Connect with us

Business

ገበሬው በጉብዝና ወራት በጉልበቱ በእርጅናው ደግሞ በጸሎቱ የታደገን ወገን ነው

Published

on

ገበሬው በጉብዝና ወራት በጉልበቱ በእርጅናው ደግሞ በጸሎቱ የታደገን ወገን ነው

ገበሬው በጉብዝና ወራት በጉልበቱ በእርጅናው ደግሞ በጸሎቱ የታደገን ወገን ነው፡፡
ከቤታቸው የወጡትን ወደ ቤታቸው እንመልስ፤
ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች ዛሬ ሸራተን ትጠበቃለችሁ፡፡
ከሄኖክ ስዩም

ዛሬ ሜዳ ወደቁ ያልናቸው ሰዎች ትናንት ቤት ነበራቸው፤ ቀዬ ነበራቸው እንዲህ ያለውን የእረፍት ቀን በሰንበቴ የሚያሳልፉ ጓዳ ሙሉ ነበሩ፡፡ ጎጃቸው መታፈሪያቸው ነበረች፡፡ አባቶቻቸው በወግ በሥርዓት ነው ያሳደጓቸው፡፡ ለኢትዮጵያ መሞት ለኢትዮጵያ መሰደድ የማይጠሉ ሀገር ወዳድ ዜጎች ናቸው፡፡ ያ ወግ የቀጠለባት መንደር ዛሬ ጠፍ ሆና የመንደሯ ህዝብ ስደት ገጥሞታል፡፡

ምዕራብ ጎንደር ዘጠና ሺ የሚሆኑ ወገኖቻችን ሜዳ ላይ ናቸው፡፡ ቤታቸው እየናፈቃቸው፡፡ እንደ ሰው በባድማቸው መኖር እየፈለጉ ግን ያለቦታቸው ናቸው፡፡ የጎጆ ጢስ የናፈቃቸው እናት ሜዳ ወድቀው የሀገር ያለህ፤ የወገን ያለህ እያሉ፤ አምርቶ ያበላ ጉልበት ለእርጥባን እየተዘረጋ ነው፤ እናም ሆ ብለን ለቤታቸው እናብቃቸው፡፡

ምዕራብ ጎንደር እንዲህ ነው፤ ልጅ በአጎቶቹ ላይ መዝመት አይችልም፤ አባት የልጁን ሚስት መግደል አይችልም፡፡ ቅማንትና አማራ እጅግ የማይነጣጠሉ ናቸው፡፡ ክፉዎች የዘረጉትን ወጥመድ አልተጠለፉበትም፤ አልተጠፋፉም፡፡ ክፉዎች ግን ክፋታቸው አላበቃም፤ ከቤት ከቀዬያቸው እንዲፈናቀሉ አደረጉ፡፡

የእንመልሳቸው ጥሪው ይሄ ነው፡፡ ይሄ ገበሬ ትናንት አርሶ አብልቶናል፡፡ የወጣትነት ዘመኑን በጉልበቱ እርጅናውን በጸሎቱ ስለ እኛ የሚደክም የእኛው አለኝታ ነው፡፡ አልማ ጥሪ አቅርቧል፡፡ መልከ መልካሙ ሰው መላኩ ፈንታ መልካም ሀሳብ እየመራ ነው፡፡ ዛሬ ሸራተን የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን ይደረጋል፡፡ አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ገዳማ የሚፈጀው መልሶ በክብር ተፈናቃዮቹን ለቤታቸው የማብቃት ስራ ተጀምሯል፡፡

ከዳር ዳር መተጋገዝ አለብን፡፡ ከዳር ዳር መጠራራት አለብን፤ አብረን ኖረናል፤ አብረን ሞተናል፤ እንዲህ ያለውን መከራ አብረን ማስወገድ ይገባናል፡፡ ጥሪውን አድምጣችሁ ለወገን የምትደርሱ ሰዎች ብሩካን ናቸው፡፡ መታደል ነው፤ ማድረግ እንደመቻል መልካም እድል የለም፤ ማድረግ የቻላችሁት እግዚሃር ስለረዳችሁ ነው፡፡

ይሄ ትብብር ግብ አለው፡፡ ከዚህ በኋላ ስደት እንዳይኖር፤ መፈናቀል እንዳይኖር፤ መገዳደል እንዳይኖር፤ የሚያደርግ አንድነትን ይፈጥራል፡፡ ሩቅ መጓዝ የምንችለው የቅርብ ችግሮቻችንን እንዲህ ተጋግዘን ስናስወግድ ነው፡፡

አምናለሁ እነኛ የደጋግ ገበሬ መንደሮች ዳግም ነፍስ ይዘራሉ፡፡ ዳግም የበጎች ድምጽ ይሰማል፡፡ ዳግም ጋጣው ነፍስ ይዘራል፡፡ ዳግም የዛፍ ስር ጥላዎች ቁጭ ብለው በሚመክሩ አረጋውያን መጪውን ጊዜ ቀና ያደርጋሉ፡፡ ሜዳ የወደቀችው እናት ለጎጆዋ ትበቃለች፡፡ ቤት ይሞቃል፡፡ ልጆች ከቤታቸው ወጥተው ትምህርት ውለው ይገባሉ፡፡ ጎተራው ይሞላል፡፡

አምናለሁ፤ ያቺ ደግ የገበሬ ሚስት ማድጋዋን ሞልታ፣ ማጀቷን አደርጅታ፣ ጥጆቿ ያስተረፉትን ጎረቤቷ በቃኝ እስኪል ስታጠጣ አያለሁ፡፡ ከተባበርን ይህ ይሆናል፡፡ ተስካሩ በወግ ይወጣል፤ ልጅ በክብር ይዳራል፡፡ መንደሩ በጥጋብ አካባቢው በበረከት ይሞላል፡፡ አምናለሁ ከተባበርን ይህ ይሆናል፡፡

ተቃጥለው አመድ በሆኑ ጎጆዎች ምትክ አዲስ ምሰሶ ያቆማቸው ቤቶች አዲስ መንደር ይፈጥራሉ፡፡ በአዲስ መንፈስ አዲስ መንደር እውን ሲሆን አሮጌውን የመከራ ሀሳብ ከወገናችን ጫንቃ ላይ እናሽቀነጥረዋለን፡፡ እናም ሆ ብለን እንነሳ፤

እኔን ለምትል እናት እኔን ብለን እንውጣ፤ ወንድሜን ለሚል ገበሬ ወንድም ጋሼ እንበለው፡፡ ይህ ከሆነ መከራን እናሸንፈዋለን፤ ችግር በህብረት ክንዳችን ይደቃል፤ ሀገር ጥቁር ልብሷን ጥላ ሸማ ትለብሳለች፡፡ ደግሞም ይህ ይኾናል፡፡
አልማን እናመሰግናለን፡፡

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close