Connect with us

Ethiopia

ለህዝብና ቤት ቆጠራ የመደባችሁትን በጀት የጌድዮን ህዝብ አብሉበት

Published

on

ለህዝብና ቤት ቆጠራ የመደባችሁትን በጀት የጌድዮን ህዝብ አብሉበት | ከአሳዬ ደርቤ

ለህዝብና ቤት ቆጠራ የመደባችሁትን በጀት የጌድዮን ህዝብ አብሉበት | ከአሳዬ ደርቤ
ርሃብ ስንት ቀን ይፈጃል?
እስኪ እናንተ ተናገሩ ተርባችሁ የምታውቁ
ከቸነፈር አምልጣችሁ ተርፋችሁ እንደሁ ሳታልቁ
ትንፋሽ ያላችሁ እንደሆነ- ያስችላችሁ እንደሁ ጥቂት
ቀጠሮ ይሰጣል እልቂት?
ስንት መዓልት? ስንት ሌሊት?…… ብሎ ነበር ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድን ወልዲያ ላይ የሆነውን አይቶ፡፡

ታዲያ ከ25 ዓመት በኋላ እኛው ባመጣነው ሰው ሰራሽ ርሃብ የጌድዮ ህዝቦች ለርሃብ ተዳርገው ወገኖቻቸውንና መንግስታቸውን ‹‹ቀጠሮ ይሰጣል እልቂት? ስንት መዓልት? ስንት ሌሊት?›› እያሉን ነው፡፡

እኛ ‹‹እንትና የማን ናት›› የሚል አጀንዳ ይዘን ስናመነዥክ እነሱ የሚበሉትን ጨርሰው የራሳቸውን ሰውነት እያላመጡ ነው፡፡

ታስታውሱ እንደሆነ የዛሬ ሶስት ዓመት አካባቢ ‹‹አንዲት ሴት የምትበላው ምግብ አጥታ በርሃብ ሞተች›› የሚል ዜና ሰምተን እንደ ጉድ ስናጮኽ ነበር፡፡ የምንቃወመው መንግስትም ‹‹በርሃብ የሞተ ሰው የለም›› ከሚል ማስተባበያ ጋር ‹‹የተከሰተውን ድርቅ ያለምንም የውጭ እርዳታ በራሴ አቅም እመክተዋለሁ›› ብሎ ሲንቀሳቀስ ነበር፡፡ እንዳለውም እርዳታ ሳይጠይቅ የድርቁን ጊዜ ማሻገር ቻለ፡፡

በዚህ ዓመት ግን ከአጀንዳችን ብዛት የተነሳ ጌድዮ ላይ በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የሚበሉት አጥተው በርሃብ ሲሰቃዩ የእኛም ጩኸት ሆነ የመንግስት ፍጥነት ቀሰስተኛ ሁኗል፡፡ እንደውም ከጌድዮ ህዝብ የምግብ እጦት ይልቅ የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ አጣዳፊ የሆነ ይመስላል፡፡

እርግጥ መንግስታችን በርካታ ነገሮች እንደተደራረቡበት እረዳለሁ፡፡ ሆኖም በርሃብ የሚንገበገቡ ዜጎችን ከመታደግ በላይ የሚቀድም ነገር ይኖራል ብዬ አልገምትም፡፡

ስለሆነም ከፍተኛ በጀት መድቦ ህዝብን እና ቤትን ከመቁጠሩ በፊት በዚህ ገንዘብ በቆሎ ገዝቶ የተራቡ ዜጎቻችን እንዲኖሩ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ትናንት በለገጣፎ ነገ ደግሞ በሱልልታ የተሰሩ ህገ-ወጥ ቤቶችን አፍርሶ ዜጎችን መጠሊያ-አልባ ከማድረግ ይልቅ ከየስፍራው የተፈናቀሉብንን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦች መታደግ ግድ ይላል፡፡

