Connect with us

Ethiopia

ኢትዮጵያዊያንን ባይተዋር ያደረገው አዋጅ

Published

on

ኢትዮጵያዊያንን ባይተዋር ያደረገው አዋጅ | ከበኃይሉ ሚዴቅሳ ፍስኃጽዮን

ኢትዮጵያዊያንን ባይተዋር ያደረገው አዋጅ | ከበኃይሉ ሚዴቅሳ ፍስኃጽዮን

ከሁለት ሳምንታት በፊት የወጣው የስደተኞች ጉዳይ አዋጅ እጅጉን አደገኛ ቢሆንም ማኅበረሰቡ ሲነጋገርበት አልታየም፡፡ የፌስቡክ ማኅበረሰብም እንደተለመደው ግልብ በሆኑ ጉዳዮች ሲጨቃጨቅ ከርሟል፡፡ እንዲህ ያሉ አእምሮን የሚቆነጥጡ ጉዳዮችን ለመወያዬት የሚያስችል ሁኔታ ተፈጥሮ አልታየም፡፡ መንግሥትም ከየትኛው ሕብረተሰብ ጋር እንደተወያየ አይታወቅም፤ አዋጁን እላያችን ላይ ጭኖብናል፡፡

አዋጁ ስደተኞችን ከካምፕ አስወጥቶ ከኢትዮጵያዊያን እኩል በሁሉም ከተሞች እንዲኖሩ የሚፈቅድ ብቻ ሳይሆን፣ የትኛውንም ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ከአገሪቱ ሕዝቦች እኩል እንዲያገኙ የሚያደርግ ነው፡፡በኢትዮጵያ ውስጥ እርሻ፣ ኢንዱስትሪ፣ ጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፎች ላይ እንዲሰማሩ ከመፈቀዱ በተጨማሪ፣ በኢትዮጵያ ያፈሩትን ሀብት ያለ ታሪፍና ቀረጥ ወደ ሀገራቸው ይዘው መሄድ እንደሚችሉም ተደንግጓል፡፡ ከውጭ ሲገቡም ያለ ቀረጥ የትኛውንም ንብረት ይዘው መምጣት ይችላሉ፡፡

አዋጁ ከ1996ቱ ጋር ሲነፃፀር፣ ከላይ የተዘረዘሩትን ጥቅሞች በአንድ ምዕራፍ በመጨመሩ የተለየ ነው፡፡ ተሻሽሏል የሚያስብለው ጉዳይ ያለውም እዚሁ ላይ ነው፡፡ እነዚህን ጥቅሞች ኢትዮጵያ ለስደተኞች መፍቀዷ፣ በዓለማቀፍ ማኅበረሰብ ለገጽታ ግንባታ ይጠቅማታል የሚሉ ሰዎች፣ ከለጋሽ መንግስታትና ተቋማት ገንዘብ ለማግኘት እንደሚያግዛትም ይገልፃሉ፡፡ ይሁን እንጂ አዋጁ አንዳንዶች እንደሚሉት በሩጫ የወጣና ስትራቴጂካዊ ጥቅሞችን ያላስተዋለ ነው፡፡

ይህንን አዋጅ ገቢራዊ ለማድረግ የሚገጥሙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ከወዲሁ የታሰበባቸው አይመስልም፡፡ ለምሳሌ በተለይም ለጋሾች እጃቸውን እንዲዘረጉ ያደርጋል የሚለው ተስፋ ምንድን ነው ማረጋገጫው? መንግሥት ስደተኞችን በኢትዮጵያ ካቆየ በቋሚነት ሊያገኘው የሚችል ገንዘብ አለ…? ለዚህ የሚሆን ከአውሮጳ ሕብረት አለያም ከመንግሥታቱ ድርጅት ወይም ከአሜሪካና ካናዳ ጋር የታሰረ ውል አለ…? ከአንድ ዓመት በፊት የስደትና ከስደት ተመላሾች አስተዳዳር ዋና ዳይሬክተር ዘይኑ ጀማል (አሁን የሰላም ሚኒስቴር ዲኤታ) በአዲስ አበባ በተካሄደ አንድ ስደተኛ-ነክ ጉባኤ ላይ፣ ኢትዮጵያ ከሰማኒያ በመቶ የሚልቀውን የስደተኞች ወጪ በራሷ እየሸፈነች መሆኑን ሲገልጹ ነበር፡፡ ያ አሀዝ አሁን መሻሻል ስለማሳየቱ ይፋ የተደረገ ሪፖርት አላጋጠመኝም፡፡ጉዳዩ አሁንም በኢትዮጵያ ጫንቃ ላይ የቆመ ከሆነ ግን ይሄ አዋጅ ምን ይዞ ጉዞን ያመጣል…

