Connect with us

Ethiopia

የአሰብ ወደብ ስራ በሲዲ ሊመረቅ ነው

Published

on

የአሰብ ወደብ ስራ በሲዲ ሊመረቅ ነው

በ1950አ.ም በአሰብ የወደብ ፕሮጀክት ላይ በዋና መሀንዲስነት ያገለገሉት አቶ በየነ ወልደገብርኤል የጻፉት ማስታወሻ ፣ በኦድዮ ሲዲ ተተርኮ የፊታችን እሁድ የካቲት 10 2011 በብሄራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጽሀፍት ኤጀንሲ አዳራሽ ይመረቃል፡፡

የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አወል ወግሪስ የክብር እንግዳ ሆነው በሚታደሙበት በዚህ ምረቃ ላይ ለሀገራቸው ውለታ የዋሉ ታላላቅ እንግዶች ይታደማሉ፡፡

የዚህ ኦድዮ ሲዲ አሳታሚና ፕሮዲዩሰር እዝራ እጅጉ ሙላት ሲሆን የቅንብሩ ተራኪና አርታኢ ዶክተር ጌታቸው ተድላ ናቸው፡፡ የወደብ መሀንዲሱ አቶ በየነ ወልደገብርኤል ይህን ሀገራዊ ግዴታ ለመወጣት አሰብ ሲያቀኑ የ27 አመት ወጣት ነበሩ፡፡

26 ሚልዮን ብር እንደፈጀ የሚነገርለት ወደብ በ1950 ጥር ወር ላይ ስራው ሲጀመር መሀንዲሱ በየነ ወልደገብርኤል ለሀገራቸው አንድ ውለታ ለመዋል ቁርጥ ውሳኔ አድርገው ነበር፡፡ ያ ወደብ 5 አመታትን ወስዶ ከተጠናቀቀ በኋላ ዛሬ 88 አመታቸው ላይ ያንን ታሪካዊ እውነት በማስታወሻቸው ላይ አስፍረው ነበር፡፡ ይህ ከዚህ ቀደም ብዙ ያልተወራለት የአሰብ ወደብ አሰራር ታሪክ በአቶ በየነ ሲነገር ብዙ እውነታዎችን ይዟል፡፡ ይህ በመጽሀፍም ሆነ በየትኛውም ሚድያ ያልወጣ ታሪክ በኦድዮ ሲዲ ታትሞ ሲወጣ ብዙዎችን መረጃ ያስጨብጣል ተብሏል፡፡

የዚህን ኦድዮ ሲዲ ሙሉ ወጪ በመቻል ያሳተመው ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን ሲሆን ካሁን ቀደም የ13 የሀገር ባለውለታዎችን ታሪክ በሲዲ ማሳተሙ ይታወቃል፡፡

የድርጅቱ መስራችና ኤክስኪዩቲቭ ፕሮዲዩሰር እዝራ እጅጉ ይህ በ 1 ሰአት በሲዲ የሚወጣ ታሪክ ለማሳተም ሲነሳ ዋናው ግቡ ለኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ክብር ለመስጠት በማሰብ ነው፡፡ እንደሚታወቀው በሀገራችን በቀደሙት ጊዜያት ታላላቅ ግንባታዎች፣ ህንጻዎችና ግድቦች ሲሰሩ የውጭ ሀገር ባለሙያዎች ስም ከፍ ብሎ ይጠራል፡፡ አሊያ የሰራው ኩባንያ ስም በስፋት ይነሳል፡፡ ‹‹ይህ ቁጭት ውስጥ የሚከት ነው›› የሚለው እዝራ እኩል ከፈረንጆቹ ጋር የደከሙ ኢትዮጵያውያን አይታወሱም፡፡ ይህን ታሪክ ለመለወጥ የአቶ በየነን ሚና በሲዲ አጉልተን አውጥተናል ሲል ተናግሯል፡፡

በአቶ በየነ ወልደገብርኤል የተጻፈ ታሪክ ጣዕም ባለው ድምጻቸው ተርከው ያቀረቡት በተባበሩት መንግስታት በእርሻ ባለሙያነት ለአመታት ያገለገሉት ዶክተር ጌታቸው ተድላ ናቸው፡፡ በህዳር ወር 1954 የአሰብ ወደብ ፕሮጀክት በንጉሰ-ነገስቱ በድምቀት የተመረቀ መሆኑን ታሪክ የሚነግረን ሲሆን የታቀደለትን ያህል ጊዜ ሳይቆይ ከተመደበለት በጀት ባነሰ ዋገገ መጠናቀቁ ይታወቃል፡፡

አቶ በየነ ወልደገብርኤል ይህን ‹‹የአሰብ ወደብ ስራ›› የተሰኘውን ጽሁፍ ሲጽፉም ሆነ በሲዲ እንዲቀርብ ሲፈቅዱ በዋናነት ለወጣት ሲቪል መሀንዲሶች ጠቀሜታው የጎላ ይሆናል ብለው በማሰብ ነበር፡፡

ለዚህ ትረካ የሳውንድ ትራክ ወይም የማጀቢያ ሙዚቃ የሰራለት ታዋቂው ሙዚቀኛ ረዳት ፕሮፌሰር አክሊሉ ዘውዴ ነው፡፡ ይህ ትረካ በፓፓራዚ የማስታወቂያ ድርጅት አማካይነት የቀረጻ ስራው የተከናወነለት ሲሆን የስራው ዋና አማካሪ ደግሞ ገነት ደምሴ ናት፡፡ ተወዳጅ የሚድያና የኮሚኒኬሽን ማእከል ይህን በሲዲ የቀረበ ስራ በሲዲ አሳትሞ ለገበያ የሚያቀርብ ሲሆን ወጣት የምህንድስና ተማሪዎችም ጋር እንዲዳረስ ያደርጋል፡፡ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን ከዚህ ቀደም ማለትም ከ1 ወር በፊት በህዳር 15 2011 ‹‹የኤርትራ ጉዳይ..›› የተሰኘውን መጽሀፍ በዲቪዲ አሳትሞ ማስመረቁ ይታወሳል፡፡ ድርጅቱ ከአሁን በኋላም የ3 የሀገር ባለውለታዎችን ታሪክ በዲቪዲ አሳትሞ የሚያስመርቅ ሲሆን በተለይ መጽሀፎችን ወደ ድምጽ መቀየር የሚለው ሀሳብ ላይ አጽንኦት ሰጥቶ እንደሚቀጥልበት ለማወቅ ተችሏል፡፡ እሁድ የካቲት 10 2011 አቶ በየነ ለእነ መላ ቤተሰባቸው የሚታደሙ ሲሆን ትረካው በ7 ደቂቃ በቪድዮ ተቀንጭቦ እንደሚቀርብ ለማወቅ ተችሏል፡፡

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close