Connect with us

Entertainment

ባንኮኔ ስር ወድቆ የተገኘ ማስታወሻ

Published

on

ባንኮኔ ስር ወድቆ የተገኘ ማስታወሻ | አሳዬ ደርቤ በድሬቲዩብ

ባንኮኔ ስር ወድቆ የተገኘ ማስታወሻ | አሳዬ ደርቤ በድሬቲዩብ

ከጥቂት ዓመታት በፊት ስኖረው የነበረውን ሕይወት አሁን ከምኖረው ጋር ሳስተያዬው እንዲህ የሚል ጥያቄ አነሳለሁ፡፡
በሱስ ጓዳ መሃል
ጨለማ ለኩሼ
የገነዝኩት ተስፋ፤
አንቺ ስትመጭ
እንዴት አንሰራራ
እንዴት ሆኖ ጠፋ?
.
ይሄንንም ሳብራራው… በዓመት ውስጥ ያሉትን 365 ቀናቶች የማሳልፋቸው ከቡና ቤት ባንኮኒ ላይ የማያቸውን መጠጦች ሁሉ እያስቀዳሁ በማንቃረር ነበር፡፡

በአንዳንድ ሌሊቶች ሶስት አራት አይነት አልኮል አዋህጄ እጠጣና እንደ ሎብሳንግ ራምፓ እንሳፈፋለሁ፡፡ በዝግመተ-ለውጥ የኋሊት ተጉዤ ወደ ዝንጀሮነት በመመለስ በእጆቼና በእግሮቼ እድሃለሁ፡፡ በልሳን አወራለሁ፡፡

ሱሪዬን ዝቅ አድርጌ ባርና ናይት ክለብ መታየት እንደ ጀመርኩ ሰሞን የሚሸጥ ዳሌ ጨምድዶ መውረግረግ ያስደስተኝ ነበር፡፡ ነበልባል ነፍሴም የዳንኪራ እና የአስረሽ ምችው ምርኮኛ ነበረች፡፡

እናም ደሞዝና አበል የተቀበልኩ ቀን በጎርደን፣ በጉደርና በቢራ፤ በአዘቦት ቀናት ደግሞ በጅን፣ በኡዞ፣ በአረቄ፣ …. ጨጓዬን ሳቆስለውና አዕምሮዬን ሳቃውሰው ከኖርኩ በኋላ ባላሰብኩት ቀን ወደ ሕይወቴ የገባች ሴት ይሄንን ሕይወቴን ለወጠችው፡፡

እናም ከዚያን ቀን አንስቶ ባሉ ምሽቶች በብረታ-ብረት ፈንታ እንደ እመጫት ሻሜትና አጥሚት እየጠጣሁ ራሴን እጅ ከፍንጅ ስይዘው ትንታ ያራውጠኛል፡፡ ቡና-ቤት ተገኝቼ በምውረገረግበት ሰዓት ከቤቴ ገብቼ ዜና እየተመለከትኩ መሆኔን ስረዳ ባንኮኔ ፍለጋ ዓይኔን አቅበዘብዝዋለሁ፡፡

ያኔ ብዙ ገንዘብ አገኝ ነበር፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ኑሮው እንደ አሁኑ ውድ አልነበረም፡፡ ሆኖም ግን የኪሴ መሙላት ሱሴን ከማሟላት ውጭ ፋይዳ አልነበረውም፡፡ ምናልባት ከጫትና ከአልኮል የሚተርፍ ገንዘብ ካገኘሁ መጽሐፍ እገዛ ይሆናል፡፡ አሁን እድሜ ለእሜቴ በበርጫ ፈንታ የምገዛው በግ ሁኗል፡፡ በመጽሐፉም ምትክ የምሸምተው የልጅ ደብተር ከሆነ ቆዬ፡፡

ይሄም ሆኖ ግን ምርቃና በማጧጡፍበት ሰዓት በግ ተራ ላይ ተገኝቼ ‹‹የመጨረሻ ዋጋውን ቁርጥ አድርገህ ንገረኝ›› እያለ የሚዘበዝብ አዲስ ማንነት ሳገኝ እፍረት ይይዘኝና ከበጎቹ መሃከል መደበቅ ያምረኛል፡፡

