Connect with us

Ethiopia

ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ፣

Published

on

ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ፣

የአርበኞች ግንቦት 7 ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መጋቢት 3 ቀን 2011 ዓም በሀገሪቱ ያለውን የለውጥ ሂደትና እያጋጠሙ ያሉትን ተግዳሮቶች እንዲሁም ድርጅቱ እራሱን አክስሞ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በመዋሀድ በቅርቡ የሚፈጠረውን አዲስ ፓርቲ በተመለከተ እየተሰሩ ያሉትን ሥራዎች ባጠቃላይ ለመገምገም አስቸኳይ ስብሰባ አድርጓል። ሥራ አስፈጻሚው ብዙውን ጊዜውን ያጠፋው አሁን በሀገሪቱ እየታዩ ያሉትንና በዚህ ከቀጠሉ የለውጡን ሂደት ፍጹም ሊያሰናክሉ ይችላሉ ብሎ ያመናቸውን የተለያዩ ኩነቶች በጥልቀት በመገምገም ነበር።

በትግራይና በአማራ ክልል ያለውን አደገኛ ውጥረትና የጦርነት ነጋሪት፤ በአማራ ክልል ውስጥ በቅማንትና በአማራ ማንነት ስም የደረሰውንና እየደረሰ ያለውን የንጹሀን ዜጎች ሕይወት መጥፋትና የብዙ ዜጎቻችንን መፈናቀል፤ በቤንሻንጉል፤ በሶማሊያ ክልል፤ ዘርን መሰረት ባደረገ ግጭት የደረሰው የንጽሀን ዜጎች ሕይወት መጥፋት፣ ንብረት መውደምና መፈናቀል፤ በደቡብ ክልል በተለያዩ ቦታዎች ላይ ከማንነት ጋር በተያያዘ (ለምሳሌ በቅርቡ በጌዲኦ ወገኖቻችን ላይ የደረሰውን መፈናቀል፤ በሀዋሳ ከተማ በተደጋጋሚ የታየው አሳፋሪ የስርአተ አልበኝነት ድርጊትና ይህም በከተማው ነዋሪ መሀከል የተፈጠረው ግጭት…ወዘተ) በየጊዜው የሚታየው የሰብአዊ መብት ረገጣና ግጭት እንዲሁም በሰላማዊ የፖለቲካ ሂደት ላይ በየጊዜው የወረዳና የዞን መስተዳደሮች እየፈጠሩ ያሉት የማሰናከል ስራ፤ በኦሮሚያ የተለያዩ አክራሪ ኃይሎች እየፈጠሩ ያለው አለመረጋጋትና እነኝህ አክራሪ ኃይሎች በሚያነሷቸው አጀንዳዎች በሕዝቡ ሰላምና በክልሉ መረጋጋት ላይ እየፈጠሩ ያለው ችግር፤ እንዲሁም እነኝሁ አክራሪ ኃይሎች አዲስ አበባን በተመለከተ የሚሰጧቸዉ ፍጹም ሀላፊነት የጎደላቸው መግለጫዎች በአዲስ አበባም ሆነ በኦሮሚያ ክልል መስተዳደር ላይ እየፈጠሩ ያለው ጫና፤ በዚህም ጫና በመወጠር፣ በኦሮሚያ ክልል መንግሥት የተሰጠው መግለጫ፤ ይህ መግለጫ በአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ ላይ የፈጠረው የፍርሀት ድባብና ይህንን የፍርሀት ድባብ በመጠቀም በከተማው ውስጥ ያሉ ወጣቶች “ልንወረር ነው” የሚል ጭንቀት ውስጥ መግባት፤ ከዚያም የመገፋት ስሜት የሚፈጥረው እልህ ውስጥና ሲከፋም እራስን የመከላከል የደመነፍስ ስሜት ውስጥ ለማስገባት የሚደረጉ ሀላፊነት የጎደላቸውን እንቅስቃሴዎችና የሶሻል ሚዲያ ጦርነቶች በጥሞና መርምረናል።

