Connect with us

Art and Culture

ክቡር ጠ/ ሚር ላሊበላን ለመታደግ እያደረጉ ላለው ጥረት ምስጋናችን ከልብ ነው

Published

on

ክቡር ጠ/ ሚር ላሊበላን ለመታደግ እያደረጉ ላለው ጥረት ምስጋናችን ከልብ ነው

የእርስዎ ሀገር በዘመነ ላሊበላ ፈረንሳይን ተንጠራርታ ሳይሆን አቀርቅራ ማየት የምትችል የካህኑ ዩሐንስ የምናብ ምድር ነበረች፡፡ | ሄኖክ ስዩም /ተጓዡ ጋዜጠኛ/

በምክንያት አመሰግንዎታለሁ፡፡ ከዚህ የሚበልጥ የሚያስመሰግን ምክንያትም የለኝም፡፡ የላሊበላ ጉዳይ ትርጉመ ብዙ ነው፡፡ የተቀበልነውን ህያው ቅርስ አፍርሰን በቃል የምናወርሰው አፈ ታሪክ እንዳይኾን ማድረግ የሀገር ክብር ነው፡፡ ችግሩ ለብዙ መቶ ዓመታት የተጠራቀመ ነው፡፡ ላሊበላ የተሰራበትን ወርቃማ ዘመን ተከትሎ ድንቅ ነገር መስራት ምኞት ኾኖ ኖሯል፡፡

በጎንደር ከታየው የወርቃማ ዘመን የእጅ አሻራ ውጤት ባሻገር ብዙ ነገራችን ማፍረስ ነው፡፡ የቀደሙት የገነቡትን ማፍረስ፤
ላሊበላ በቆመች ሀገር ላይ ችግር የገጠመው ቅርስ ብቻ አይደለም፡፡ ትናንትን የምታፈርስ ሀገር ላይ የሚኖር ቅርስ በመሆኑ ተጎድቷል፡፡ ከምድር በታች የተጠበቡ አባቶች ቢወልዱንም ከምድር በላይ መሰልጠን አቅቶን ዛሬ መሬት የምንምሰው ለቀመበር ብቻ ሆኗል፡፡ እንዲህ ስንሆን የትካዜያችን መሸሺያ ላሊበላ ነው፡፡ እንዲህ ስንሆን ልባችን ወደ ደብረ ሮሐ ይሰደዳል፡፡ አክሱም ጫፍ የሰቀልነውን ክብር ላሊበላ አኑረን ወጥተን የገባን ነን፡፡

ላሊበላ ቅርስ ብቻም አይደለም፡፡ ዝናብና ማዳበሪያ ሳይል ወደ ውጪ ከምንልከው የግብርና ምርት የተሻለ የውጪ ምንዛሪ የምናገኝበት የበረከት ቅሪት ነው፡፡ ይሄንን ቅርስ የሚደርስለት መሪ አጥተን ነበር፡፡ ህዝብ አቅም አጣሁ ብሎ ነበር፡፡ የሚለመን ማን ነው የሚለው ጥያቄ ሆኖ ነበር፡፡ ነበሩን ሁሉ እልባት ለመስጠት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እያደረጉት ያለውን ጥረት እጅ ነስቼ የማመሰግነው ነው፡፡

መሪ ሆኖ ለማኝ መሆን ውርደት ነው፤ ቢሆንም ለሀገር ነው፡፡ የእርስዎ ሀገር በዘመነ ላሊበላ ፈረንሳይን ተንጠራርታ ሳይሆን አቀርቅራ ማየት የምትችል የካህኑ ዩሐንስ የምናብ ምድር ነበረች፡፡ ዛሬ የትናንት የኩራት ታሪኳን ትውልድ እንዲኮራበት ለማድረግ እጇን ወደ ፈረንሳይ የዘረጋች ሀገር ሆናለች፡፡

የፈረንሳይ መንግስት በጎንደርና በሀረር የሚገኙ ቅርሶችን ለመታደግ ቀና ልቡ አሳይቶ ለፍሬ ያበቃ መንግስት ነው፡፡ ላሊበላን ለመታደግም ስላሳየው መልካም ፍቃድ ምስጋናችን ወደር የለውም፡፡

እነኚህ ቅርሶች የየዘመናቱ ፖለቲካ የየታሪክ ምዕራፋችን ሽኩቻዎች ትኩረት ነፍገዋቸው እዚህ የደረሱ ናቸው፡፡ ጥሩ ቀን ሲመጣ ከጥሩ ነገራችን እንማር ብንል እንኳን ጥሩው ነገራችን እጃችን ላይ ከሌለ ከምን እንነሳለን? እንደላሊበላ ያሉ ቅርሶች መነሻችን ናቸው፡፡

የፈረንሳዩ መሪን በጥንታዊቷና ታሪካዊቷ ከተማ ለመቀበል የተዘጋጀው ሥነ-ሥርዓትም የላሊበላን ከተማ ክብር የጠበቀ ነው፡፡ የወዳጁ ሀገር መሪ እንደ ጥንቱ ዛሬም ልቡ እንግዳን ለመቀበል ራሱን እንደ አብረሐም ያዘጋጀውን ህዝብ ማየት መቻላቸው አጋርነታቸውን ከልባቸው እንዲያደርጉት ያግዛቸዋል፡፡ ከምንም በላይ ግን መሪዎች በመጡ ቁጥር ላሊበላን አንድ ነገር እናድርገው በሚል ልመና ሳይለያቸው ለቅርሱ ህልውና የሚደክሙትን ጠቅላይ ሚኒስትር ሳላደንቅም ሆነ ሳላመሰግን አላልፍም፡፡

የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ

ኢትዮ ጵያን የተመለከቱ የተለያዩ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዘኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close