Connect with us

Ethiopia

የደህንነት ሥጋት ያጠላበት የሀገራችን ፖለቲካ 

Published

on

የደህንነት ሥጋት ያጠላበት የሀገራችን ፖለቲካ

የደህንነት ሥጋት ያጠላበት የሀገራችን ፖለቲካ  | በሬሞንድ ኃይሉ

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተደጋግሞ እንደተገለጸው መንታ መንገድ ላይ ቁሟል፡፡ የአመራር ሽግግር ከተደረገ በኋላ ወራት መጥተው ወራት ቢነጉዱም ሀገሪቱን ከመንታው መንገድ ፈቅ ለማድረግ አልተቻላቸውም፡፡ ይህ ደግሞ በህዝቡ ላይ ተጨማሪ የስጋት ወራት እንዲሰፍኑ ዕድል ፈጥሯል፡፡ ዛሬ የክልል አመራሮች ከፖለቲካዊ ንትርክ ከፍ ብለው ለጦርነትም ቢሆን አናንስም የሚል ዛቻ ማሰማት ጀምረዋል፡፡ ህገ-ወጥ መትረየስ የታጠቁ መኪኖች በቁጥጥር ስር ዋሉ የሚሉ ዜናዎችን የአዘቦት ወሬ ሁነዋል፡፡

በአንዳንድ አከባቢዎች የመንግስት መዋቅር የፈረሰ ይመስል የጦር መሳሪያ ንግዱ በገሃድ የሚታይ ሆኗል፡፡ በክልል ከተሞች የሚኖሩ ወዳጆቼ እንደነገሩኝ ከሆነ ደግሞ በአንዳንድ ከተሞች የምሽት የጦር መሳሪያ ንግዱን ተከትሎ የሚካሄደው የመሳሪያ ተኩስ ነዋሪውን እንቅልፍ እየነሳው ነው፡፡ ክልሎች እርስ በእርስ ለመዋጋት በድብቅ ልምምድ ላይ ናቸው የሚል ወሬ እውነትም ይሁን ውሸት መስማት መለመዱ ያሸብራል፡፡ የዜጎችን ሀገራዊ ተስፋ ይነጥቃል፡፡ የዜጎች ስሜታዊ ውህደት የሌላት ሀገር ደግሞ እንደ ሀገር ለመቀጠል ያስቸግራታል፡፡

በሰሜንም ሆነ በደቡብ ያለ ሰው ቢያንስ ኢትዮጵያዊ በሚያደርገው እንድ ጉዳይ ላይ ሊግባባ ይገባው ነበር፡፡ አሁን ግን እሱ ያለ አይመስለም፡፡ ይህን ጽሁፉ በማዘጋጅ ስዓት አንድ የሀገራችን መገናኛ ብዙሃን ብሄርተኛ ፖለቲከኞችና ዜጎች የአዕምሮ ችግር ያለባቸው ናቸው የሚል ዜና እያሰማ ነው፡፡ ሌላው በአንጻሩ ብሄሬ ካልተከበረ ሌላው ጥንቅር ብሎ ይቅር የሚል አቋም ያራምዳል፡፡የዚህ ሁሉ ሰንክሳር መጨረሻው የት ሊሆን ይችላል? አሸናፊነቱስ የማን ነው?

ከመጀመሪያው ጥያቄ እንነሳ፡፡ ወቅታዊው የኢትዮጵያ ፖለቲካ መንታ ምሰል ያለው ነው፡፡ በአንድ ጎኑ የሀገሪቱን ፖለቲካ ወደ ተሸለ ደረጃ ለማድርስ ይረዳል፡፡ ሳሙኤል ሀንቲንግተን እንደሚገልፀው ሀገራዊ አለመረጋጋቶች ፖለቲካን ለማዘመን ወሳኝ ሚና አላቸው፡፡ ለዚህ ሩቅ ሳንሄድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን የመጡበትን መንገድ ብቻ መመልከት ይቻላል፡፡

ህወሓት መራሹ ኢህአዴግ ከዙፋኑ የወረደው በህዝባዊ እንቢተኝነት ነው፡፡ ባለፉት ጥቂት ወራት የታየው ተስፋ የመጣውም ከዚህ ሀገራዊ አለመረጋጋት በኋላ ነው፡፡ የፈረንሳይና አሜሪካ ዴሞክራሲ የፈነጠቀውም በግጭት ውስጥ መሆኑ አያከራክርም፡፡

ይሁን እንጅ ፖለቲካን ለማዘመን ግጭትና አለመረጋጋት የግድ አይደለም፡፡ በመካከለኛው ዘመን በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ቀዳሚ የነበረችው ሆላንድ ከባድ የፖለቲካ ምስቅልቅ ለታላቅነቷ አረዳትም፡፡ የእንግሊዝ የኢንዱስትሪ አብዮትም ጦርነት ብቻ የወለደው አልነበረም፡፡ ግጭተ ፖለቲካን ለማዘመን መርዳቱ ባያከራክርመ ከንቱ ድካም የሆነባቸውም ሀገራት አሉ፡፡ ለዚህ ደገሞ የራሳችን ሀገር ማሳያ ናት፡፡ ኢትዮጵያ ተደጋጋሚ ውስጣዊ ግጭቶችን ብታስተናግድም የረባ የፖለቲካ ዕደገትን አላስመዘገበችም፡፡ ታዋቂው የኢትዮጵያ ፖለቲካ አጥኝ ክርስቶፈር ክላፋም ከዚህ በኋላ ስለዚች ሀገር ዕጣ ፋንታ ለመናገር አልደፍርም ያለውም አለመረጋጋቶቹ ለፖለቲካችን ጠብ የሚያደርጉት ነገር ባለመኖሩ ነው፡፡ እንዲህ ያለው የተመሰቃቀለ እውነት ታዲያ ወቅታዊው የሀገራችን ፖለቲካዊ ጡዘት መዳረሻው የት እንደሚሆን እንዳንገምት ያደርገናል፡፡

