Connect with us

Ethiopia

ተስፋን የዘራ ህዝብ መካራን ስለምን ያጭዳል?

Published

on

ተስፋን የዘራ ህዝብ መካራን ስለምን ያጭዳል? | በሬሞንድ ኃይሉ

ተስፋን የዘራ ህዝብ መካራን ስለምን ያጭዳል? | በሬሞንድ ኃይሉ

ፌስቡክ የሀዘን ድንኳን ይመስል ዋይታ በዝቶበታል፡፡ ከግራና ከቀኝ ጩኸት በርክቷል፡፡ ኢትዮጵያ ግማሽ ምዕተ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ለስድስተኛ ጊዜ የጀመረችው የለውጥ እንቅስቃሴ ተጨናግፏል የሚል ድምጽ እዚህም እዛም ይሰማል፡፡ ይህ ቀቢጸ ተስፋ መሆን እንደ ከዚህ ቀደሙ ከዴሞክራሲ የምንገናኝበትን ድልድይ ብቻ ስብሮ ዘውር የሚል አይመስልም፡፡ ኢትዮጵያም እንደ ሀገር መቀጠሏ የሚያስፈራበት ወቅት ላይ ደርሰናል፡፡ የአማራ ክልል ምክር ቤት የትግራይ ክልል ጦርነት አውጆብኛል የሚል መግለጫ አውጥቷል፡፡ አዴፓ ህወሓትን ወደ ክልሌ ጦር አስጠግቷል ሲል ወንጅሏል፡፡ አብሮ የኖረ ፤አብሮ የሞተን ህዝብ ፖለቲከኞች ለጦርነት ሊማግዱት አሰፍስፈዋል፡፡

ወዲህ ደግሞ አዲስ አበባ፣ በረራ፣ ፊንፊኔ የሚሉ ቃላቶች የእናሸንፋለንና እናቸንፋለን አምሳያ ሁነው ሀገር ሊያፈርሱ ከጫፍ ደርሰዋል፡፡ በደቡብ ክልል ማንነትን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች የሰርክ ሕይወት አካል ሁነዋል፡፡ ከኦሮሞ የምትጠቀም ብቻ ሳይሆን ኦሮሞንም የምትጠቅም ኢትዮጵያን ዕውን ማድረግ አለብን የሚለው የፖለቲካ ኃይልም አድፍጦ መታገሉን ቀጥሏል፡፡ በዚህ ሁሉ መሀል ግን ለሀገር እታገላለሁ የሚሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ድምጻቸውን አጥፍተዋል፡፡ የመደመር ፖለቲካ ቁርባን ሁኖባቸው ዝምታ ግዴታቸው ሆኗል፡፡ ወቅታዊ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ያስፈራል፡፡ ተስፋ ያደረገውን ህዝብም የሀዘን ማቅ እንዳያከናንብ ያስጋል ፡፡ የሚያስገርመው ነገር ግን አሁንም በዚህ ሀገራዊ ዳፋ ላይ መግባባት አልተቻለም፡፡

ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ አህመድ ስልጣነ መንበሩን ከያዙ አንሆ አመት ሊሞላቸው የቀናቶች ዕድሜ ቀርቷቸዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ የተካሄዱ ለውጦች የሚያስመሰግኑትን ያህል የጎደለው ነገርም ሊያሰወቅሳቸው ይገባል፡፡ ባለፉት አስራ ሁለት ወራት የተካሄደው የለውጥ እንቅስቃሴ ሀገር የመለውጥ አቅም ዕንደነበረው ሁሉ ሀገር ላትመለስ እንድትጠፋ የማድረግ ዕድልም ነበረው፡፡ ይህን መንታ ገጽታ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒሰትር መለስ ዜናዊ አገላለጽ በመዋስ መመልከቱ ተገቢነት ያለው ይመስላል፡፡