ወንደላጤ እያለሁ ካልሲ ከማጠብ ይልቅ መግዛትን እመርጥ ነበር፡፡ ሰይጣን አሳስቶኝ ሳቸፈችፍ ብገኝ እንኳን ከአንድ ጥንድ ካልሲ ውጭ አጥባለሁ ማለት ዘበት ነው፡፡ አንድ ቀን እንደውም ያጠብኳቸውን ካልሶች ላሰጣ ስል የተለያዩ ሆነው አገኘኋቸው፡፡ ከዚያም የሁለቱንም ካልሶች አጣማጅ ፈልጌ ከማጠብ ይልቅ አንዱን እርጥብ ካልሲ ከቋንጣዎቹ ጋር ቀላቅዬ ያንዱን ብቻ አለቅልቄ ማስጣቴን አስታውሳለሁ፡፡ ታዲያ እንዲህ ያለው ሰነፍ ወጣት አሁን አባት ሆንኩኝ ብሎ የልጆቹንና የሚስቱን ልብስ ውሃ ውስጥ ዘፍዝፎ እያቸፈቸፈ ሳገኘው ‹‹ቂቂቂቂቂ›› የሚል ሳቅ ያመልጠኛል፡፡

ዘልዛላ ሳለሁ የባለቤቴ ጓደኞች እኔ ጋር ግንኙነት መመስረቷን ሲሰሙ ‹‹ምን ነካት?›› ከሚል ጥያቄ ጋር ጤነኝነቷን ተጠራጥረው ነበር፡፡ ከዚህም አልፈው ዝልግልግ አክታቸውን ከመሬት ላይ በመትፋት ‹‹ይች ምራቅ ከመድረቋ በፊት ከዚህ ወመኔ ጋር ያልተለያየሽ እንደሆነ ሰው ብለሽ አትጥሪን›› እያሉ ወደ ትዳር እንዳትገባ ሲመክሯት ነበር፡፡ ሳትሰማቸው ቀረች እንጂ!

ታዲያ እነዚህ መካሪዎቿ የተፏት ምራቅ መድረቅና አለመድረቋን እየተከታተሉ መቃሚያ ቤት ወይንም ደግሞ ቡና ቤት ውስጥ የምገኝበትን ቀን ሲጠባበቁ ሱፐር-ማርኬት አካባቢ ስዘዋወር አዩኝ፡፡ ከቤታችን በመጡ ጊዜም ጫት በመቅጠፍ ፈንታ ሽንኩርት ስከትፍ አገኙኝ፡፡ ሬስቶራንትና ባር በምቀያይርበት ሠዓትም የልጄን ዳይፐር ስቀይር ተመለከቱ፡፡ ይሄንንም ሁኔታ ያስተዋሉ ቁሞ-ቀር ጓደኞቿ ‹‹ምን አይነት መተት ብታስነካው ይሆን ያንን የመሰለ ልጅ እንዲህ ያበላሸችው›› እያሉ ይጠያየቁ ያዙ፡፡ ጤነኝነቴም ያጠራጥራቸው ጀመር፡፡

አልፎ አልፎ ዓላማ የለሽ ስካር ማስተናገድ ሲከብደኝ በአማላጅም ሆነ በግዳጅ የሚጣላኝ ሰው አፈላልጌ ጠርሙስ እወራወር ስለነበር የፈነከትኩባቸውና የተፈነከትኩባቸው ሌሊቶች ቁጥራቸው ቀላል አልነበረም፡፡

አሁን ላይ ታዲያ አምባጎሮ የሚወደው ጎረምሳ በአንዲት ቀጫጫ ሴት ቁጥጥር ስር ወድቆ በግልምጫዋ እየተርበደበደ ሲገኝ በጣም አድርጎ አያስገርምም?

ወንደላጤ እያለሁ ደሞዜን በተቀበልኩበት ቀን የዱቤ መዝገብ ከያዘች ኮማሪት ፊት ለፊት ቁጭ ብዬ የጠጣሁትን አልኮልና የበላሁትን እህል አሰላ ነበር፡፡ ለምሳሌ ያህል ‹‹ሰርኬ›› የተባለች የሬስቶራንት ባለቤት ዱቤዬን ቁልቁል ስትደምር ቆይታ ‹‹የመጠጡ 800 ብር፤ የምግቡ ደግሞ 120 ብር በድምሩ 920 ብር›› ስትለኝ ‹‹የምግቡ 120 ብር የሞላው ምን ምኑን ስበላው ከርሜ ነው?›› እያልኩ እሞግታት ነበር፡፡

እናም በተወሰኑ ዓመታቶች ውስጥ ያ የልቆ የሚወድ ሰውዬ በደሞዙ ቀን የአስቤዛ ደብተር ከያዘች ሚስቱ ጎን ተቀምጦ ‹‹ቁብ ሁለት ሽህ ብር፣ ወርሐዊ ቁጠባ አንድ ሺህ ብር፣ የጤፍ መግዣ 800 ብር›› ስትለው ‹‹የባለፈው 25 ኪሎ ጤፍ ከምኔው አለቀ?›› የሚል ጥያቄ ሲያነሳ ቢገኝ ሌላ ሰው እንጂ ያ ዱቤያም ወጣት ነው ብሎ ለመገመት አይከብድም?

