Connect with us

Ethiopia

አዲሱ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ኃይል አሰላለፍ! | ሬሞንድ ኃይሉ

Published

on

አዲሱ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ኃይል አሰላለፍ! | ሬሞንድ ኃይሉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ኃይል አሰላለፍ! | ሬሞንድ ኃይሉ @DireTube

የኢትዮጵያ ፖለቲካ እየተናጠ ነው፡፡ መናጡ ምን እንደሚያወጣ ግን ማንም እርገጠኛ አይደለም፡፡ ወዲያ ህወሓት በፌደራል መንግስቱ ክህደት ተፈጽሞብኛል ትላለች፡፡ ወዲህ የኦሮሞ ፖለቲካ ልሂቃን ቅራኔያቸውን በማጥበብ ላይ ተጠምደዋል፡፡ የአማራ ፖለቲካ ባለፈው ሳምነት መገባደጃ በደብረ ማርቆስ ከተማ ለአርበኞች ግንቦት ሰባት ፓርቲ ከተደረገው አቀባበል በኋላ ለመገምት አዳጋች ሁኗል፡፡ ይህ ወቅታዊ ስንክሳር መዳረሻው የት እንደሆነ ባይታወቅም ቀጣዩን የፖለቲካ አሰላለፍ ለማወቅ ፍንጭ ይሰጣል፡፡

ህወሓት ምን ታስባለች?
ህወሓት መራሹ ኢህአዴግ አሁን የለም፡፡ በፖለቲካ የሚሆነው ባይገመትም በአጭር ጊዜም ሀገር ወደ ማስተዳደር ይመለሳል ተብሎም አይጠበቅም፡፡ ይህን እውነት ህወሓት እራሷም የምትረዳው ይመስላል፡፡ እንዲህ ከሆነ መቀሌ ያለው የፖለቲካ ልሂቅ ፍላጎት ሰልጣን መልሶ ከመንጠቅ ይልቅ ስልጣን የያዘውን ቡድን ቅቡልነት መሸርሸር እንዲሁም የትግራይን ክልል ጥቅም በሚችለው አቅም ማስከበር ናቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ ህወሓት የኢትዮጵያ ህዘብ የፌደራል መንግሰቱን በጥርጣሬ እንዲመለከተው የሚያደርጉ መግለጫዎችን ሳታሰልስ እያወጣች ትገኛለች፡፡

ማዕከላዊ መንግሰቱ ለፌደራሊዝሙና ህገ-መንግስቱ ቁብ እንደሌለውም አስታውቃለች፡፡ እንዲህ ያለው ከመቀሌ የሚነሳ ሀሳብ ለኦዲፒ የህልውና ስጋት እንደሚሆን አየጠራጥርም፡፡ ምክንያቱም የኦዲፒ ፖለቲካዊ መሰረት ማጠንጠኛው እውነተኛ ፌደራሊዘምና ህገ-መንገስት ነው፡፡ የኦሮሞ ፖለቲካ ልሂቅ ሰልጣን ላይ ያለው ኃይል ለፌደራሊዝም ደንታ የለውም ብሎ ካሰብ ኦዲፒን መቃወም እንደሚጀምር ይገመታል፡፡

ሌላው ህወሓት በመገለጫዋ ታሳቢ ያደረግቸው ጉዳይ የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው የሚለውን መርህ ይመስላል፡፡ የትግራይ ፖለቲካ ልሂቅ ከአማራ ፖለቲካ ልሂቅ ጋር የለየለት አተካራ ውስጥ ከገባ ሰነባብቷል፡፡ መቀሌ ባህርዳርን አህዳዊ ስርዓትን የሚናፍቁ ሰዎች መዲና አድርገ ስላታለች፡፡ ህወሓት ይህን አቋም ከሌላው በተለየ መንገድ ለማሰተጋባት የምትፈልገው የኦሮሞ ፖለቲካ ልሂቃንን በቀላሉ ከጎኗ የምታሰልፈበት መንገድም ስለሆነም ጭምር ነው፡፡ ይህ ደግሞ ህወሓት ለጊዜውም ቢሆን ጠቅሟታል፡፡ የኦሮሞ ፖለቲካ ልሂቃን ፌደራሊዝሙ ላይ አነደራደርም በማለት ከአማራ ፖለቲካ ልሂቃን መነጣላቸውም የዚህ ውጤት ነው፡፡

ኦዲፒ ምን እያደረገ ነው ?
ወቅታዊውን የአሮሞ ፖለቲካ ለተመለከተ ሰው የጀዋርን መሐመድን ተደማጭነት በቀላሉ የሚረዳ ይመስላል፡፡ ጀዋር ከወራት በፊት ከአዲስ ማለዳ ጋዜጣ ጋር በነበረው ቆይታ የሚከተሉትን ፍሬ ነገሮች ተናግሮ ነበር፡፡

