Connect with us

Ethiopia

ኢሕአዴግ ቤት ውስጥ የተፈጠረው ምንድን ነው? ‹ችግር ጠማቂስ› ማነው?

Published

on

ኢሕአዴግ ቤት ውስጥ የተፈጠረው ምንድን ነው? ‹ችግር ጠማቂስ› ማነው?

ኢሕአዴግ ቤት ውስጥ የተፈጠረው ምንድን ነው? ‹ችግር ጠማቂስ› ማነው? | በኃይሉ ሚዴቅሳ ፍስሃጽዮን

ሰሞኑን አስቀያሚ ስሜት ላይ ስለነበርን ቆዝሜ ከርሜያለሁ፡፡ብሄራዊ ሐዘን ላይ ስለነበር ጠጠር ያለ ፖለቲካ መፃፍ አልፈለግሁም፡፡አሁን ግን ሐዘኑ ባይለቀንም ወደ ጉዳዬ ተመልሻለሁ፡፡እንዲህ ስልም እጠይቃለሁ፤‹‹በርግጥ በኢሕአዴግ ቤት ውስጥ ምን ተፈጠረ?››

በቅድሚያ ይህንን ጥያቄ ለምን እንዳነሳሁ ልጥቀስ፡፡የኦሮሚያ መግለጫና የጠቅላይሚኒስትሩና ምክትላቸው ከመግለጫው የተቃረነ ሐሳብ ያነሳው ጉዳይ ነው ዋነኛው አጀንዳ፡፡ባሳለፍነው ሳምንት በወጣው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት መግለጫ ‹‹የአዲስ አበባም ሆነ ተያያዥ ጉዳዮች በቅደም ተከተል ምላሽ እንደሚያገኙ የተስማማንባቸው ጉዳዮች ነበሩ›› ብሎ ነበር፡፡ከዚያም ‹‹ነገር ግን በአዲስ አበባና ኦሮሚያ መካከል ያለው የወሰን ጉዳይ እልባት እስከሚያገኝ ድረስ የኦሮሚያን ወሰን ተሻግረው የተሠሩ መኖርያ ቤቶች በዕጣ መተላለፋቸው ተቀባይነት የለውም›› ሲል እቅጩን ተናገረ፡፡ቀጠለናም፣ ‹‹መኖሪያ ቤቶቹ በእጣ ለተጠቃሚዎች የማስተላለፍ ሂደት እንዳይተገበር አቋም ይዟል”

“በአዲስ አበባ ጉዳይም ከወሰንና ቤቶች ጉዳይ በዘለለ የከተማዋን የኦሮሞ ባለቤትነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክረን እንቀጥላለን” የሚለው ጉዳይም በዚሁ በአቶ ለማ መገርሳ መንግሥት የወጣ መግለጫ ነው፡፡በተለይ ሁለተኛው አንቀጽ ላይ የሰፈረው ሐሳብ ለየት ያለ ሐሳብ ያለው ይመስለኛል፡፡‹‹የከተማዋን የኦሮሞ ባለቤትነት ለማረጋገጥ››የሚለው ቃል፣አዲስ አበባን የኦሮሞ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የሚገልጽ መሆኑን ነው፡፡

ከዚያ በኋላ ነው ጠቅላይሚኒስትሩና ምክትላቸው ‹ተከድተናል› የሚል ይዘት ያለው ንግግር ያደረጉት፡፡ባሳለፍነው ሳምንት በሴቶች ቀን ላይ በአዲስ አበባና በባሕርዳር ሁለቱም መሪዎች ያደረጉት ንግግር ከዚህ ከኦሮሚያ መግለጫ ጋር ፍጹም የተቃረነና አካታች ነው፡፡ይልቁንም አብረው ከርመው አሁን ሸርተት ያሉ ሰዎችን ጠቅላይሚኒስትር ዐቢይ ‹‹ጥቂቶች ›› ብለው ሲጠሯቸው፣አቶ ደመቀ ደግሞ ‹‹ችግር ጠማቂ›› ብለዋቸዋል፡፡

ይሔኛውን ጉዳይ እንመለስበታለን፡፡በቅድሚያ ስለ አዲስ አበባ የተነሳውን ሐሳብ እናስቀድም፡፡

በአፍሪቃ ሕብረት አዳራሽ በተካሄደ የሴቶች በዓል ላይ ጠቅላይሚኒስትር ዐቢይ ካርቱም ብዙ ኢትዮጵያዊያንን መያዟንና ናይሮቢም በርካታ ሱማሊያዊያንን ማስጠለሏን ጠቃቅሰው፣አዲስ አበባ እንኳን ለኢትዮጵያዊያን ለአፍሪቃም የምትበቃ መሆኗን አነሱ፡፡ነገሩ የሚያሰባስብ እንጂ የሚያለያይ መሆን እንደሌለበትም መከሩ፡፡

