠው ጉዳይ ይሆንና የዚህ ሁሉ ልምድ ድምር ውጤት ፍጡር ሁሉ የሚጠየፋት ሀገር ባለቤት መሆን ነው፡፡ እናም ጆሮአችን የሚሰማውን መከራ በመልካም በመስማት አናለማምደው፤ እናቁመው፡፡ መፈናቀል ይቁም ስደት ይቁም ዘረኝነት ይቁም ሰው መጥላት ይቁም፤ መንጋ መሆን ይቁም፡፡ ሰው መሆን ከፍ ይበል፤ ሰው የሰው መድሃኒት ነውና፤

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** የተለያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዝኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close