Connect with us

Ethiopia

የኦዴፓ ነገር…”ምድሩም፣ አየሩም የእኛ ነው!”

Published

on

የኦዴፓ ነገር…"ምድሩም፣ አየሩም የእኛ ነው!"

የኦዴፓ ነገር…”ምድሩም፣ አየሩም የእኛ ነው!” | በጫሊ በላይነህ

በያዘው ሳምንት መጀመሪያ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ከ51 ሺ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለተጠቃሚዎች እንደሚያስተላልፍ በይፋ መናገሩ የኦ ኤም ኤን ሚዲያ ባለቤትና አክቲቭስት ጃዋር መሐመድንና ተከታዮቹን አስቆጣ፡፡

በተለይ በኮዬ ፈጩ (ገላን ከተማ) ተገንብተዋል የተባሉት የጋራ መኖሪያ ቤቶች በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የተገነቡ በመሆኑ በዕጣ ሊተላለፉ አይገባም የሚል ግልጽ የሆነ ተቃውሞና ዛቻ አዘል መልዕክት አስተላለፈ፡፡ “የመኖሪያ ቤቶች ዕጣ ባለዕድለኞች ቤት አገኘን ብላችሁ ወደኮዬ ፈጪ ኮንደሚኒየም ትመጡና ችግር ይፈጠራል” እስከማለትም በአደባባይ ዛተ፡፡ ይህ ዛቻ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ማስደንገጡ አልቀረም፡፡

የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ዕጣ ከትላንት በስቲያ ዕረቡ ዕለት ባወጣበት ሥነሥርዓት ላይ የአስተዳደሩ ካቢኔ ለልማት ተነሺ ለሆኑ አርሶአደሮች የኮንደሚኒየም ቤቶች ያለዕጣ እንዲሰጣቸው በድንገት ለመወሰን መገደዱን በምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ በኩል መነገሩ የእነጃዋር ዛቻ ውጤት አድርጎ መውሰድ ይቻላል፡፡

እነጃዋር በዚህም አልረኩም፡፡ የዕጣውን መውጣት ተከትሎ ትላንት በበርካታ የኦሮሚያ ከተሞች ማለትም በጉደር፣ በሆለታ፣ በሻሸመኔ፣ በጭሮና በሌሎችም ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎች እንዲካሄዱ አስደረጉ፡፡ ይህንንም ተከትሎ ትላንት ማምሻውን የኦሮሚያ ክልል መንግሥት መግለጫ አወጣ፡፡ በሕግ ማስከበር ስም በለገጣፎ- ለገዳዲ ሰዎች ሲፈናቀሉ፤ ቅሬታቸውን እንኳን ለመስማት የተሳነው የኦሮሚያ ክልል ምክርቤት ለእነጃዋር የሜንጫ ዛቻ ፈጣን ምላሽ መስጠቱ ወገንተኝነቱ ከእነማን ጋር እንደሆነ በግልጽ ያሳየበት ክስተት ነው፡፡

የኦሮሚያ ክልል መንግሥት መግለጫ በአጭሩ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ መካከል ያለው የአስተዳዳር የወሰን ጉዳይ እልባት ሳይሰጠው የጋራ መኖሪያ ቤቶች በዕጣ መተላለፋቸውን ተገቢ አይደለም፣ ስለሆነም እንዳይተገበር ወስነናል የሚል ነው፡፡

