Connect with us

Art and Culture

በሴቶች ቀን ታላላቅ ታሪክ የሚዘክራቸውን ሴቶች ስንዘክር

Published

on

በሴቶች ቀን ታላላቅ ታሪክ የሚዘክራቸውን ሴቶች ስንዘክር

በሴቶች ቀን ታላላቅ ታሪክ የሚዘክራቸውን ሴቶች ስንዘክር፤ የኢትዮጵያውያን ሴቶች ለታላቋ አፍሪቃዊት ሀገር፤ (ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም የዓለም የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ ታሪክ የተለየ ስፍራ የሚሰጣቸውን ኢትዮጵያውያን ሴቶች እናስታውሳቸው ሲል ስለ ጥቂቶቹ ገናና ኢትዮጵያውያን ሴቶች እንዲህ ይተርክልናል፡፡) ሄኖክ ስዩም በድሬቲዮብ

በኢትዮጵያ የሺህ ዓመታት ታሪክ ብርቱ ሴቶች የታሪኩ ማዕከል ናቸው፡፡ ያለ ድንቅ ሴቶቻችን የማይደመጥ ታሪክ ያኖሩ አባቶች ምስጋና ይግባቸውና ዓለም ለሴት ቀን መድቦ ሴት ከፍ ትበል ከማለቱ በፊት በኢትዮጵያውያን ትውፊት የሴቶች ሥርወ መንግሥትም ነበር፡፡

ጌዴዮ አኮማኖዬ የሚለውና ሴት ብቻ ስትመራው የኖረው የሴት ሥርወ መንግሥት ጣፋጭ ታሪክ እንዲህ ላለው ሀሳባችን ማስረጃ ነው፡፡ ጥቂት ሴቶችን ነገር ግን በታሪካችን ልዩ ስፍራ የሚሰጣቸውን የሴቶች ቀን ነውና እናነሳሳቸው፡፡

የኢትዮጵያ ሴቶች አይደሉም ምድሩ ራሱ ከንግሥት ሳባ ተቆራኝቶ የሚተረክ ነው፡፡ ከአረብ ጉሮሮ አስጥለን ከየመን ልብ ፈልቅቀን የእኛ ያደረግናት ንግሥት ሳባ ቀዳሚዋ የኢትዮጵያ ሴቶች ተምሳሌት ናት፡፡

ሳባ ከሠለሞን ከፈጠረችው ወዳጅነትና ቀዳማዊ ምኒልክን ወልዳ ቀጠለ ከተባለው ሠለሞናዊ ሥርወ መንግስት ይበልጥ ሳባ የመሪነት፣ የጥበብ ናፋቂነት፣ የኢትዮጵያ ገናና ስልጣኔ ምልክትነት ጎልቶ ይነሳል፡፡ ሳባን ተከትሎ ንግሥት ሶፍያ የምትባለው የአብረሃ ወ አጽበሐ እናት መንታዎቹን ገናና ኢትዮጵያውያን ነገሥታት በመውለድ ከምትነሳበት ባሻገር የኢዛና ሰፋፊ ግዛቶች በጦር ድል ሲጠቃለሉ የአክሱም ገናና ዘመን ሲመለስ ከልጆቿ ጎን በምክር ነበረች ይሏታል፡፡

ሌላዋ ዩዲት ናት፡፡ የታሪክ ምሁራኑ ሊከራከሩ ቢሞክሩ እንኳን የሀገሬ ሰው የለም ብሎ በአማርኛም በትግርኛም በአፋርኛም ስም ያወጣላት፤ በጦር አቅሟ ገናና፤ በዋለችበት የጦር አውድ ድል አድራጊ፣ አክሱምን ማፈራረስ የቻለች፡፡ ሰለሞናውያኑን ሸዋ ድረስ ያሰደደች፤ ለካራ ምሽግ መሠራት ምክንያት የኾነች፤ እንደ መርሐ ቤቴ ያሉ ስሞች ከስሟ ጋር የሚነሱ፣ መቃብሯ ነው የሚባለው ጋዕዋ የተባለ ስፍራ ሳይቀር ታፍሮና ተከብሮ ኖሮ የሺ ዓመታት የአርኪዎሎጂ ግኝት ስፍራ ለመሆን የበቃ ባለ ታሪክ ናት፡፡

