Connect with us

Ethiopia

የዶ/ር አምባቸው መንገድ! | በሬሞንድ ኃይሉ

Published

on

የዶ/ር አምባቸው መንገድ! | በሬሞንድ ኃይሉ

ዳንዲ አምባቸው: የዶ/ር አምባቸው መንገድ! | በሬሞንድ ኃይሉ

ስሙን እንጅ ግብሩን ያልቀየረው አዴፓ አምባቸው መኮንንን(ዶ/ር) የክልሉ ርዕስ መስተዳደር አድርጎ ከሾመ ቀናት ተቆጥረዋል፡፡ የአቶ ገዱ አንዳርጋቸው ስንብት ምክንያቱ በውሉ ባይገለጽም የአምባቸው(ዶ/ር) መሾም ግን የሚጠበቅ መሆኑ አያከራክርም፡፡

አንደበተ ርዕቱ የሚባለው አምባቸው በቀድሞው አመራሮች ላይ የሰላ ትችት ያቀርብ የነበረ ሰው እንደመሆኑ መጠን የለውጡ አሰላለፍ ወደፊት እንደሚያመጣው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ እንደ ግለሰብም ሆነ እነ እንደ ህዝብ በቀድሞው አመራር የአማራ ህዝብ ተብድሏል ብሎ ያምናል የሚባለው አምባቸው ከቀድሞው ርዕሰ መስተዳድር አያሌው ጎበዜ ጋር በነበረው አለመግባባት በድርጅቱ ውስጥ መነገጋሪያ እንደነበር ይነገራል፡፡

አንድ የአዴፓ አመራር እንዳጫወቱኝ የአቶ አያሌውና የአምባቸው (ዶ/ር) የወቅቱ አለመግባባት መሰረታዊ መነሻው አምባቸው ለትምህርት ወደ እንግሊዝ ለመሄድ ቢፈልግም መከልከሉ ነበር፡፡ አቶ አያሌው በርካታ የትምህርት ዕድል የሚፈልጉ ሰዎች ባሉበት በዚህ ወቅት በድጋሚ አንተን ወደ ውጭ አንልክም ማለታቸው ያሰቆጣው የአሁኑ ርዕሰ መስተዳዳር ለቀድሞው አመራር ጀርበውን ለመስጠት አላንገራገረም፡፡ በእልህ አስጨራሽ ሙግት በውጭ ትምህርቱን ተከታትሎ ከመጣም በኋላ ከኩርፊያም በዘለለ አመራሩን በሰላ ትችቱ ይነቅፍ ጀመረ፡ ፡በፓርቲው ውስጥ ያለውን የአማራ ብሄርተኝነት ማቀጥቀጥም በዋናነት ከሚመሩት ተራ ተሰለፈ ፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ አለመረጋጋት እያየለ ሲመጣም አምባቸው መኮንን የሚለው ስም በአማራ ፖለቲካ ውስጥ ተደጋግሞ ከሚጠሩት ተርታ ተመደበ፡፡

የቀድሞው የኢህኢዴን ታጋይ አምባቸው መኮንን(ዶ/ር) ከዘመናት የፖለቲካ ውጣ ውረድ በኋላ ህይወቱን ሊሰጥለት የተመኘውን ክልል መምራት ጀምሯል፡፡ አዲሱ ርዕሰ መስተዳዳር በባዕለ ሲመታቸው ዕለት ባደረጉት ንግግር የአማራን ህዝብ ለመምራት መታደል ትልቅ አጋጣሚ ቢሆንም ፍርሃትንም ያጭራል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ በርግጥም የአማራን ክልል በዚህ ወቅት ማስተዳደር ትልቅ ዕድል ብቻ ሳይሆን በጣም ትልቅ ፈተናም ነው፡፡

ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታውን ለተመለከተ ሰው ደግሞ አምባቸው መኮንን (ዶ/ር) ገና በአፍላነታቸው ዘመን በአፍሪካ ቀዳሚ ጦር ያለውን ደርግን አሸነፍን ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን እውን እናደርጋለን ብለው ትግል ከመጀመራቸውም የሚበልጥ ከባድ ፈተና ከፊታቸው ተደቅኗል፡፡ ይህ ፈተና የሚጀምረው ለፓርቲያቸው የሚበጅ አጋር ድርጅት ከመፈለግ ነው፡፡

የአማራ ፖለቲካ ልሂቃን በተደጋጋሚ በስራ ላይ ያለው ህገ-መንግስት የክልሉን ህዝብ ያገለለ በመሆኑ ሊሻሻል ይገባል የሚል አስተያየት ይሰነዝራሉ፡፡ ፌደራሊዝሙም የአማራን ህዝብ ለመበዝበዝ የተዘየደ ሴራ መሆኑን ያወሳሉ፡፡ እንዲህ ያለው የክልሉ ልሂቃን ሙግት በጊዜ ሂደት ኦዴፓም ደጃፍ የደረሰ ይመስላል ፡፡ ፓርቲው በያዝ ለቀቅም ቢሆን ህገ-መንግስቱ እንዲሻሻል እንደሚፈልግ አስታውቋል፡፡ ግን ይህ እንዴት እውን ሊሆን ይችላል?

