Connect with us

Art and Culture

ደኽና ሁን ጋሽ ጌታቸው!

Published

on

ደኽና ሁን ጋሽ ጌታቸው! | ማዕረግ ጌታቸው

ደኽና ሁን ጋሽ ጌታቸው! | ማዕረግ ጌታቸው@DireTube

ሞት የህይወት ፌርማታ ነው፡፡ ከዚኽኛው ዓለም ወደ ሌላኛው ዓለም ለመጓዝ የተሰለፍንበት፡፡ ጌታቸው ደባልቄን የማውቃቸውው እዛ ስለፍ ላይ ነው፡፡ ግን ስልሰፉን ይረሱት ነበር፡፡ ለዚህም ነው ሞትን ይረቱት ይመስል ከህመማቸው ጋር እየታገሉ ተስፋ ማድረግን የተካኑት ፡፡ ጌታቸው ተስፋ ያደርጋሉ ፡፡ ዓይናቸውን ተሸሏቸው ድጋሚ ማንበብ እንደሚችሉ፡፡ ስለብሄራዊ ቴአትር የጻፉት መጽሐፍ ታትሞ ከሰው እጅ እንደሚደርስ ……ወዘተ፡፡ የጋሽ ጌታቸው የተስፋ ልክፍት እስከ ዘላለም ዓለም የሚደርስ ይመስለኛል፡፡

ከሳመንታት በፊት በብሄራዊ ቴአትር ፏየ አደራሽ ቴአትር ቤቱ ወደፊት በምን መንገድ መጓዝ አለበት የሚል የምክክር መድርክ ሲዘጋጅ ከወጣቶቹ ይልቅ በቦታው የተገኙት እሳቸው ነበሩ፡፡

የጌታቸው ትውልድ ዘመን በኢትዮጵያ እምቢተኝነት የገነገነበት ነው፡፡ ጣሊያን ተመልሳ መጣች የሚለው ወሬ ኢትዮጵያን ሲንጥ አርበኞች እምቢ ለሀገሬ እያሉ ሲሸፍቱ የቴአትሩ ሊቅ ገና ጨቅላ ነበሩ፡፡ ግን እንደ ትውልድ ዘመን አቻዎቻቸው በዓሉ ግርማ ፣ጸጋየ ገ/መድኅን፣ ሰለሞን ደሬሳ የልጅነት ተውስታቸው የኋላ ዘመናቸውን ደጋግሞ ፈትኖታል፡፡ ጌታቸው አንደ በዓሉ ግርማ በደርግ አይገደሉ እንጅ ተሰቃይተዋል፡፡ ሎሚ ተራ ተራ የሚል ሙዚቃን የደረስከው አብዮቱን ጥርጣሬ ውስጥ ለመክተት ነው ተብለው ተገርፈዋል፡፡ የጌታቸው እምቢ ባይነትግን በዕስር ቤት የሚመለስ አልነበርም ፡፡ ሰልፍ መውጣት የጥይት ሲሳይ በሚያደርግበት በዚያን ሰሞን የብሄራዊ ቴአትር ሰራተኞችን አስተባብረው ደሞዝ ጭማሪ ካልተደረገልን ብለው አድማ እንዲመታ አድረገዋል፡፡

የቴአትሩ ሰው አምቢተኝነት ጉርመስና የወለደው አልያም ከደርግ ጋር በተፈጠረ ቅራኔ የመጣ አይደለ ፡፡
ጌታቸው ገና በጥበብ ህይወት ዳዴ በሚሉበት የብላቴናነት ዘመን ኢ-ፍታሃዊነትን እምቢ ባይ ነበሩ፡፡ 1943 ዓ.ም ማዘጋጃ ቴአትር የተቀጠሩ ታዳጊ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ወደ ተስፋ ኮከብ ትምህርት ቤት አዳሪ ሁነው እንዲዛወሩ ሲደረግ ቀድሞ አይሆንም ያሉት የያኔው ታዳጊ ጌታቸው ነበሩ፡፡ ለጥበብ ስራችን አይመቸንም፡፡ መንግስት የመደበልን የኪስ አበል ባልተገባ መንገድ ነው የተቋረጠው ብለው በህጻን ልባቸው አምጽዋል፡፡ ይህ መካረረም ለወራት ታዳጊዎቹ እንዲበተኑ አድርጓል፡፡