ባቲ ዲል ወንበራ ሌላዋ ጀግና ኢትዮጵያዊት ሴት ናት፡፡ የአሚር ማሕፉዝ ሴት ልጅ ናት፡፡ የምስራቅ አሚሮች ከደጋው ክርስቲያን ነገሥታት ጋር ጦርነት ላይ በነበሩበት ዘመን የተፈጠረች ሴት ናት፡፡ የኢትዮጵያም ኾነ የውጪ ታሪክ ጸሐፍት ተርከው ያልጠገቧት ወጣት ጀግና ስትኾን የኢማም አህመድ ሚስት ናት፡፡ በዘመኗ በተካሄዱ ጦርነቶች ሁሉ አብራ የተሰለፈች በጀግነነት ስሟን የታሪክ ሊቃውንት ደጋግመው ያነሱላት የታሪካችን አንድ መገለጫ ሆነች፡፡ ሰብለወንጌል ንግሥት ባቲ ዲል ወንበራን አንስተን የማንተዋት ኢትዮጵያዊት እቴጌ ናት፡፡ የእቴጌነት ዘመኗ ስደት ጦርነትና መከራ የተፈራረቀበት ነበር፡፡ የኢማም አህመድ ጦር በርትቶ የደጋውን ክርስቲያን ጦር ሲያሸንፍ ጦሩን የመምራቱ ሃላፊነት የወደቀባት ንግሥት እንደነበረች ታሪኳ ይነግረናል፡፡

የዐፄ ልብነ ድንግል ሚስት የንጉሥ ገላወዴዎስ እናትና ሞግዚት የነበሩት እቴጌ ሰብለ ወንጌል አርባ አመታት በቆየ የግዛት ዘመን የገጠማቸውን ጦርነት ለመፍታት ከፖርቹጋል ወታደሮች ጋር ተቀናጅተው በመጨረሻም ወይና ደጋ ላይ የተካሄደውን ጦርነት ለድል ያበቃች ጀግና ናት፡፡ ንግሥት ፉራ በኢትዮጵያ ብዙ ካልተጻፈላቸው ገናና ሴት ነገሥታት አንዷ ናት፡፡

የታሪክ ሊቃውንት አፈ ታሪክ ናት እውነት ነበረች በሚለው ላይ ሙግት ቢገጥሙም በሲዳማ ተረክ ከፍ ያለ ስፍራ ይዛ የኢትዮጵያውያን ሴቶችን ክብር የምታሳይ ጀግና ንግሥት ኾና ትተረካለች፡፡

እቴጌ ምንትዋብ የጎንደር ዘመን ታሪክ ትልቅ ቦታ የሚሰጣት ኢትዮጵያዊ ንግሥት ናት፡፡ የዐፄ ባካፋ ሚስት በጎንደር ከሚገኙ ድንቅ አብያተ መንግሥታት የአንዱ ሕንፃ አስገንቢ የጎንደርን ቁስቋም ቤተ ክርስቲያን ያሰራች በርካታ የውጪ ሀገር ጸሐፍት ዝናዋንና ክብሯን ከፍ አድርገው ተርከውላታል፡፡ በሙያና በዕደ ጥበብ ኢንዱስትሪ መስፋፋት በአብነት ትምህርት ቤት እድገት በሌሎችም ድንቅ ተግባራቷ አሁንም ድረስ ስሟ በክብር ይጠራል፡፡

እቴጌ ጣይቱ ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ፤ በኢትዮጵያ ሴት ነገሥታት ታሪክ ከንግሥት ሳባ ቀጥሎ ብዙ የተባለላት ሴት ንግሥት ጣይቱ ናት፡፡ በጀግንነት፣ በአመራር፣ በፖለቲካዊ ውሳኔዎችና ስማቸው ጎልቶ ከሚጠራው ዳግማዊ ምኒልክ አብሮ በመነሳት ጣይቱ የዘመናችን ሴቶች ምሳሌ የኾነች ኢትዮጵያዊ ንግሥት ናት፡፡ ዓለም ከአድዋ ጦርነት ማግስት ስሟን ከፍ አድርጎ አስተጋባው፤ በሀገር ፍቅርና በመሪነትም ቢሆን መገለጫ ሆነች፡፡

ዛሬ የዓለም ሴቶች ቀንን ስናክብር ዓለምን ሳናውቀው የምናውቃቸው ታላላቅ ኢትዮጵያውያን ሴቶች የሀገራችን ምልክቶች ሆነው ኖረዋል፡፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** ኢትዮ ጵያን የተመለከቱ የተለያዩ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዘኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close