አሁን ወደድንም ጠላንም ኦሮሞ ሀገር ማሰተዳደር ጀምሯል ፡፡ ይህ ደግሞ ለዘመናት መስዕዋትነት የተከፈለለት ትልቅ ድል ነው፡፡ ይህን ድል የኦሮሞ ፖለቲከኞች እርስ በእርስ በመዋጋት ከእጃችን እንዲወጣ ማድረግ የለበንም ፡፡ሁላችንም ለኦሮሞ ህዝብ አንሰራለን ካለን ተቀራርበን በመወያየት ልዩነታችንን ማስወገድ አለብን፡፡ ይህን የማያደርግ ካለ ግን እሱ ለኦሮሞ ህዝብ ይሰራል ለማለት ይቸግራል፡፡ (ቃል በቃል የተወሰደ አይደልም )

ጀዋር ከላይ ያለውን ሀሳብ በሰነዘረበት ቃለ-መጠይቁ የአሮሞ ፖለቲካ ልሂቃን ወደ አንድነት እንዲመጡ እየሰራ እንደሆነ ተናግሮ ነበር፡፡ ኦሮምያ ላይ በርግጥም አሁን የሚሰተዋለው ልዩነት መጥበብ የጅዋርን ፖለቲካዊ ስሌትና ተደማጭነት የሚያስመሰክር ይመስላል፡፡ በኦዲፒና ኦነግ ፍጥጫ ስትታመስ የነበረችው ኦሮሚያ በጀዋር መሪነት በአባ ገዳዎች ሽምግልና ዛሬ ላይ ወደ መረጋጋ እየተመለሰች ነው፡፡ ይህ ደግሞ ኦዲፒ ህወሓት ከዚህ በፊት የነበራትን አይነት ክልላዊ መሰረት እንዲኖረው ይረዳል፡፡ የኦሮሞ ፖለቲካ ልሂቃንም አንደ አንድ ሁነው በሀገራዊው የፖለቲካ መድረክ ላይ እንዲሰለፉ ዕድል ይፈጥራል፡፡

አዴፓ የት ነው ያለው ?
አማራ ዴሞክራሲዊ ፓርቲ አሁን ባላው የፖለቲካ አሰላለፍ ውስጥ የት እንደሚቀመጥ ለመገመት አዳጋች ነው፡፡ ይህ እውነት ግን ለክልሉ ገዥ ፓርቲ ብቻ ሳይሆን ለአማራ ፖለቲካ ልሂቃንም የሚሰራ ይመስላል፡፡ በዚህ ክልል የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ቡድኖች እርስ በዕርስ ለመደጋገፍ አይደለም ተቀራርቦ ለማውራት የሚያስችል የትግል ስትራቴጅ የላቸውም፡፡ በዚህ ምክንያትም የክልሉ ፖለቲካዊ መልካምድር የተበጣጠሰ ነው፡፡ የጋራ አጀንዳም የለውም፡፡

አዴፓ ሙሉ ትኩረቱን ጎንደር ላይ አድረጎ የውጭ ኃይሎች የሚላቸው ወገኖች ክልሉን እያተራመሱት መሆኑን ሲግጽ ፤አብን የህዝብና ቤት ቆጠራው ይራዘም ይላል፡፡ የቀረው የክልሉ ፖለቲካ ልሂቃም የአዲስ አበባ ባለቤትነት ጉዳይ እልባት እንዲሰጠው ይጠይቃል፡፡ ይህ የአማራ ፖለቲከኞች በየፊናው መጓዝ በክልሉ ህዝብ የጋራ ችግሮች ላይ መግባባት እንዳይኖርና መፍትሄም እንዳይመጣ ያደርጋል፡፡

ማጠቃልያ፡- ወቅታዊው የኢትዮጵያ ፖለቲካ በሀገሪቱ ታሪክ ውስጥ ያለው የሶስቱ ፈረሶች ፉክክር አሁንም መቀጠሉን ያሳያል ፡፡ መረራ ጉዲና (ፕ/ር)የሚጋጩ ህልሞች የሚሉት የአማራ፣ ትግራይና ኦሮሞ ፖለቲካ ዛሬም የየቅል ጉዟቸው ቀጥለዋል፡፡ ይህ ደግሞ ለሀገሪቱ ተስፋን ሳይሆን ስጋትን ያወርሳል፡፡ ትናንት በዚህ ጎዳና መጥተን እዚህ ከደረስን ነገስ ምን ይገጠመን ይሆን የሚል ጥያቄም ያጭራል፡፡

 

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close