Connect with us

Ethiopia

የዘረኞች አጀንዳ ጣራ መንካት እና የጠ/ሚኒስትሩ ዝምታ

Published

on

የዘረኞች አጀንዳ ጣራ መንካት እና የጠ/ሚኒስትሩ ዝምታ | በጫሊ በላይነህ

የዘረኞች አጀንዳ ጣራ መንካት እና የጠ/ሚኒስትሩ ዝምታ | በጫሊ በላይነህ

ባለፈው አንድ ዓመት ለውጡ ይዟቸው የመጣቸው መልካም ዕድሎች ብዙ ናቸው፡፡ ጉድለቶችም እንዲሁ፡፡ ከጉድለቶች ሁሉ ግን የአክራሪ ብሔርተኝነት ምቹ ጫካ አግኝቶ ጠብና ቁርሾ ወደመፍጠር መሸጋገሩ በአስከፊነቱ የምንጠቅሰው ነው፡፡

ከቅርብ ወራት ወዲህ በአንዳንድ አክራሪ ብሔርተኞች እየተከናወኑ ያሉት ተግባራት ለኢትዮጽያ ብቻ ሳይሆን እንጠቅመዋለን ለሚሉት ብሔርም የሚጠቅም አይደለም፡፡ “ሁሉም ነገር የእኛ ነው” የሚለው የአክራሪ ብሔርተኝነት አጀንዳ እነጠ/ሚ ዐብይ ይዘውት ከተነሱት የኢትዮጽያዊነት ትርክት ጋር ጨርሶ አብሮ የሚሄድ አይደለም፡፡

“እኛ እና እነሱ” የሚለውም ትርክት የራስን ብሔር ከፍ አድርጎ የሌላውን በማኮሰስና በማሳነስ እንዲሁም በጠላትነት በመፈረጅ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ በአሳሳቢነቱ በርካታ ኢትዮጽያውን እያወገዙት ነው፡፡ አገር እያስተዳደረ ያለ ፓርቲ ደጋፊ ነን፣ የለውጡ ሞተር እኛ ነን የሚሉ ግለሰቦች በትንንሽ አጀንዳ ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጠር ላባቸውን እየዘሩ ነው፡፡

የሰሞኑ የኮንደሚኒየም አጀንዳ የዚሁ አካል አድርጎ መውሰድ ይቻላል፡፡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትም የእነዚህን ነውጠኞች አጀንዳ ተረክቦ ማራገብ መጀመሩ ብዙዎችን አስደንግጧል፡፡ ሠላማዊውን የአዲስ አበባ ሕዝብ ለተቃውሞ እየገፋውም ይገኛል፡፡

እነዚህ ኃይሎች ምንድነው የሚፈልጉት? የለውጥ አመራሩ ሁለት መንፈቅ ሳይሞላው፣ በሌላ አነጋገር በሁለት እግሩ እንኳን መሬት መርገጥ ሳይጀመር እንዲህ አይነት የቁርሾ አጀንዳ ለምን ማንሳት ፈለጉ? የሚሉ ጥያቄዎች እንደተጠበቁ ሆነው የለውጥ አመራር ኃይሉ ይህን የጠባብነት ትርክት ፊት ለፊት ወጥቶ መጋፈጥ አለመፈለጉ የህዝብን እምነት እየሸረሸረበት ስለመሆኑ አስረጂ አያስፈልግም፡፡ ትላንት ሆ ብሎ ለለውጥ ኃይሉ ድጋፉን የሰጠው ሕዝብ አሁን ደግሞ ቆም ብሎ ምን እየተካሄደ ነው ብሎ መጠየቅ ጀምሯል፡፡

በተለይ ከኦሮሞ አክራሪ ብሄርተኝነት ጋር ተያይዞ ሁሉም ነገር የእኛ ነው የሚለው የጠባቦች መንገድ የታዘቡ ብዙ ወገኖች አፍ አውጥተው ትላንት በደገፉዋቸውን በእነጠ/ሚ ዐብይ የመከዳት ስሜት ውስጥ ከቷቸዋል፡፡ አንዳንዶች እነዐብይ ድብቅ አጀንዳ አላቸው እያሉም ነው፡፡ ከክስተቶቹ ጋር ተያይዞ እጅግ ብዙ ጥያቄዎች ሕዝቡ ውስጥ ተፈጥረዋል፡፡

በሌላ በኩል የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች አንዱ የሆነው ህወሓት እንዳኮረፈ ነው፡፡ ብአዴን/አዴፓ ከህወሓት ጋር ለጦርነት የሚፈላለጉበት አውደ ውስጥ ተዘፍቋል፡፡ ወዲህ መለስ ሲል ደግሞ በአዲስአበባ ከተማ በበቂ ሁኔታ አልተወከልኩም ከሚል ጀምሮ በኦዴፓ እየታዩ ያሉ አካሄዶች በብልጣብልጥነት እስከመፈረጅ ደርሷል፡፡ ደኢህአዴን በክልል ይገባል እና በማንነት ይከበርልን ጥያቄ ተቋስሎ እርስ በርስ ሊበላላ ጫፍ ላይ ቆሟል፡፡ ማዕከላዊ መንግሥት ይህ መደፍረስ እምብዛም ያስጨነቀው አይመሰልም፡፡ ዶ/ር ዐብይ አሕመድ ይህን ከባድ ውጥረት ለመፍታት ወይ የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ጉባዔ ጠርተው አልተወያዩም፡፡ ወይንም ችግር የሚፈጥሩ ወገኖችን ሲያስታግሱ አልታዩም፡፡

ጠ/ሚኒስትሩ በአንድ ወቅት “የድብቅ ፖለቲካ ከአሁን በኃላ በቃ፡፡ የስራ አስፈጻሚው ውሳኔ ለሕዝባችን ቶሎ መስማት አለበት፡፡ ከሕዝባችን የሚደበቅ ነገር የለም” ብለው ነበር፡፡፡ ግን በተግባር ለመተርጎም ተቸግረው እያየናቸው ነው፡፡ አገር እንዲህ በተወጠረችበት ጊዜ እንኳን ፕረስ ኮንፈንስ አዘጋጅቶ ነገሮችን ግልጽ ለማድረግ አቅም አላገኙም፡፡

እናም በዝምታ አገር መምራትን የመረጡ መስለዋል፡፡እዚህም እዚያም መካረሮች ጫፍ ደርሰው አገር ሊያፈርሱ ነው በሚባልበት በዚህ ጊዜም በዝምታቸው ጸንተዋል፡፡ ምናልባትም ችግሮቹ በገጠመኝ እንዲፈቱ የተውአቸው መስለዋል፡፡ ግን እስከመቼ?

አሁንም ቢሆን ሐዝብ ወጥተው እንዲናገሩ፣በአክራሪ ብሔርተኝነት ላይ ያላቸውን ግልጽ አቋም እንዲናገሩ፣ በተግባርም እርምጃ እንዲወስዱ ይፈልጋል፡፡ በአጭሩ ዝምታው ይብቃ፣ የጥቂት አክራሪዎች መፈንጫ መሆን ይብቃ፣ ሕግና ሥርዓት ይከበር እያለ ነው፡፡ ይህን ጥያቄ ዶ/ር ዐብይ እና የሚመሩት ኦዴፓ/ኢህአዴግ መቼ ሊመልሰው አስቦ ይሆን?

የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙኢትዮ ጵያን የተመለከቱ የተለያዩ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዘኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close