Connect with us

Africa

የሱዳን አመጽና የአል በሽር መንገዳገድ

Published

on

የሱዳን አመጽና የአል በሽር መንገዳገድ | በኃይሉ ሚዴቅሳ ፍስኃጽዮን

የሱዳን አመጽና የአል በሽር መንገዳገድ | በኃይሉ ሚዴቅሳ ፍስኃጽዮን

ጁላይ1-1989 (እ.ኤ.አ) ማለዳ የኦምዱርማን ሬዲዮ በወታደራዊ ማርሽ ሙዚቃ ሱዳናዊያንን ከእንቅልፍ ቀሰቀሳቸው፡፡ እስከዚያች ጠዋት ድረስ በአገሬው ሕዝብ ምርጫ የነገሰው የጠቅላይሚኒስትር ሳዲቅ አል መሐዲ መንግሥት አገሪቱን እያስተዳደረ ነበር፡፡ ሆኖም በዚያች ቅዳሜ ጠዋት ሱዳንን ከእንቅልፍ ያባነነ ወታደራዊ ሴራ ፈነቀለው፡፡

ወታደራዊ መፈንቅለ-መንግሥቱን ያካሄዱት ሰዎች እስልምናን ከፊት አድርገው ‹‹የሱዳን ሉዓላዊነት ከአላሕ ነው›› ሲሉ አስተጋቡ፡፡ ሥራቸውም አገራቸውን ፍትሕ የሰፈነባት፣ሰላም የሞላባት ማድረግ እንደሆነ ገለጹ፡፡ ‹‹ሱዳን በአምላክ እንደተመረጠች ሁሉ በሰው ልጆች በሙሉ እንድትወደድ ማድረግም›› ሌላኛው ግባቸው መሆኑን አተቱ፡፡ ሐሰን አልቱራቢ ያስተባበሩት እስላማዊ ኃይልና ሐሰን አል በሽር የመሩት ወታደራዊ ጁንታ ተጋግዘው የሱዳንን ሕዝብ ከመረጠው መንግሥት ሥልጣን ነጠቁት፡፡

ቃል እንደገቡትም በሱዳን ሰላም ማስፈን ሳይችሉ ቀሩ፡፡ ጅምላ ጭፍጨፋ፣ እስር፣ ግርፋት፣ ሙስና… የሶስት አስርታት የሱዳን ፖለቲካ መገለጫ ሆኑ፡፡ በፕሮፌሰር አሌክስ ዲ ዋል ቋንቋ ሱዳን የደራች ‹‹የፖለቲካ ገበያ›› ሆነች፡፡ የአፍሪቃ ሶስተኛዋ የነዳጅ ዘይት ቀጣና ደቡብ ሱዳን ተገነጠለች፡፡ ተገንጥላም ከእናት ምድሯ ጸብ ፈጠረች፡፡ ዳርፉር ከመንግሥት ጋር ጦር ተማዘዘች፤ አል በሽርም በዓለማቀፍ ፍርድ ቤት ተከሰሱ፡፡ በአገራቸውም የሕዝብ ቁጥር በእጥፍ ሲጨምር የኑሮ ውድነትና የድህነት አሀዞች ተመነደጉ፡፡ 29 በጋዎችን የዘለቀው የአልበሽር አገዛዝ አሁን ሱዳናዊያንን ለአደባባይ ተቃውሞ ዳርጓል፡፡

አመጹ የት ይደርሳል?!

የአመጹ ፍፃሜ የት እንደሆነ አይታወቅም፡፡ ሆኖም ጠንክሮና አፍጥጦ መውጣቱ እውን ሆኗል፡፡ ይሁን እንጂ አመጹ በተደራጁ ኃይሎች የሚመራ ባለመሆኑ፣ ስትራቴጂካዊ ዓላማዎችን የቀረፀ አለመሆኑና በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ትልቅ ሚና ያለው ጦሩ ከአል በሽር ጎን መቆሙ የፕሬዚዳንቱን ፍፃሜ ሊያዘገየው ይችላል፡፡ ያልተደራጀ አመጽ፣ በፍኖተ-ካርታ የማይመራ አብዮት ደግሞ ትክክለኛውን የሕዝብ ጥያቄ ነጥቆ የራሱን አምባገነናዊ ሥርዓት ሊያነብር ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ ከ1967ቱ የኢትዮጵያ አብዮት በኋላም ሆነ ከ2013ቱ (እ.ኤ.አ) የግብጽ አመጽ ወዲህ ታይቷል፡፡

እናም አል በሽር ያልተደራጀውን የአመፃ ኃይል በጠብ መንጃ እያስታገሱና እያሰሩ እስከ 2020 (እ.ኤ.አ) ምርጫ ድረስ ችግሩን ሊያሻግሩት ይችላሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ወደ ምርጫ ከተገባ ደግሞ አል በሽር በድጋሚ አሸንፌያለሁ ቢሉ ተደራጅተው ወደ ውድድር የሚገቡት ‹ተሸናፊዎች› አመጹን ካቆመበት ሊያስቀጥሉት ይችላሉ፡፡ ያኔ ሐሰን አል በሽር ወይ እንደ ቤን አሊ ስደት አለያም እንደ ሙባረክ እስር ወይም ከከፋ እንደ ጋዳፊ ሞት ሊገጥማቸው ይችላል፡፡ ወይም ደግሞ ፓርቲያቸው በሠራዊቱ የሕቡዕ ድጋፍ ጠንካራ ማሻሻያ አድርጎ አል በሽርን ገለል በማድረግ የጦሩ ይሁንታ የተቸረው አንድ ሰው ወደ ፊት ሊያመጣ ይችላል፡፡ እንደዚያ ከሆነ አል በሽር እንደ ሙጋቤ ያለ እጣፈንታ ሊገጥማቸው ይችላል፤ ጡረታቸው ተከብሮላቸው ዝም ብለው እንዲኖሩ ይደረጉ ይሆነናል፡፡እንደ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ተሸልመው እንደማይሸኙ ግን በርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡

በራሷ ፖለቲካ ውጣውረድ ውስጥ ያለችው ኢትዮጵያ ይህንን የሱዳንን ጉዳይ እንዴት እየተከታተለችው እንደሆነ የሚያሳይ መግለጫ ከመንግሥት በኩል አልወጣም፡፡ ‹‹በሉዓላዊ ሀገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አንገባም›› እንደሚል ግን ይጠበቃል፡፡ ይሁን እንጂ አንድ ግዙፍ ችግር እንደተደቀነ መካድ አይገባም፡፡ ከአልበሽር በኋላ የኢትዮ-ሱዳን ግንኙነት የሚገጥመው ሳንካ ምን እንደምመስል ከወድሁ መገመቱ አስቸጋሪ ይሆናል።

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** የተለያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዝኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close