ፖፖ ተነተርሶ፣ ሲጋራ ነክሶ በጭስና በፈንገስ መሃከል በፍጹም ጤንነት ሲኖር የነበረ ወንደላጤ… አሁን ‹‹ሚስት አገባሁ ብሎ›› በንጹህ መኝታ ቤትና ዝባድ፣ ዝባድ በሚሸት አንሶላ መሃከል አስም አፍኖት ሲገኝ ‹‹ማርጧል›› እንጂ ‹‹ታፍኗል›› ብሎ የሚያስብለት ይኖር ይሆን?

በዚያ እረፍትና እምነት አልባ ዘመኔ ከጫትና ከመጠጥ ቤት ተቀምጬ ሳስበው አምላክ እንደሌለ ይሰማኝ ነበር፡፡ በማሰብ ያጣሁት አምላክ በንባብ ቢገኝ ብዬ ‹‹ፈጣሪ የለም›› ከሚሉ መጽሐፍቶች መሃከል ፈጣሪን እንደ ጉድ አፈላለኩት፡፡

ከዚያም ‹‹የለም›› የሚለውን የፈላስፎች ድምዳሜ ይዤ መጽሐፍ ቅዱሱን ገለጥኩት፡፡ ሆኖም ግን ዋነኛ ፍላጎቴ ማጣት እንጂ ማግኘት ባለመሆኑ የፈጣሪ መገኛው እንደ ኦሪት ዘመን እራቀኝ፡፡ የመገላገል ስሜትም ተሰማኝ፡፡

ውዷ ባለቤቴ ግን በስንት ንባብ ያገኘሁትን እጦቴን ያለምንም ስብከት በልጄ አማካኝነት አምክናው ተገኘች፡፡ ስለዚህም የዓይን መግለጫ ሲጋራ ለኩሼ ስካር የሚያጠፋ ሽሮ ፍትፍት በማፈላልግበት ማለዳ ጋቢ ለብሼ ቤተስኪያን ውስጥ ራሴን ሳገኘው ሰኔ ጎለጎታዬን ፈገግ ብዬ ማንበብ እጀምራለሁ፡፡

‹‹እግዜር የለም›› በሚል አቋም አማኞችን በማጣጥልበት አፌ መንደር ለመንደር እየዞርኩ ‹‹የአቡዬን ጠበል ቅመሱልኝ›› ብዬ ስናገርበት ቃሉ የእኔ አልመስልህ እያለኝ ከትከሻዬ ላይ የተቀመጠ መላዕክት አፈላልጋለሁ፡፡ የቢራና የጅን ጠርሙስ በጨበጥኩበት እጄ ጸበል የያዘ ኮዳ ማንጠልጠሌን ስረዳ ቀስ ብዬ በጋቢዬ እሸፍነዋለሁ፡፡

የልጃቸው መበላሸት ያሳሰባቸው ወላጆቼ እኔን እና ሱሴን ለማለያየት ያላደረጉት ጥረት አልነበረም፡፡ በመጨረሻም እንደማልመለስ ሲገባቸው አባቴ ‹‹ምከረው ምከረው እንቢ ካለ መከራ ይምከረው›› ብሎ ሲተርትብኝ እማዬ ‹‹ወልደህ ቅመሰው›› ብላኝ ነበር፡፡
እናም በምክርም ሆነ በመከራ አልመለስ ያልኩት ሰውዬ በትዳር ልብ ገዝቼ የምጠላውን የአባቴን ምክር ልጄ ላይ እየተገበርኩ ሳገኘው የእናቴ ወልደህ ቅመሰው እርግማን ትዝ ይለኝና ልጄን ሱስ ከማይደርስበት ስፍራ ማስቀመጥ ያምረኛል›› እልሃለሁ፡፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** የተለያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዝኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close