እየሆነ ያለው ግን ከዚህ በተቃራኒው ነው፡፡ ድንኳን ውስጥ ሰፍሮ ‹‹የመጠሊያና የምግብ ያለህ›› የሚል ህዝብ ይዘን ስለመናፈሻ እናወራለን፡፡ ጊዜ የማይሰጥ የርሃብ ሰቆቃ በላያችን ላይ ወድቆ ሳለ የከርሞውን አጀንዳ ወደ ዘንድሮ ገትተን ተጨማሪ ችግሮችን እንፈጥራለን፡፡ ‹‹ስሜ፣ ማንነቴ፣ ባለቤትነቴ፣ ክልልነቴ›› በሚሉ ሐይሎች እንታመሳለን፡፡

‹‹ደጅ ላይ የወደቁትን እንዴት እና የት እናስፍራቸው?›› ብሎ መምከር ሲገባ ‹‹አንትና ክልል ላይ የጨረቃ-ቤት ሰርተው የሚኖሩትን ዜጎች እንዴት እናፈናቅላቸው?›› ለሚለው አጀንዳ ቅድሚያ ተሰጥቶ የዶዘር ግዥ ሲፈጸም እንመለከታለን፡፡

እየተቀለበሰ ላለው ለውጥ፣ እየመሸከ ለሚገኘው ኢኮኖሚ፣ አንድነቷ እየተሸረሸረ ለምትገኘው አገር… መፍትሔ የሚሰጡ ሰዎች ተሸብበው፣ ዋነኛ መንስኤ በመሆን እኒህን ችግሮች የሚመጡት ግለሰቦች ‹‹የለውጡ ሐይሎች›› ተብለው አገሪቱንም ሆነ መንግስትን ሲያምሱት እያየን ግራ እንጋባለን፡፡ ሆኖም በዚህ ጉዳይ ላይ ‹‹ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ ነው›› እንደሚባለው ‹‹ሼማ ያደምቃል፣ ማቅ ይሞቃል የሚጠቅመውን ባለቤቱ ያውቃል›› ከማለት ውጭ ለጊዜው የምለው አይኖርም፡፡

ሆኖም ሁሉም የየራሱን ችግር እያንጠለጠለ ‹‹ቅድሚያ ለኔ›› እያለ መጮኹን ባይተውም…. መንግስት ግን የችግሮቻችንን ግዝፈት በጩኸታችን ልክ መስፈር የለበትም፡፡ ተርቦ ዝም ያለውን ህዝብ ችላ ብሎ፤ ጠግቦ ለሚጮኸው ቅድሚያ መስጠት አይኖርበትም፡፡ ለመጮህም መብላት ያስፈልጋልና ‹‹ስንዴ እሚደርስ ለፍስለታ፣ እኔ እምሞት ዛሬ ማታ›› እንደተባለው…. መንግስት የፍስለታውን ልማት ማቀዱን ትቶ የማታውን እራት ማድረስ አለበት፡፡

ህብረተሰቡ የሚሳተፍባቸውን የእርዳታ ማሰባሰቢያ መድረኮችን በማዘጋጀት፣ ለህዝብ ቆጠራና ለአንዳንድ ልማቶች የመደበውን በጀት በማዛወር የጌድዮን ህዝብ ከርሃብ ቸነፈር መታደግ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ደግሞ ከሚታየው ነገር ተነስተን ስንተነብይ ዛሬ በአንድ ቦታ የተከሰተው ርሃብ ነገ ላይ የሁላችንም እጣ-ፈንታ መሆኑ ስለማይቀር ካሁኑ ለተወሰነ ጊዜ ትተነው የነበርነውን የስንዴ ልመና የሚያቀላጥፍ ግብረ-ሃይል አቋቁሞ ወደ ለጋሽ አገራት መበተን ይኖርበታል፡፡

በሌላ መልኩ ግን እኛም ብንሆን ወገኖቻችንን በርሃብ እየተሰቃዩ ባሉበት ጊዜ ‹‹መንግስት እንዳረገ ያድርጋቸው›› ብለን ዝም ማለት የለብንም፡፡ ስለሆነም በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች የቻሉትን ያህል የሚለግሱባቸውን የእርዳታ ማሰባሰቢያ አማራጮች ዛሬውኑ በመዘርጋት ለወገኖቻችን ልንደርስላቸው ይገባል›› እላለሁኝ፡፡

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close