Connect with us

Ethiopia

ፓትርያርኩ የደህንነት ሥጋት አለብኝ አሉ

Published

on

ፓትርያርኩ የደህንነት ሥጋት አለብኝ አሉ

ፓትርያርኩ የደህንነት ሥጋት አለብኝ አሉ

እሑድ፣ የካቲት 24 ቀን 2011 ዓ.ም. በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ባለ ሢመታቸውን ያከበሩት 6ኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት “ለሕይወቴ እሰጋለሁ” በማለት መንግሥትን የደኅንነት ዋስትና መጠየቃቸው ተሰማ፡፡

የልዩ ሀገረ ስብከታቸው አዲስ አበባ አድባራትን መነሻ ያደረጉና በመንበረ ፓትርያርኩ ቅጽር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረከቱ በሚታዩ የካህናትና የምእመናን አቤቱታዎችና ክሦች አንድምታና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ለመነጋገር ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት በቀረበ ጥያቄ መሠረት፣ ቅዳሜ፣ የካቲት 16 ቀን ከቀትር በኋላ ወደ ታላቁ ቤተ መንግሥት አምርተው ከዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ጋራ የተወያዩት ቅዱስነታቸው፣ ኾነ ተብሎ ወደ ጽ/ቤታቸው እንዲጎርፉ በሚደረጉ አቤቱታዎች ሥራቸውን ለማከናወን እንደተቸገሩና ለሕይወታቸውም እንደሚሰጉ በመጥቀስ መንግሥት የደኅንነት ዋስትና እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

አቤቱታዎቹ፣ በየደረጃው ያልተመረመሩና አግባብነታቸውም ያልተመዘነ እንደኾነ ፓትርያርኩ ገልጸው፣ እርሳቸውን የማስጨነቅ ዓላማ እንዳለው አመልክተዋል፤ አቤቱታ አቅራቢ ከተባሉ ካህናትና ምእመናንም ከጉዳዩ ጋራ ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌላቸውና የውሎ አበል ስለተከፈላቸው ብቻ የተሰለፉ ግለሰቦች የተለዩበትን አጋጣሚ መፈጠሩን አንሥተዋል፤ አቤቱታችንን እናሰማለን ብለው ወደ ቢሯቸው እንዲገቡ ከተፈቀደላቸው በኋላ፣ “አንተ ለምንድን ነው ጉዳያችንን የማትጨርስልን” እያሉ ያንጓጠጧቸውና የሰደቧቸው መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

ሰልፎቹ በአመዛኙ የሚደረጉት፣ ቋሚ ሲኖዶስ ሳምንታዊ ስብሰባ የሚያካሒድበት ረቡዕ እና ዐርብ እየተጠበቀ እንደኾነና በማሰለፍ የሚተባበሩትም “እዚያው አጠገቤ ያሉት ናቸው” በማለት ኹለት ብፁዓን አባቶችን በሓላፊነት ድርሻቸው ጠቅሰዋል፤ “የጠሉትን እያስነሡ የወደዱትን ለማሾም እየተጠቀሙበት ነው፤” ብለዋል፤ “በጸጥታ በኩል ተቸግረናል፤ በስብሰባችን ቀናት ሰዉን ቀስቅሰው ያመጣሉ፤ ሦስት እና አራት ሺሕ ኾነው ጥሰው እየገቡ ግቢውን እያጨናነቁት ነው፤ አጨናንቋቸው፣ መፍትሔ ታገኛላችሁ እየተባሉ፤ ጋዜጠኛም አብሮ እየመጣ የቤተ ክርስቲያንን ስም ጥላሸት እየቀባ ነው፤ ቢሮዬ ገብተው ሶፋ ላይ ተቀምጠው አንወጣም ያሉ ጎረምሶችም አሉ፤ መሥራት አልቻልኩም፤” ሲሉ አምርረዋል፡፡

የሰልፉ አነሣሾችና አስተባባሪዎችም፣ በሚጽፏቸው ደብዳቤዎች “የለውጥ አካል ነን፤ የለውጥ አካል ይግባ” በማለት መንግሥታዊ አካላትን መጥቀስ እንደሚያዘወትሩና እርሳቸውን ደግሞ የለውጥ ተቃዋሚ አድርገው ለማሳየት እንደሚጥሩ ተናግረዋል፤“ወይስ እናንተ ናችሁ አደራጅታችሁ የምትልኩብን?” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጠይቀዋል፤ ጉዳዩን ቀደም ሲል ለመንግሥት በደብዳቤ እንዳስታወቁና ምላሽ እንዳልተሰጣቸው አውስተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበኩላቸው፣ በአገራዊ ለውጡ ስም አልያም “ጊዜው የእነ እገሌ ነው” እያሉ ከባለሥልጣናት ጋራ በማዛመድ ጫና ለመፍጠር እንዲሁም ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት የሚደረግ እንቅስቃሴ በርግጥም በቤተ ክህነቱ ውስጥ ካለ እንደሚከታተሉት ለፓትርያርኩ ገልጸውላቸዋል፤ ላቀረቡት የደኅንነት ዋስትና መንግሥት ጥበቃ እንደሚያደርግና የሚያጎድለው ነገር እንደሚይኖር አረጋግጠውላቸዋል፡፡

(ምንጭ፡- ሐራ ተዋህዶ)

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close