የምስራቅ አፍሪካዋ ግዙፍ ሀገር የነውጥና ለውጥ እንቅስቃሴ መዳረሻው የት እንደሆነ ባይታወቅም የግጭት አሸናፊዎቹን ግን መተንበይ ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው በኢትዮጵያ አለመረጋጋት በለስ የሚቀነቸው ወገኖች ጎረቤት ሀገራት ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ከሁሉም ጎረቤቶቿ ጋር በደም የተሳሰረች ሀገር ናት፡፡ ሱማሌ ግማሽ አካሉ ሱማሊያ ነው፡፡ አኝዋከና ኜዌርም በተመሳሳይ ኢትዮጵያም ደቡብ ሱዳን ውስጥ ይገኛል፡፡ ትግረኛ ተናጋሪ ከመረብ ወዲህ ብቻ ሳይሆን ማዶም ተንሰራፍቷል፡፡ ይህ ድንበር ዘለለ የሆነ የብሄሮች ትስስር ኢትዮጵያ መረጋጋት በሚሳናት ስዓት ተጎጅ እንደትሆን ያደርጋታል፡፡ በኢትዮጵያዊነታቸው ተስፋ ያጡ ብሄሮች ሌላ ሀገር ጋር መቀላቀልን አልያም አዲስ መመስረትን እንዲሰቡም ይገፋፋል፡፡

ይህ መከራከሪያ በምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ውስጥ የተለመደ ነው፡፡ 30 ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በዚህ ቀጣና ሁለት አዳዲስ ሀገራት ተፈጠረዋል፡፡ ኤርትራና ደቡብ ሱዳን ከእናት ሀገራቸው መመነናቸው ለዚህ አብነት ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለገኘችው ሱማሌ ላንድም በዋናዋ ሱማሌያ ተስፋ መቁረጥ የፈጠራት ሀገር ናት፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵየያ ፖለቲካ አለመረጋጋት ወደ ግጭቶች የሚያመራ ከሆነ ጎረቤት ሀገራት ከታላቋ ኢትዮጵያ ጥላ የመላቀቅ ዕድል ይፈጥርላቸዋል፡፡ ኃያለኑ ሀገራትም አፍሪካዊት ሶሪያን ለመፍጠር ይመቻቸዋል ፡፡ ጸጋየ ገ/መድህን አንደሚለውም ዳሩ ሲነካ መሃሉ ዳር አንዲሆን ያደርጋል፡፡

የሀገራች ፖለቲካ በዚህ ከቀጠለ ሌላው ተጠቃሚ የሚያደርገው የፖለቲካ ነጋዴዎችን ነው፡፡ ኢትዮጵያ የረባ ነዳጅ ባይኖራትም አንድ መቶ ሚለዮ ህዘብ አላት፡፡ ይህ ህዝብ ለፖለቲካ ንግድ የተመቸ ነው፡፡ በዚህ ሀገር የመንግስት መዋቅር ቢፈራርስ በርካታ ሚሊየነሮች ቢሊየነር ይሆናሉ፡፡ አሌክስ ዳዋል የሱማሌያ መንግስት አልባ መሆን ለህገ-ወጥ ገንዘብ አዘዋዋሪዎች ምቹ ዕድልን እንደፈጠረ ያወሳል፡፡ ደሀብሽልን የመሰሉ ዓለማቀፍ የገንዘብ አዘዋዋሪዎች ለመፈጠራቸው አንዱ ምክንያትም መንግስት መዳከሙ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ሱማሌያ ወደ ኬንያ በሚሊዮን የሚቆጠር ኩንታል ከሰል ብትልክም ለመንግስቱ ጠብ የሚል ነገር የለም፡፡ ህገ-ወጦች የራሳቸውን ሀገር መስርተው በባይደዋ በኩል ከጀመሩት ንግድም እስካሁን የሚያስቆማቸው አልተገኘም፡፡ በደቡብ ሱዳን ያለው የመሳሪያ ንግድም የግጭት ነጋዴዎች እንዲከብሩ አድርጓል፡፡

ከላይ ያነሳናቸው ሁለት ቀላል ማሳያዎች ህዝብ ከፖለቲካዊ ግጭቶች እንደማያተርፍ ያሳያል፡፡ በተለይም በምስራቅ አፍሪካ ግጭት ፖለቲካን ለማዘመን እንደማይረዳም ያረጋግጣል፡፡ እንዲህ ከሆነ ኢትዮጵያዊያን ዛሬ ላይ ወደ ተካረረ ፍጥጫ ለመግባት የተዘጋጀነው ለምንድን ነው? ብለን እራሳችንን እንድንጠይቅ ያደረገናል፡፡ አሸናፊ የሌለው ጦርነትስ ማንን ይጠቅማል? ማንንም፡፡ እንዲህ ከሆነ የምንታገለው ለሀገራችን ሳይሆን ለፖለቲካ ነጋዴዎች ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ትርፉን የዜሮ ብዜት ያደርገዋል፡፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** ኢትዮ ጵያን የተመለከቱ የተለያዩ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዘኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close