እነኝህን የተለያዩ ኩነቶች ለየብቻቸው ለምንና እንዴት ተፈጠሩ ከሚለው ባሻገር እነኝህ ኩነቶች በጋራ የሚሰጡትን የሀገሪቱን ተጨባጭ ስእልና ተደምረው በለውጡ ሂደት ላይ እየፈጠሩ ያለውን ድባብ በተቻለ መጠን ከስሜት በመውጣት ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ለመረዳት ሞክረናል። ይህ አጠቃላይ ሁኔታ በቶሎ መፍትሄ ካልተፈለገለትና በዚሁ እንዲቀጥል እድል ከተሰጠው የለውጡን አቅጣጫ ከማስለወጥ ባሻገር በሀገራችን ላይ ሊያመጣ የሚችለውን አደጋ በአንክሮ ተመልክተናል።

ሀገሪቱ የነበረችበት ፍጹም አምባገነናዊ ሥርዓት ከከተታት እጅግ አስቸጋሪ ያለመረጋጋት ሁኔታ ለጊዜውም ቢሆን ወጥታ፤ ከዚህ በፊት እንዳለፍንባቸው ሁሉንም ነገር ስር ነቀል በሆነ አብዮታዊ ሂደት መፍታት የሚያስከትለውን አስከፊ ውጤት በመረዳት፤ ፍጹም አሸናፊና ተሸናፊ በማይኖርበት ሁሉንም ባቀፈ ለዘብተኛ የሪፎርም ሂደት ወደ እውነተኛና ዘላቂ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መሄድ ይቻላል በሚል በከፍተኛ ተስፋ ከ11 (አሥራ አንድ) ወራት በፊት የለውጥ (ሪፎርም) ሂደት መጀመሩ ይታወቃል።

ይህ የለውጥ ሂደት የፈጠረው ተስፋ ግን ቀስ በቀስ ጥግ በያዙ በከረሩና የራስንና የተወሰነ ቡድንን ፍላጎት ብቻ ባስቀደሙ ኃይሎች ግፊትና ጫጫታ ማህበረሰባችንን ወደ ጭንቀት፤ አልፎም ዋናውንና ዘላቂውን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሊያሰናክል ወደሚችል አደገኛ አቅጣጫ እየገፉት ይገኛሉ። እንዲህ አይነት ኃይሎች የለውጡን አጀንዳ ከተቆጣጠሩት ከዚህ በፊት ሀገሪቱ አግኝታ የነበረችውን የለውጥ እድሎች እንዳመከንናቸው ይህንንም የለውጥ እድል አምክነን ሀገራችን ልትወጣ ወደማትችለው ቀውስ ልንከታት እንችላለን የሚል ከፍተኛ ስጋት አድሮብናል።

ሥራ አስፈጻሚው ይህን የለውጥ ሂደት ለማደናቀፍ የሚሞክሩ ኃይሎችን ስሜትና ፍላጎት ለመረዳት ሞክሯል። በአንድ በኩል ከዚህ በፊት የመንግሥት ስልጣንን በመያዝ ሲያገኙት የነበረው ጥቅም እንዳይቀርባቸው የሚሞክሩ ወይንም ለውጡ ከዚህ በፊት ለሰሯቸው በደሎች ቂም መወጫ ይሆናል ብለው የሚሰጉና በየክልሉ በተለያየ የስልጣን ደረጃ ላይ የሚገኙ ጸረ ለውጥ ኃይሎች እንዳሉ ተገንዝበናል።

በሌላ በኩል ደግሞ ይህ አገራችን የተያያዘችዉ የለውጥ ሂደት ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚሆንና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በእኩልነት የሚያይ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመፍጠር መሆኑን በመዘንጋት የራሳቸውንጠባብ ቡድን ፍላጎት ማሟላትን ዋና አላማቸው አድርገው፤ የመንግሥት ስልጣንን የሁሉም ዜጎች ፍላጎት ማስጠበቂያና መብት ማስከበሪያ መሳሪያ ሳይሆን በቡድን በቡድን ለዘውጌ ባለተራው የሚታደልና በዚህም ሥልጣን ባለ ተራው የፈለገውን የሚያደርግበት አድርጎ በመውሰድ “ተራው የኛ ነው” በማለት “የድርሻቸውን” ለመውሰድ የቋመጡ፤ ወይንም ሥልጣን በነኝህ ቡድኖች መካከል በሚደረግ ድርድር የሚታደል ስለሚሆን “የድርሻችንን” ለማግኘት ራሳችንን ለዚያ ማዘጋጀት አለብን ብለው የሚያስቡ ናቸው።