በዚያኑ ቀን ማታ በአቶ ገዱ አንዳርጋቸው የሽኝት ፕሮግራም ላይ የታደሙት አቶ ደመቀ ደግሞ ‹‹በመሰረቱ አዲስ አበባ ሁሉም ነዋሪዎች በእኩልነት የሚጠቀሙባትና የሚበለጽጉባት የጋራ መዲናችን ናት›› ሲሉ በአጽንኦት ተናገሩ፡፡ይህ የሁለቱም መሪዎች ንግግር የተደመጠው እንግዲህ የአቶ ለማ መገርሳ መንግሥት ‹‹አዲስ አበባን የኦሮሞ ለማድረግ እየሠራን ነው›› የሚል መግለጫ ካወጣ በኋላ ነው፡፡የሁለቱም መሪዎች ንግግር መቶ በመቶ ከክልሉ መግለጫ ጋር ይጣረሳል፡፡‹‹የኔ ብቻ ነች›› የሚልና ‹‹የጋራችን ነች›› የሚል የይዘት ልዩነት ያለው ነው፡፡

ሌላው በዚህ ቀን ሁለቱም መሪዎች በተለያየ መድረክ የተናሩት ንግግር ይዘት ‹‹ተክደናል›› የሚል መንፈስ ያለው መሆኑ ነው፡፡
‹‹ድል ብቻ የመጋራትና ሽንፈትን የመሸሽ አባዜ እንዲወገድ ልጆችን አስተምሩ፡፡ሰው ማለት ለችግርም ኃላፊነት የሚስድ ድልን በወጉ የሚጋራ እንጂ እፍታ እፍታውን እየላሰ ድስት ማጠብ ሲመጣ የሚሸሽ አለመሆኑን ልጆቻችሁን አስተምሩ››
ይህ ከጠቅላይሚኒስትር ዐቢይ ላይ የተወሰደ ንግግር ነው፡፡ ድል ሲመጣ አለሁ ያለ እፍታውን የላሰ አሁን ግን ክፉ ቀን ሲመጣ የሸሸ አንድ የሆነ አካል እንዳለ ለመጠቆም እንደነገሩን ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ይህ የእርሳቸው ንግግር በምክትላቸው እንዲህ ተደግፏል፡፡‹‹አንዳንዱ ዘመኑን በግሉ ቁመት ልክ ሰፍቶ ሲጎድል ግጭት ጠማቂ፣ሲሞላ መፍትሔ አፍላቂ ሆኖ የለውጡ አባዋራነትን ለብቻው ተከናንቧል፡፡››

የአቶ ደመቀ ንግግር ከአለቃቸው ትንሽ ጠንከር ያለ ይመስላል፡፡ዶ/ር ዐቢይ ድልን ስንቋደስ ከከረምን በኋላ ችግር ሲመጣ የሸሸ አለ ያሉት አካል፣በአቶ ደመቀ ችግር ጠማቂ ተብሎ እየተፈጠሩ ካሉ ቀውሶች ጀርባ ይሄው ኃይል እንዳለ በገደምዳሜ ነግረውናል፡፡ይህ ሁለቱን መሪዎች አንድ የከዳ አካል እንዳለ የሚጠቁም ግዙፍ መናበብ ነው፡፡ይሄ አካል ማነው የሚለው በቀጣይ ጊዜ የሚነግረን ይሆናል፡፡አብዮት ልጆቿን በልታም እንደሁ እንሰማለን፡፡

ጠቅላይሚኒስትር ዐቢይ በተለይ ለአንድነት ኃይሎች ‹‹የኢትዮጵያዊያን አንድነት ወዳጆች ዝምታ ጥቂቶች እንዲጮሁና ብቻቸውን እንዲደመጡ እያደረጋቸው ነው፡፡ዛሬ እደዋዛ ብቻቸውን የሚደመጡ ለትውልድ የማያስቡ የአንድነት ብርታት ያልገባቸው፣ከሱማሊያ እንኳ መማር ያልቻሉ ሰዎች ይዘውን እንዳይጠፉ ለኢትዮጵያ አንድነት በጋራ እንስራ›› ሲሉ ጥሪ ባቀረቡበት መድረክ፣‹‹የኔ ልጅ በርታ በርታ የሚሉ ቲፎዞዎች ስናሸንፍ እንጂ ስንሸነፍ ቀዳሚ ወቃሾች እነሱ ናቸው፡፡ጥቂቶች ብቻቸውን እንዳይደመጡ ብዙሃን ይተባበሩ›› ሲሉ በተከፋ ፊት እልህ በያዘው አንደበት ተናግረዋል፡፡

እንዲህ ያለው ነገር በርግጥ በኢሕአዴግ ቤት ምን እየተከናወነ ነው? ብለን እንድንጠይቅ የሚያደርግ ነው፡፡መካካድ ? መጠላለፍ? ወይስ ሌላ ? ጊዜ እስኪመልስልን ማኪያቬላዊውን አስተዳደር በማኪያቬላዊ ትንተና እንቆዝምበታለን፡፡

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close