በእኔ ዕይታ ይህ መግለጫ የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዴፓ) ገዥ ፓርቲ መሆኑን ጨርሶ የዘነጋበት ነው፡፡ ኦዴፓ በአሁን ሰዓት አገር እያስተዳደረ ያለ ፓርቲ ነው፡፡ አንድ አገር የሚያስተዳድር ፓርቲ ደግሞ እይታው በክልል ከታጠረ ወይንም አገራዊ ቁመና መያዝ ካልቻለ ትልቁን ኃላፊነቱን ዘንግቷል ማለት ነው፡፡ ይህ ክልል አጠር መግለጫው ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በኦዴፓ ላይ ሊኖራቸው የሚገባውን መተማመን የሚንድ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኮዬ ፈጩ ቤቶችን ሲገነባ ለተነሺ አርሶአደሮች ካሳ ከፍሏል፡፡ “ካሳው አንሷል፣ አርሶአደሩ ተጎድቷል” የሚል የቆየ ክርክር መኖሩ የማይካድ ነው፡፡ ይህ “የካሳ አንሶናል፣ ተበድለናል” ጥያቄ ለኮዬ ፈጩ ብቻ ሳይሆን በየትኛውም አካባቢ የተነሱ አርሶአደሮችና የከተማ ሰዎችን የሚመለከት ነው፡፡ የሁሉም ጥያቄ መልስ ግን በተናጠል ሳይሆን ለሁሉም አብሮ የሚመለስ ነው፡፡

ልብ በሉ!..በልማት ስም በመፈናቀል ረገድ ከአርሶአደሩ ባልተናነሰ የአዲስ አበባ ነዋሪ ባለፉት ዓመታት ከባድ ዋጋ ከፍሏል፡፡ በልማት ስም እትብቱን ከተቀበረበት ቀዬ በአነስተኛ ክፍያና የምትክ ቦታ ሲፈናቀል ኖሯል፡፡ ብዙ ወገኖች ከአካባቢያቸው በመነሳታቸው ብቻ ለተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች መዳረጋቸው ጸሐይ የሞቀው ሀቅ ነው፡፡ ግን የአዲስ አበባው ተፈናቃይ የሚጮህለት ባለመኖሩ ብቻ ተረስቷል፡፡ በአንጻሩ የኮዬ ፈጩ ሕዝብ የሚጮህለት በማግኘቱ ብቻ ቀድሞ ከወሰደው ካሳ በተጨማሪ ያለዕጣ ቤት እንዲሰጠው ተወስኖለታል፡፡ እሱም አልበቃም ተብሎ ዜጎች በገዛ አገራቸው ወደክልላችን መጥታችሁ መኖር አትችሉም የሚል አዋጅ አገር በሚመራ ፓርቲ ተነግሮባቸዋል፡፡

በአንድ ወቅት ጠ/ሚኒስትር አብይ አሕመድ እንዲህ ብለው ነበር፡፡ “ድንበር እና ወሰን ማምታታት አለ፡፡ አማራ እና ኦሮም፤አማራ እና ትግራይ ድንበር የላቸውም፡፡ ወሰን ነው፡፡ ድንበራችን ከኬኒያ ጋር ነው፡፡፡ አንድ አማራ ነቀምት፣ አንድ ኦሮሞ ጅግጅጋ ላይ መኖር ካልቻለ ከባድ ነው፡፡…”

አዎ! መሬት ላይ ያለው እውነታ ግን አንዱ በሌላው ክልል በሠላም በፍቅር የመኖሩ መብት በአክራሪ ብሔርተኞች በአደባባይ መሻሩን የሚያሳይ ነው፡፡ ኦዴፓ እንደአገር መሪነት ያለውን ሰፊ ሚና ዘንግቶ በጠባቡ ሜዳ መጫወትን የመረጠ መስሏል፡፡

ኦዴፓ በዚህም አቋሙ ከዛሬ ነገ ዕጣ ወጥቶልኝ ከመኖሪያ ቤት ችግሬ እላቀቃለሁ ብሎ ሳይተርፈው ሲቆጥብ እየኖረ ካለው ወደ አንድ ሚሊየን የሚጠጋ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ፈላጊ የአዲስአበባ ነዋሪ ጋር ፊት ለፊት ተላትሟል፡፡ ኦዴፓ “መሬቱም፣ አየሩም የእኛ ነው” የሚሉ አክራሪ ብሔርተኞችን አጀንዳ እያራገበ እንዴት ኢትዮጵያን ያህል ትልቅ አገር እና ሕዝብን በእኩልነት፣ በወንድማማችነት መርህ መምራት ይችላል የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ሆኗል፡፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** ኢትዮ ጵያን የተመለከቱ የተለያዩ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዘኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close