አቶ መለስ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ከዳፋ ጋር ያመሳስሉት ነበር፡፡ አንድ ግለስብ የተራራውን መናድ አይቀሬነት አስተውሎ ወደ ቤቱ ሩጫ ቢጀምር ከዳፋው የማምለጥ ዕድሉ የሚወሰነው በፍጥነቱ እንጅ ሩጫ ላይ በመሆኑ አይደለም፡፡ እንደ አቶ መለስ ገለጻ የተራራውን መናድ ተርድቶ ሩጫ የጀመረ ሰው ግብግቡ ከጊዜ ጋር ነው፡፡ ያ ሳይሆን ከቀረ ግን መሮጥ ካለመሮጥ እኩል ነው፡፡ ቀድሞ ሩጫ ጀምሮ ቤት አቅራቢያ ላይ በተራራ ናዳ መሞትም ሩጫ ሳይጀምሩ ባሉበት ማሸለብም ልዩነት የላቸውምና፡፡

የኢትዮጵያ ፖለቲካ የለውጥ ጅምር ከዚህ ምሳሌ ጋር እጅግ የተሳሰረ ይመስለኛል፡፡ ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ የሚመሩት መንግስት ሩጫ ቢጀምርም የሩጫው ፍጥነት ካለመሮጥ ጋር እየተመሳሰለ ነው፡፡ መንግስት ብዙ ነገር ቀይሪያለሁ እያለ ቢለፍም ሀገርን ከመጣው ዶፍ ለመታደግ እየተሳነው ነው፡፡ ይህ ደግሞ ባለፉት ወራት ተስፋን ሲዘራ የኖረ ህዝብ ምርቱ ሀዘን እንዲሆን አድርጓል፡፡ የኢትዮጵያዊያን በእንዲህ ያለ ሰንክሳር ውስጥ መዳከር ፖለቲካችን ከተግባር ይልቅ ወሬ ጠገብ ከመሆኑ ይመነጫል፡፡ በዚች ሀገር ይህ ነው የሚባል የዴሞክራሲ አብዮት ተካሂዶ አያውቅም፡፡ ለዚህም የሚሆን ማህበራዊ መደላድል የለም፡፡ ዴሞክራሲንና ፍታሃዊ የፖለቲካ ስርዓትን የመገንባት ሂደት ባልጀመርንበት ሁኔታ ውጤቱን እንጠብቃለን፡፡

ኢትዮጵያ ከሰሞኑን በወጣ ሪፖርት የህግ -የበላይነትን በማክበር በኩል ከዓለማችን የመጨረሻ ሀገራት ተርታ የምትመደብ መሆኗ መገለጹ ይታወሳል፡፡ የአንድ ሀገር ፖለቲካዊ ዕደገት አዕማድ በሆነው የህግ- የበላይነት ያለን እውነታ ይህ ቢሆንም እኛ ግን አሁንም የሚያኩራራ ለውጥ አምጠተናል እያልን ከመናገር ወደ ኋላ አላልንም፡፡ ሀገር እንደ ሀገር ሁሉንም ዜጎች በፍታሃዊነት መጥቀም የሚችለው ጤናማ የፖለቲካ ስርዓት መዘርጋት ሲችል ብቻ መሆኑ አያከራክርም፡፡

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ግን የፈረቃ ፖለቲካ ነው፡፡ በተለያዩ ጽሁፎቼ ደጋግሜ ጆን ማርካኪስን ዋቢ በማድረግ እንደጠቀስኩት የሀገራችን የመቶ ዓመት ታሪክ የእኔ ተረኛ ነኝ ልግዛ እሰጣ ገባ እንጅ ሌላ አይደለም፡፡ ይህን ሀቅ ከመሰረቱ መቀየር ያስፈልጋል፡፡ ከአሸናፊ ተሸናፊ ትርክት ወጥተን የጋራ ፖለቲካዊ ምህዳር መፍጠር አለበን፡፡ ያ ካልሆነ ግን አማራ ሲመራ ኦሮሞና ትግራይ፣ ትግራይ ሲመራ አማራና ኦሮሞ ፣ኦሮሞ ሲመራ ትግራይና አማራ ከፖለቲካ ሜዳው ገለል መደረጋቸው አይቀርም፡፡ እሱ ደግሞ ለሀገር ጽልመት ነው ፡፡ ትንሳኤ የሌለው ፅልመት፡፡

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close