አዴፓ የአማራን ህዝብ ጥቅምና ፍላጎት በዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ ለማስጠበቅ ታክቲካዊና ስትራቴጅካዊ አጋሮችን መለየት ይኖርበታል፡፡ ይህ የቤት ስራ ለአዲሱ የክልሉ ርዕስ መስተዳደር ከባድ መሆኑ አያከራክርም፡፡ የአምባቸው መኮንን (ዶ/ር) ድርጅት ካለፈው ሩብ ምዕተ ዓመት ሁለት አስርታት የሚሆነውን ከህወሓት ጋር ስትራቴጅክ ጥመርት ፈጥሮ ዘልቋል፡፡ ይሁን እንጅ የሁለቱ ፓርቲዎች ወዳጅነት ካላቸው የፖለቲካ ካፒታል አንጻር መጠነ ሰፊ ልዩነት የሚስተዋልበት ነበር፡፡ አብዛኛው የአማራ ፖለቲካ ልሂቅ ከላይ ከፍ ብየ እንደገለጽኩት ህገ-መንግስቱን የማይቀበል ፤ፌደራሊዝሙንም የሚተች ሲሆን የትግራይ ፖለቲከኞች በአንጻሩ ሁለቱ ጉዳዮች የዛሬዋ ኢትዮጵያ አዕማዶች ናቸው ብለው የሚያምኑ ናቸው ፡፡ ይህ መራራቅ ሰፍቶም በጊዜ ሂደት አዴፓና ህወሓት ሆድና ጀርባ ሆነዋል፡፡

ኦሮሚያ ላይ ባለው ህዝባዊ አመጽ ከህወሓት ጋር እስጣ ገባ የገጠመው ኦዲፒም ይህን በመጠቀም ከአዴፓ ጋር አዲስ ወዳጅነትን ለመመስረት ችልሏል፡፡ አምባቸው መኮንን (ዶ/ር)የተሳተፉበት የሁለቱ ፓርቲዎች አጋርነት ታክቲካዊ ይሁን ስትራቴጅካዊ ለመለየት ቢያስቸግርም ህወሓት መራሹን አገዛዝ ለማንኮታኮት ግን አቅም ነበረው፡፡ በዚህ የተነሳም ኦዲፒ ወደ ስልጣን እንዲመጣ በማድረግ በኩል አዴፓ ትለቅ ሚና ተጫውቷል፡፡ ነገር ግን በአሁናዊው የሀገሪቱ ፖለቲካ ኦዲፒና አዴፓ ለየቅል የሚባል መንገድ የጀመሩ ይመስላል፡፡ በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ ኦዲፒ ያወጣው መግላጫ ከዛም የአዴፓው ሊቀመንበር ደመቀ መኮንን በአደባባይ ብልጣ ብልጥ ፖለቲከኞች የሚሰሩትን ስራ እንቃወማለን ማለታቸው ለዚህ አይነቱ ልዩነት ዋቢ መሆኑ አይቀርም፡፡

የኦዲፒና አዴፓ አጋርነት የሚፈተነው ግን በአዲስ አበባ ጉዳይ ብቻ አይደለም ፡፡ ኦዲፒ በህገ-መንግስቱና ፌደራሊዝሙ የማይደራደር ፓርቲ መሆኑን በተደጋጋሚ ተናግሯል፡፡ የኦሮሞ ፖለቲካ ልሂቃንም ከአሁኑ ህገ-መንግሰት አንድ አንቀጽ እንኳን እንዲነካ እንደማየይፈልጉ በአደባባይ ሲናገሩ ከርመዋል፡፡ ይህ ደግሞ አዴፓ እታገልለታለሁ የሚለውን ህዝብ አስከፍቷል ፡፡ እንዲህ ከሆነ አዴፓ ለእሱ ትግል አጋር የሚሆን ሌላ ፓርቲን ማፈላለግ ይኖርበታል፡፡ ኢህአዴግ ቤት ካሉት ህወሓትና ኦዲፒ ጋር በሀገሪቱ የፖለቲካ አዕማድ ህገ-መንገስቱና ፌደራሊዝም ላይ ልዩነት ያለው አዴፓ ቀጣይ ክልል ዘለለ ወዳጁ ማን ሊሆን ይችላል ? ለርዕሰ መስተዳድር አምባቸው መኮንን የቀረበ ጥያቄ ነው፡፡

የአማራ ክልል አዲሱ ርዕስ መስተዳደር አጋር ፓርቲን ከማፈላለግ በተጨማሪም እሳቸውም የሚደግፉት የአማራ ብሄርተኝነት ጉዳይ ፈር የማስያዝ ፈተና ይጠብቃቸዋል፡፡ የአማራን ብሄርተኝነት ወደ ዴሞክረሲያው ብሄርተኝነት የመቀየሩ ተግባርም በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በማኅበራዊ ሚዲያ የሚመራውን የክልሉን አስተዳደር ውሳኔ ወደ ፖለቲካዊ ውሳኔ መመለስ ይኖርባቸዋል፡፡

እነዚህ ፖለቲካ የቤት ስራዎች ሲሆኑ በኢኮኖሚው በኩል በሚሊዮን የሚቆጠረውን የአማራ ወጣት የስራ ዕድል እንዲፈጠርለት ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባራ መሆኑ አያከራክርም፡፡ በተለይም በቅርብ ዓመታት ትልቅ መነጋገሪያ የነበረውንና የክልሉ የኢንዱስትሪ አብዮት መነሻ ይሆናል የተባለውን የአባይ ኢንዱስተሪ ዞን ግቡን እንዲመታ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close