ሶስተኛው አይነት አደናቃፊ ደግሞ ይህ የተያዘው የለውጥ ሂደት ሳይሆን ያለፉት 28 አመታት ውጤት የሆነና “የለውጥ ኃይል” የሚባለውም ያንን ሥርዓት በለውጥ ስም በብልጣብልጥነት ለማስቀጠል የሚሞክር ስለዚህም ሁኔታው ሲረጋጋለት የቀድሞውን ሥርዓት ምናልባትም በአዲስ ፊቶችና በአዲስ የዘውጌ ኃይል የበላይነት መልሶ የሚያስቀምጥ ስለሆነ የለዉጥ ኃይሉ እንዳይረጋጋ ማድረግ ትክክለኛ የትግል እስትራቴጂ ብቻ ሳይሆን በዚህ ሂደት ሁኔታዎች ወደ በፊቱ ይዞታቸው መመለሳቸው የማይቀር ስለሆነ ለውጥ አለ ብሎ ራስን በየዋህነት ከማሞኘት እራስን ለመጪው ግጭት/ትግል ማዘጋጀት ተገቢ ነው ብሎ የሚያምን ኃይል ነው።

የእነኝህ ሶስት ኃይሎች ባህሪይና ድርጊት አገራችን ዉስጥ እውነተኛ ዴሞክራሲዊ ሥርዓት ለመገንባት የሚደረገዉን ጥረት ለከፍተኛ ፈተና ዳርጎታል። እነዚህ ኃይሎች ለውጡን ለማደናቀፍ የሚፈልጉበት የውስጥ ግፊታቸው የተለያየ ቢሆንም ሶስቱም እርስ በርሳቸው ይመጋገባሉ። በለውጡ ሂደት የሚመጡ ማናቸውንም አይነት እንቅፋቶች በማጦዝ ለውጡን ለመጠምዘዝ ይሞክራሉ። የሀሰት ወሬዎች ይፈበርካሉ ወይንም ግማሽ እውነት ያባዛሉ፤ ሆን ብለው ጠላት ይፈጥራሉ፤ የኔ የሚሉት ቡድን ወይንም ማህበረሰብ “ተጠቅቻለሁ” የሚል የቁጭት ስሜት ውስጥ እንዲገባ የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ በዚህም ሂደት ሊሰማቸው የሚችልን ደመ ሞቃት ወጣት ኃይል በስሜት እየቀሰቀሱ በዙሪያቸው ይሰበስባሉ፤ ግጭት ውስጥ እንዲገባም ይገፋፉታል። አንዳቸው ሌላኛውን በስሜት ሊያነሳሳ የሚችል ዘለፋ ይረጫሉ ወይንም ለማስፈራራት ወይንም አንገት ለማስደፋት ይሞክራሉ። ይህ የመጠፋፋት ሂደት ግን እነሱ እንደሚያስቡትና እንደሚመኙት አንዱን አሸናፊ ሌላውን ተሸናፊ አድርጎ የሚጠናቀቅ አይሆንም። የነኝህ ኃይሎች የጋራ እንቅስቃሴ ለውጡን ለመቀልበስ ቢችል እንኳን የሚገኘው ውጤት ሁሉንም የሚያጠፋና እግረመንገዱንም ሀገሪቱን በሙሉ ጠራርጎ ሲኦል የሚከት መሆኑን ለመገንዘብ ነብይ መሆን እይጠይቅም። በየቦታው በእነኝህ ኃይሎች የሚተነኮሱ ግጭቶች የሚያስከትሉትን የመቶዎች እልቂትና የሚሊዮኖች መፈናቀልን ባይናችን እያየነው ያለው ነውና!!!