ጌታቸው ደባልቄ አስናቀችን የሚያህል ተዋናይት ምኒልክን ወሰናቸውን የሚያህል ድምጻዊ ከጥበብ ያዛመዱ ድንቅ ባለሙያ ናቸው ፡፡ አስናቀችን ከገዳም ሰፈር አንስተው ከመድረክ ያስተዋወቋት እሳቸው ናቸው፡፡ ምንሊክን የመጀመሪያ ሙዚቃውን “አልማዝ እያሰብኩሽ ዘወትር” የደረሱለት እሳቸው ነበሩ፡፡ እርጅና የማይበግረው የማስታወስ ችሎታ የተሰጣቸው አረጋዊው ጌታቸው ከብሄራዊ ቴአትር ውጭ ያለችው አዲስ አበባ አዲስ አበባ አትመስላቸውም፡፡ ለእሳቸው አዲስ ቀን ማለት የብሄራዊ ቴአትር መናፈሻ ውስጥ ካለችው ፔፒሲ ስር ሂዶ ከአምሰት ስዓት እስከ ስምንት ስዓት አረፍ ማለት ነው ፡፡ ሁለት አስርታትን እዛች ቦታ ተቀምጠው ከትዝታቸው ጋር ተሟግተዋል፡፡ ትውስታቸውን አውግተዋል፡፡ ለአዕላፍ ተመራማሪዎች ሳይሰስቱ መረጃ ሰጥተዋል፡፡

ጌታቸው በዘመናቸው ትልቅ መድረክ መሪ ነበሩ፡፡ በእሱ ተጋብቶባቸውም ይሆናል ጨዋታቸው ይጣፍጣል፡፡ ደግሞም አንደ ጎግል የትኛውም የዘመናቸው የኪነ-ጥበብ ባለሙያ ሲነሳ ሙሉ መራጃ ይሰጣሉ፡፡ አንድ ወቅት ስለ ጥላሁን ገሰሰ ሞት ስናወራ ፡፡ ጥላሁን ለሀገሩ ከስራው ነገር ሩቡም አልተወራለትም አሉኝ፡፡ እንዴት? አልኳቸው፡፡ “የቀይ ኮከብ ዘመቻ ጊዜ ታዋቂ ድምጻዊያን ወደ ስፍራው አምርተው ስራቸውን እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ተሰጥቶ ነበር፡፡ በጊዜው ጥላሁን ሆስፒታል ነበር፡፡ ግን ደርግ በእናት ሀገር ቀልድ የለም ብሎ ከሆሲፒታል አልጋ ላይ አስነስቶ ከቡድኑ ጋር ወደ ኤርትራ ክፍለ ሀገር ላከው፡፡ የሀገር ጉዳይ ግዴታ ነው ተብሎም ከኦርኬስትራው ጋር ከመድረክ አቆመው ፡፡ ጥላሁን ጥቂት ከዛዜመ በኋላ ከጉሮሮው ደም ይፈሰው ጀመር፡፡ ብዙዎቻችን ብንደናገጥም እሱ ግን ስለሀገሩ እያዜመ ስለነበር ነገሩን ከቁም አልቆጠረው፡፡ ”

ሌላ ቀን ከወሬ ወሬ ስለ ማርያም አኬባ ጨዋታ ስንጀመር ጋሽ ጌታቸው እንደተለመደው አስገራሚ ታሪክ ይነግሩኝ ጀመር፡፡” በነገርህ ላይ ማርያም አኬባ አዲስ አበባ ላይ እየዘፈነች የመድረክ መጋረጃ ዘግተንባታል አሉ ፡፡” ሁሌም አንደማደርገው ለምን ?የሚል ጥያቄ አስከተልኩ፡፡ የአፍሪካ አንድነት ደርጅት ምስረታ ሲካሄድ መሪዎች በተገኙበት የተለያዩ ድምጻዊያን ስራዎቻቸውን ያቀርቡ ነበር ፡፡ ከእነዚህ መካካል ማሪያም አኬባ አንዷ ነበረች፡፡ ተራዋ ሲደርስ ወደ መድረክ የወጣቸው አኬባ ቶላ የምትወርድ አልሆነችም፡፡ ዘፈኗ ቢባል ቢባል አላልቅ አለ፡፡ በዚህ የተበሳጩት የወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስተር ግርማቸው ተክለሃዋርያት ይኽማ መሪዎችን መናቅ ይመስላል ብለው እየዘፈነች መጋረጃውን ዝጉት አሉ፡፡ አማራጭ አልነበረም ፡፡ እየዘፈነች መጋረጃውን ዘጋንባት ፡፡

ፀሀፈ ተውኔተ፣የቴአትር አዘጋጅ ፣የሙዚቃ ግጥም ደራሲው ጌታቸው ደባልቄ ትውስታዎቻቸውን ጥለው ላይመለሱ አሸልበዋል፡፡ የእሳቸው ሞት የአንድ ግለሰብ ብቻ ሳይሆን የአንድ ቤተ-መዘክር ውድመት ነው፡፡ ግን አሁን ስዓቱ የስንብት ነው ፡፡ ደና ሁን ጋሼ ጌች፡፡ ደና ሁን ያባቴ ሞግሼ!ደና ሁን ………!

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** የተለያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዝኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close