Connect with us

Ethiopia

የአድዋ ድል እና ከአጼ ሚኒሊክ ጋር ተያያዝነት ካላቸዉ የአማራ ክልል ታሪካዊ ስፍራዎች

Published

on

የአድዋ ድል እና ከአጼ ሚኒሊክ ጋር ተያያዝነት ካላቸዉ የአማራ ክልል ታሪካዊ ስፍራዎች

የአድዋ ድል እና ከአጼ ሚኒሊክ ጋር ተያያዝነት ካላቸዉ የአማራ ክልል ታሪካዊ ስፍራዎች በከፊል፡-

#ደሴ ሙዚየም

ሙዚየሙ ከደሴ ወደ አዲስ አበባ መውጫ በስተቀኝ የሚገኘውና በተለምዶ ዲቪዥን በመባል ከሚጠራ ቦታ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ በክልላችን ከሚገኙት የተደራጁ ሙዚየሞች ውስጥ አንዱ ነው፡፡

በሙዚየሙ አጼ ሚኒሊክ ለንጉስ ሚካኤል የተበረከተው ስልክ፣ በአድዋ ጦርነት ጥቅም ላይ የዋሉ መሳሪያዎች እና በርካታ ውድ ቅርሶች ይገኙበታል፡፡

#አንጎለላ

አንጎለላ ከተማ ከደብረብርሃን ከተማ በስተምዕራብ 10 ኪ/ሜ ርቀት ላይ የምትገኝ ስትሆን የመሰረቷት ንጉሥ ሳህለ ስላሴ /1805-1840ዓ.ም/ ቤተ መንግስት ፍርስራሽ ሕንፃ ይገኝባታል፡፡

አንጎለላ አድዋ ላይ ጣሊያንን ድል በመምታት ለኢትዮጵያ እና ለመላው ጥቁር ሕዝብ ኩራት የሆኑት ዳግማዊ ምኒልክ እና ፊታውራሪ ገበየሁ(አባ ጎራው) የተወለዱባት ከተማ ናት፡፡

በአድዋ ጦርነት ሲፋለሙ የወደቁት የፊታውራሪ ገበየሁ አጽም ያረፈውም በከተማዋ በሚገኘው አንጎለላ ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡

ይስማ ንጉሥ ለታሪካዊው የአድዋ ጦርነት መነሻ በመሆን ከሚጠቀሱ ምክንያቶች መካከል የውጫሌ ውል ቀዳሚው ነው፡፡

የውጫሌ ውል በንጉሥ ምኒሊክ እና በጣሊያን ንጉሥ ኡምቤርቶ ወኪል ኮንት ፔዮትሮ አንቶሎኒ መካከል በአምባሰል ወረዳ ውጫሌ በሚባል ቦታ ሚያዚያ 25 ቀን 1881ዓ.ም የተደረገ የውል ስምምነት ነው፡፡

የውጫሌ ውል 20 አንቀጾች የነበሩት ሲሆን በኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ ያስነሳው አንቀጽ 17 ነው፡፡

አንቀጽ 17 በአማርኛ “የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ለሚፈልጉት ጉዳይ ሁሉ በኢጣሊያ መንግስት አጋዥነት መላላክ ይቻላቸዋል፡፡” የሚል ሲሆን ቀጥተኛ ትርጉሙም የኢትዮጵያ መንግስት ከፈቀደ/ከፈለገ በኢጣሊያ በኩል ከውጭ መንግስታት ጋር ግንኙነት ማድረግ እንደሚችል የሚጠቅስ ነው፡፡

የአንቀጹ የጣሊያንኛ ትርጉም ግን “የኢትዮጵያ መንግስት ከውጭ አገር መንግስታት ጋር የሚያደርገውን ግንኙነት በኢጣሊያ መንግስት አማካኝነት ማድረግ ይገባዋል፡፡” የሚል ነበር፡፡

ይሄም የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት በቀጥታ በጣሊያን በኩል እንዲከናወን የሚያስገድድ ነበር፡፡

በአንቀጽ 17 አማካኝነት ጣሊያን የውሉን ሀሳብ በጣሊያንኛ በመቀየር የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በመገርሰስ የጣልያን ሞግዚት እንድትሆን ቀዳዳ እያበጀች መሆኑ ነገሥታቱ እና መኳንንቱ ሰለተገነዘቡ የውጫሌ ውልን እንደማይቀበሉት አሳወቁ፡፡

የጣሊያን መንግስት ውሉን ለማፍረስ አሻፈረኝ በሚልበት ጊዜ የውጫሌ ውል እንዲፈርስና ኢትዮጵያ ለማይቀረው ጦርነት እንድትዘጋጅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካበረከቱ ግለሰቦች መካከል እቴጌ ጣይቱ ብጡል ዋና ተዋናይ እንደነበሩ ታሪክ ይናገራል፡፡

በዚህ ጊዜም “እኔ ሴት ነኝ፣ ጦርነት አልወድም፡፡ ግን እንዲህ መሳዩን ውል ከምቀበል ጦርነት እመርጣለሁ፡፡ ይስሙ ንጉሥ!” የሚል ታሪካዊ ንግግር አድርገዋል፡፡ ይሄን ንግግራቸውን ተከትሎም የውጫሌ ውል የተፈረመበት ቦታ “ይስማ ንጉሥ” በሚል ተሰይሞ እዚህ ዘመን ደርሷል፡፡

ይስማ ንጉሥ ከደሴ በወልዲያ መንገድ 60 ኪ/ሜ ርቀት ላይ ከምትገኘው ውጫሌ ከተማ ለመድረስ 7 ኪ/ሜ ሲቀር ከዋናው መንገድ 4 ኪ/ሜ ወደግራ ገባ ብሎ ከአምባሰል ተራራ ግርጌ ይገኛል፡፡

በአሁን ጊዜ በቦታው የቱሪዝም ልማት ስራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡

#ወረኢሉ

ወረኢሉ በደቡብ ወሎ ዞን ከሚገኙ ወረዳዎች ውስጥ አንዷ ናት። የብዙ ተፈጥሯዊ፣ ባህላዊ እና ታሪካዊ ቅርሶች ባለቤት የሆነችው ወረኢሉ ከደሴ 91 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡

ከተማዋ ቀደም ባለው ጊዜ ‹‹ዋሲል›› በመባል ትጠራ እንደነበረ ይነገራል፡፡ አንዳንዶች ግን የከተማዋን መመስረት ከአጼ ምኒልክ ዘመነ መንግስት ጋር ያገናኙታል፡፡

በታሪክ የወረኢሉ ስም ጎልቶ የሚነሳው ዳግማዊ ምኒልክ ለአድዋ ጦርነት የክተት አዋጅ በአሳዋጁበት ጊዜ የሸዋ እና ደቡብ ሰራዊት በአንድ ማዕከል እንዲሰባሰብ የመረጧት ቦታ በመሆኗ ነው፡፡ በዘመኑ ለሰራዊቱ ትጥቅ እና ስንቅ ማዘጋጃ ማዕከል በመሆንም ለተመዘገበው ድል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክታለች፡፡

(ምንጭ፡-የአማራ መገናኛ ብዙሃን ድርጅት)

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close