በዚህ ሁኔታ እንደ ድርጅታችን ያሉ ለውጡ እውነተኛ አላማው የሆነውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በመፍጠር እንዲቋጭ የሚፈልጉ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ ለውጡን የሚደግፉ የመንግሥት ኃይሎች፤ የሲቪክ ማህበራት፤ ምሁራን፤ ግለሰቦች፤ ምን ማድረግ አለባቸው? ከዚህ አኳያ በቅርብ ጊዜ ታሪካችን ካለፉትና ከመከኑት የለውጥ ሙከራዎች ምን እንማራለን? የመጀመሪያውና በጣም ወሳኝ የሆነው የቅርብ ጊዜ ታሪካችን ትምህርት፤ የለውጥ ሂደቱን አጀንዳ እንደነኝህ አይነት በርጋታ ማሰብ የማይችሉ፤ በምክንያታዊ ትንተና ሳይሆን በስሜት የሚጋልቡ ዋልታ ረገጥ አክራሪ ኃይሎች የለውጥ አጀንዳውን ከተቆጣጠሩት ጥፋት እንጂ ምንም በጎ ነገር ይመጣል ብለን መጠበቅ እንደማንችል ነው።

በ1966ቱ የለውጥ ጊዜ አጀንዳውን የተቆጣጠሩት አክራሪና ጥራዝ ነጠቅ የሶሻሊስት እምነት ተከታዮች ምንም አይነት ሌላ አማራጭ አናይም፤ “ንጹህ እምነታችንን” የሚበርዝ ማናቸውም ለዘብተኛ አመለካከት ከጠላትም በላይ ጠላት ነው ብለው ፈርጀው በውሀ ቀጠነ እርስ በርሳቸው ሲራኮቱ ደጋፊዎቻቸውን አስበልተው፤ ብዙ እናቶችን ማቅ አስለብሰው፤ ሀገሪቱን ለመከራ ዳርገዋት አለፉ። በነኝህ ጽንፈኛ አመለካከት የተለከፈው ባለጊዜ ወታደራዊ ኃይል ለሁሉም የተለያየ አመለካከት ጉልበትን እንደመፍትሄ ይዞ ሲገፋ አገሪቱን በወጣቶች ሬሳ ሞልቶ፤ ኢኮኖሚውን አድቅቆ፤ በተረኛው ባለጉልበት ተሸንፎ በውርደት ለቀቀ። ከዚህ አመለካከት ያልወጡና ይበልጡንም ማህበረሰቡን በዘር በመከፋፈል የስልጣን ጊዜያቸውን ለራሳቸው ጥቅም ለማዋል የተንገበገቡ ኃይሎች ከየትኛውም በኩል የሚመጣን ለዘብተኛ አካሄድ ገፍተውና ያለኛ ለሀገርና “ለብሄር ብሄረሰቦች” የሚያስብ የለም ብለው የዘረጉት የዝርፊያ ሥርዓት ራሳቸውን ጠልፎ ጥሎ እዚህ አይነት ምስቅልቅል ውስጥ ሀገሪቷን ከተዋት የራሳቸውን “የብሄር ምሽግ” ቆፍረው ተቀምጠዋል። የተለያዩ ጥቅሞችና ፍላጎቶች ያሉበትን የኛን አይነት ድሀ ሀገር በአንድ አይነት አክራሪ አመለካከት ብቻ ወጥረን ማህበረሰቡን በሰላም እናኖራለን ማለት በፍጹም የማይቻል ቅዠት መሆኑን ይኸው የራሳችን ሀገር የቅርብ ጊዜ ታሪክ ትምህርት ሊሆነን ይገባ ነበር። ይህ ለውጥ እንዲሳካ ከተፈለገ ለዘብተኛ ኃይሎች የለውጡን አጀንዳና ሂደት መቆጣጠር መቻል አለባቸው።

