Connect with us

Ethiopia

ከሦስት ዓመት በፊት በወላጆቻቸው ተጥለው የተገኙ ህፃናት ዛሬ አዲስ አበባ ገብተዋል

Published

on

ከሦስት ዓመት በፊት በወላጆቻቸው ተጥለው የተገኙ ህፃናት ዛሬ አዲስ አበባ ገብተዋል

ሣኡዲ አረቢያ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከሦስት ዓመት በፊት በወላጆቻቸው ተጥለው የተገኙ ህፃናት ዛሬ አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡

ህፃን ሀፍሣ መሀመድ የዛሬ ሦስት አመት ገደማ፣ ህፃን አሚር መሀመድ ደግሞ ከሁለት ዓመት በፊት ነበር ምድራችንን የተቀላቀሏት፡፡

ከነዚህ ህፃናት ከኢትዮጵያዊት እናቶች የተወለዱ ሲሆን፣ እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ እንኳን ወደዚች ምድር በሠላም መጣችሁ ተብለው ክፍን፣ ሽፍን አልተደረጉም፡፡ ይልቁንም ህይወት ዘርተው ወደ ምድር ብቅ ባሉበት በሣኡዲ አረቢያዋ ሪያድ ከተማ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የስደተኞች መጠለያ በር ላይ መወርወር ነበር ዕጣቸው፡፡ ህፃናቱ በሪያድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የስደተኛ መጠለያ ውስጥ በተደረገላቸው ድጋፍ ህፃን ሃፍሣ የሦስት ዓመት፣ ህፃን አሚር ደግሞ የሁለት ዓመት ተኩል ዕድሜያቸውን እንዲቆጠሩ ሆነዋል፡፡

ክብርት የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በጥር ወር መጀመሪያ በሣኡዲ አረቢያ በነበራቸው የስራ ቆይታ መንገድ ላይ ተጥለው የተገኙትን ህፃናት ጐብኝተው ነበር፡፡ ህፃናቱ በቤት ሠራተኝነት ወደ ሣኡዲ አረቢያ ከሄዱ ኢትዮጵያውያን ተወልደው መጣላቸውንም በሳኡዲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ገለፃ የተደረገላቸው ሲሆን፣ ህፃናቱ ከአዋቂ ስደተኞችና የአዕምሮ ሕሙማን ጋር በመጠለያ ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውንና ኤምባሲውም ለህፃናቱ እያደረገ ያለው ድጋፍ በቂ አለመሆኑን ተመልክተው ነበር፡፡

በመሆኑም ህፃናቱ በመጠለያ ተቋሙ ውስጥ ከአዋቂዎችና ከአዕምሮ ሕሙማን ጋር ጭምር አንድ ላይ መቀመጣቸው በሕፃናቱ ዕድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር በመታመኑ ሕፃናቱን ተቀብሎ እንክብካቤ የሚያደርግ ማዕከል በማፈላለግ ሠላም የሕፃናት መንደር ህፃናቱን ተቀብሎ ለማሳደግ ፈቃደኝነቱን በገለጸው መሠረት ዛሬ የካቲት 28 ቀን 2ዐ11 ዓ.ም. ማለዳ ሕፃናቱ ከሣኡዲ አረቢያ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ተደርገዋል፡፡

ሕፃናቱ አዲስ አበባ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ክብርት የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ፣ ክብርት ወ/ሮ አለሚቱ ኡመድ የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር ዴኤታ፣ የአዲስ አበባ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ አመራሮች እና የሠላም የህፃናት መንደር ሀላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡

ክብርት የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጐጌ ተስፋዬ በአቀባበል ስነ-ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፣ ዜጎች በህገ-ወጥ መንገድ ወደተለያዩ ሀገራት የሚያደርጉት ጉዞ ከተለያዩ የመብት ጥሰቶች አንስቶ እስከመደፈር ለሚደርሱ ችግሮች እያጋለጣቸው ይገኛል፡፡ የእነዚህ ህፃናት ተጥሎ መገኘት የሚነግረንም ህገ-ወጥ ጉዞ ከተጓዥ ባሻገር ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ህይወት ወደከፋ አደጋ እየወሰደው መሆኑን ነው ብለዋል፡፡

በሕገ-ወጥ መንገድ የሚደረግ የውጭ አገር ጉዞ ዜጎችን ለበርካታ ችግርና መከራ እየዳረገ በመሆኑም፣ ዜጎች በአገር ውስጥ ሰርቶ መለወጥን ቅድሚያ እንዲያደርጉ፣ በውጭ አገር ሰርተን መኖር እንፈልጋለን ካሉ ደግሞ ህጋዊ የውጭ አገር ስራ ስምሪትን ብቻ እንዲከተሉም ሚኒስትሯ አስገንዝበዋል፡፡

በሣኡዱ አረቢያ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኮሙዩኒቲ አባላት ሕፃናቱ መንገድ ላይ ወድቀው እንዳይቀሩ ላበረከቱት መልካም ተግባር አመስግነው፣ ህፃናቱ ወደ ሀገራቸው ገብተው ከወገኖቻቸው ጋር እንዲያድጉ የበኩላቸውን ጥረት ላደረጉት በሣኡዲ አረቢያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ፣ የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሴቶችና ህፃናት ቢሮ እና ሠላም የሕፃናት መንደርን አመስግነዋል፡፡

ክብርት ወ/ሮ አለሚቱ ኡመድ የሴቶች ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር ዴኤታ በበኩላቸው፣ ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በሣኡዲ በነበራቸው ቆይታ የተመለከቷቸው ህፃናት የሚገኙበትን ሁኔታ በመረዳት ለሀገራቸው እንዲበቁ ላደረጉት ጥረት አመስግነው፣ ህፃናቱን በቀጣይ የሚረከቡ ሰዎችም እንደራሳቸው ልጅ አሳድገው ለቁምነገር እንዲያበቁ አደራ ብለዋል፡፡

በአቀባበል ስነ-ስርዓቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶችና ህፃናት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ አልማዝ አብርሃ ከሁለቱ ህፃናት መካከል አንዷን ወስደው ለማሳደግ ቃል ገብተዋል፡፡

(ምንጭ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር)

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close