ለውጡን የሚደግፉና ግቡን እንዲመታ የሚፈልጉ የፖለቲካ ድርጅቶች ከጊዜያዊ የፖለቲካ ጥቅም ይልቅ ለሀገር መረጋጋትና ለእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መመስረት ተሰባስበው መስራት ይጠበቅባቸዋል። የስልጣን ትግሉን ሀገር ከተረጋጋ በኋላ በሚደረገው ምርጫ ይደርሱበታል። በየጊዜው ባክራሪዎች በሚነሳ ጫፍ የረገጠ አጀንዳ ተተብትበው እንዳይወድቁ መጠንቀቅ አለባቸው። የሲቪክ ማህበረሰብ አባላት የሀገራቸውን ጉዳይ ለጥቂት አክራሪዎች አሳልፈው ሳይሰጡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምስረታ ከልባቸው መስራት አለባቸው። ሁኔታው መስመር እየሳተ ሲሄድ ከዳር ቆመው ሊመለከቱ በፍጹም አይቻላቸውም። እነሱንም ያጠፋቸዋልና! ለውጡን ከዳር ለማድረስ ለጊዜው የመንግሥትን ስልጣን የያዙ “የለውጥ ኃይሎች” ባክራሪ ኃይሎች ጩኅት ሳይረበሹና እነሱን ለማማለል በሚል በምንም አይነት ከዋናው የሀገር ሰላም ማስጠበቅና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግር ሀላፊነታቸው ሳይዘናጉ ለውጡን በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲሄድ ሁኔታውን ማመቻቸት ይጠበቅባቸዋል። እነኝህ ኃይሎች ከዚህ ሰፊ የጋራ አጀንዳ ውጭ ማንኛውንም የተለየ ቡድን የሚደግፉ ወይንም የራሳቸውን የወደፊት የፖለቲካ እድል እያሰሉ የሚሄዱ ከመሰሉ ማህበረሰቡ በሰፊው የሰጣቸውን አመኔታ ያጡና ሀገሪቱን ለአደጋ እንደሚዳርጓት መገንዘብ ይኖርባቸዋል፤ ይህንንም በተግባር ማሳየት ይጠበቅባቸዋል። የሀገሪቱ ምሁራን በተረጋጋና ምክንያታዊ በሆነ ትንተና የለውጡን ሂደት መዳረሻና ሊገጥሙት የሚችሉትን ተግዳሮቶች ሳይታክቱ ማህበረሰቡን በማስተማር ለውጡ አቅጣጫውን እንዳይስት ከልባቸው መስራት አለባቸው። የሚዲያ አካላትና አርቲስቶቻችን ያለእውነተኛ ዴሞክራሲ ሙያቸው ራሱ ትርጉም የሌለው እንደሆነ አውቀው ለውጡ እዚያ እንዲደርስ መግፋት፤ የአክራሪ አስተሳሰቦችን አደጋ ማጋለጥ ይጠበቅባቸዋል። እንዲህ አይነት የለዘብተኛ ኃይሎች ትብብርና በለውጡ ሂደት የሚኖራቸዉ ቀጥተኛ ተሳትፎ ብቻ ነው ይህንን ለውጡ የተጋረጠበትን አደጋ መከላከልና ሁላችንም የደከምንለትን እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እውን ሆኖ ማየት የምንችለው።

አርበኞች ግንቦት 7 ይህ ለውጥ የታለመለትን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መስርቶ እንዲቋጭ ከመፈለግ ባሻገር በአሁኑ ጊዜ ምንም ሌላ አላማ የለውም። የምንሰራው የድርጅት ሥራ ኢላማው ዘላቂ ዴሞክራሲያዊ ሥርአትን በጠንካራ መሰረት ላይ ለማቆምና የሀገሪቷን ስትራቴጂካዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ያለመ ነው። እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በጠንካራ መሰረት ላይ መቆም የሚችለው ሁሉንም ዜጎች በእኩልነት በሚያይ፤ ዜግነትን መሰረት ባደረገ ፖለቲካ ነው ብለን ከልባችን እናምናለን። ይህንንም ለሁሉም ህዝባችን ያለምንም መታከት እናስተምራለን። ይህን እምነታችንን ግን በማንም ላይ በጉልበት ለመጫን አንሻም። በሰላማዊ መንገድ በሚደረግ የሀሳብ ትግልና፤ በመጨረሻም በነጻና ፍትሀዊ ምርጫ ማህበረሰቡ የወሰነውን ውሳኔ ለመቀበል ምንም ችግር የለብንም። ይህ እንዲሆን በመጀመሪያ ሰላም እንዲሰፍን ይገባል። ያለሰላም ፖለቲካ የለም። ያለ ሰላም ዴሞክራሲ የለም። ያለሰላምና እውነተኛ ዴሞክራሲ ደግሞ ሀገር አይኖርም።

ሰላምና እውነተኛ ዴሞክራሲ ብሎም ሀገር እንዲኖር፣ ከወረዳ ጀምሮ እስከ ከፍተኛው የመንግስት የሥልጣን እርከኖች ድረስ ያሉት የሃላፊነት ቦታዎች በራሱ በሕዝቡ በተመረጡ ሃላፊዎች መያዝ ይኖርባቸዋል ብሎ አርበኞች ግንቦት 7 ከልብ ያምናል። ክልሎች በክልሉ ሕዝብ በተመረጡ መሪዎች፤ ከተሞች በራሱ በከተማው ሕዝብ በተመረጡ ከንቲባዎች (የፌደራሉ ከተማ የሆነችውን አዲስ አበባን ጨምሮ)፤ ወረዳዎች በራሱ በወረዳው ሕዝብ በተመረጡ አስተዳዳሪዎች፤ ቀበሌዎችም የቀበሌውን ጉዳይ በተመለከተ የሚመሯቸውን ሰዎች እራሳቸው የቀበሌው ነዋሪዎች የሚመርጡበት ሁኔታ ሲኖር ብቻ ነው እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ፌደራሊዝም ሊኖር የሚችለው ብለን እናምናለን። ከዚህም ባሻገር የፌደራል መንግሥቱ ባጠቃላይ የሀገሩ ሕዝብ መመረጥ ያለበት ብቻ ሳይሆን በሕግ የተቀመጠለትን ሥልጣን በብቃት መተግበር የሚችል ጠንካራ ፌደራል መንግሥት መሆን አለበት ብለን እናምናለን። ድርጅታችን ይህን እምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ በየወረዳው ሕዝብን የማሰባሰብ የማሰልጠንና የማደራጀት ሥራ ላይ ያለውን አቅም በሙሉ በመጠቀም እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። የዚህ እንቅስቃሴ ሂደት ሌሎች መሰል ሀገራዊ ድርጅቶችን አካቶ በሚቀጥሉት ጥቂት ሳምንታት ከወረዳ ጀመሮ በሚዋቀር በአዲስ ሀገራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ምስረታ የሚጠናቀቅ ይሆናል።

በመጨረሻም የተለያዩ፣ የሀገርና የሕዝብ፣ ደህንነት፣ ፍላጎትና ጥቅም፣ ግድ የማይሰጣቸው ቡድኖች፣ በየግዜው የሚቀስቅሱት ግጭትና አለመረጋጋት ከቁጥጥር ውጭ ቢወጣና የተጀመረውን የሀገር ማዳን ለውጥ መስመሩን ቢስት፣ የሚፈጠረው እጅግ አደገኛ ሀገራዊ ሁኔታ ማንም አሸናፊና ተሸናፊ የማይሆንበት ምድራዊ ሲኦል እንደሚፈጥር አርበኞች ግንቦት 7 ቅንጣት ያህል ጥርጥር የለውም። ስለዚህ ማናቸውም የህብረተሰብ ክፍል፣ ድርጅት፣ ቡድንና ግለሰብ፣ የጽንፈኛ ቡድኖችና ግለሰቦች ለሚፈጥሩት ጊዚያዊ የግጭት ስሜት ሰለባ እንዳይሆንና እንዲያውም በሚቻለው ሁሉ የለውጡን ሂደት በመደገፍ፣ ኢትዮጵያን እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሀገር ለማድረግ በሚደረገው ጥረት በሚቻለው ሁሉ እንዲሳተፍ ፣ አርበኞች ግንቦት 7 ወገናዊ ጥሪውን ያስተላልፋል።

ኢትዮጵያ ለዘላላም ትኑር፣
አርበኞች ግንቦት 7፣ የአንድነትና የዴሞክራሲ ንቅናቄ፣
መጋቢት 2011 ዓም

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close