አዋጁ በሩጫ የተዘጋጀ እንደሆነ የሚገባን ስለመዘዋወር መብት የሚዘረዝረውን ምዕራፍ ስናነብ ነው፡፡ ይህ ክፍል፣ ስደተኞች የመኖሪያ ቤት ሰርተው እንዲኖሩ የሚደረገው ተሰድደው በመጡበት አገር አቅራቢያ በሆነ አካባቢ ነው፡፡ የመንግሥት መረጃ እንደሚያመለክተው በኢትዮጵያ ከ30 የሚበልጡ ሀገራት ዜጎች በጥገኝነትና በስደተኛነት ይኖራሉ፡፡ ይህ አዋጅ ግን እነዚህን ሀገሮች ረስቷቸው እዚሁ ከምሥራቅ አፍሪቃ አካባቢ ተሰድደው የመጡ (የሚመጡ)፣ ሰዎችን ታሳቢ ያደረገ መብት ሰጥቷል፡፡የደቡብ ሱዳን ስደተኛ፣ ጋምቤላ እና በአካባቢው ሊሰፍር ይችላል፡፡ ኤርትራዊያንም፣ በትግራይ፣ ሱማሊያዊያን በሱማሌ ክልል… ቤት ሊሰሩ ንብረትም ሊያፈሩ ይችላሉ፡፡ የሶሪያ ስደተኞችስ ? ከየመን የሚመጡትስ/የመጡትስ ? ለአገራቸው ቅርብ የሆነው የኢትዮጵያ አካባቢ የቱ ነው…?

በስደት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት አብዛኞቹ ሰዎች እናቶችና ሕፃናት ወይም መሥራት የማይችሉ አቅመ ደካሞች ናቸው፡፡በተለይ ከደቡብ ሱዳን የመጡ ስደተኞች የእድሜያቸው ስብጥር እንደዚያ ያለ መሆኑን ዓለማቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) ሲገልጽ ከርሟል፡፡ እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ አምራች የሚባሉ አይደሉም፡፡ ከካምፕ ውጭ ወደ ከተሞች ሲበተኑም፣ በኢትዮጵያውያን የተፈጠረን ጥሪት መቀራመት ላይ እንጂ ‹ኢኖቫተር› ሆነው፣ በፈጠራ የታከለ ሥራ መሥራት የሚችሉ አይደሉም፡፡አብዛኞቹም የትምኅርት ዝግጅታቸው ለኢትዮጵያ እሴት የሚጨምር አይደለም፡፡ ይህ አዋጅ አርቆ አስተዋይ አይደለም የሚያስብለው አንድ ነጥብም ይህ ይመስላል፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ ኢትዮጵያ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ስደተኛ ተቀብላለች፡፡ይህ ምናልባትም ካለን የሕዝብ ቁጥር አንፃር ሲታይ በውቅያኖስ ላይ አንድ ሊትር ውሃ የመጨመር ያህል ቀላል ሊሆን ይችላል፡፡ግን ይህ የተለጠጠ መብትን ያጎናጸፈ አዋጅ ተጨማሪ ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ እንዲጎርፉ ሊያደርግ አይችልም…? ይህስ በባላአገሩ ሕዝብና በመጤው መሀል ቅሬታ ፈጥሮ በሂደት መጤ-ጠል አስተሳሰብ ቢጎለብትስ…?እንግዳ ተቀባይ ነኝ ሲል የኖረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ፣መንግሥት ባወጣው በዚህ አዋጅ ምክንያት ይህንን ነባር እሴቱን የሚሸረሽር ነገር አይከሰትም?

በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ያሉ ስደተኛ ጣቢያዎች ተዘግተው ስደተኞች ወደ ማኅበረሰቡ ሲቀላቀሉ፣ በዜጋው ባሕል፣ ቋንቋና ማንነት ላይ የሚያደርሰው መዋጥና ተጽእኖስ (Assimilation) እንዴት ይታያል…?በአዋጁ አንቀጽ 40 ላይ የተቀመጠው ድንጋጌ ስደተኞች በቡድንም ሆነ በተናጠል በአንድ አካባቢ ከሚኖር የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ጋር እንዋኸድ ብለው ቢጠይቁ እንደሚፈጸምላቸው ይገልፃል፡፡ ይሁን እንጂ በሂደቱ የኢትዮጵያዊያኑ ፈቃደኝነት ሊጠየቅ እንደሚችል አይጠቁምም፡፡ ስለዚህ ብልጫ ያለው የኑዌር ስደተኛ ከደቡብ ሱዳን መጥቶ፣ አነስተኛ አኙዋኮች በሚኖሩበት የጋምቤላ ክልል ልዋኸድ ቢል ያለ ኢትዮጵያዊያኑ ይሁንታ ስደተኛው ጥያቄው ተተግብሮለት፣ የአኙዋኮችን ባሕልና ማንነት ታሪክ ሊያደርግ የሚችል ‹ዴሞግራፊ› ሊፈጠር ይችላል ማለት ነው፡፡ እነዚህንና መሰል ጉዳዮችን አለማጤኑ ነው፤ አዋጁን ግርድፍ ሊያስብለው የሚችለው፡፡

የደኅንነት ሥጋት ምንጭ?!
ይህ አዋጅ አንዳች ብሔራዊ ደኅንነትን ሊገዳደር የሚችል ሥጋትንም ያጭራል፡፡ ይኸውም ስደተኛን እንደ ቅዱስ ማኅበር ማየቱ ነው፡፡ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር ደም ያቃባ ቂም ያለባት፣ ከሰሜን አፍሪቃ የሚነሳ የታሪካዊ ባላንጣነት አጀንዳ በተዘረጋበት መሥመር ውስጥ ያለች፣ ከአንደኞቹም ጎረቤቶቿ ጋር የተካለለ ድንበር የሌላት ናት፡፡ ይህ ባለበት ሁኔታ ስደተኛ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ተንቀሳቅሶ ይኑር፤ ሀብትም ያፍራ ብሎ ማወጅ የካይሮ ጆሮ ጠቢዎች መረባቸውን ያስፉ፣ ቂምና ቁርሾ ያላቸው የምሥራቅ አፍሪቃ ታጣቂዎች (ለምሳሌ አልሸባብ) እና አንዳንድ መንግሥታትም ኢትዮጵያን ለማተራመስ በስደተኛነት መልክ ገብተው በባሌም በጉለሌም፣ በመቀሌም በሞያሌም ይንጎራደዱ ማለት ነው፡፡

ስደተኞች በሁሉም የአገሪቱ አካባቢ ተበትነው በሚኖሩበት ሁኔታ፣ ኢትዮጵያ ከአንዲት ጎረቤት ሀገር ጋር ብትጋጭ፣እነዚህ ስደተኞች ለሀገራቸው ወግነው የስለላና የውስጥ አርበኝነት ሥራ ቢሰሩስ? ይህ እኮ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ጊዜ ታይቷል፡፡ የብሔራዊ ደኅንነትን ጉዳይ የሚያወሳስብ ሌላ አጀንዳ ተከሰተ ማለት ነው፡፡

የከፋው ሁሉ ኢትዮጵያ መጥቶ ሀብት እንዲያፈራ የሚፈቀድ ከሆነ፣ በሂደት ሕገ-ወጥ የፋይናንስ ስደት (Illicit Financial Flow) ቢፋፋምስ…? ስደተኞች ኢትዮጵያ ጊዜያዊ መጠለያው እንደሆነች የሚያስብ ስደተኛ፣ ከዜጎች እኩል መብት ተሰጥቶት ቢኖርም ከኢትዮጵያዊያን እኩል ለሀገሪቱ ሊቆረቆርና ሊወግን አይችልም፡፡ ምክንያቱም ይቺ አገር ዘላለማዊ ሀገሩ እንዳልሆነች ያውቃልና፡፡ ታዲያ የፀጥታ ችግር ምንጭ የሆነ ድርጊት ውስጥ (ለምሳሌ ‹መኒ ላውንደሪንግ›) ተሳትፎ ቢያደርግስ እንደሚታወቀው ወደ ኢትዮጵያ የሚሰደዱት የጎረቤት ሀገራት ዜጎች በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚኖር ዘመድ አላቸው፤ገንዘብም ያስልካሉ፡፡ ታዲያ ያ በውጭ ምንዛሬ የሚላክ ገንዘብ በብዛት ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ጎረቤት ሀገራት በቅንነት ሊያዩት ይችላሉ ወይ…? ለምሳሌ ኤርትራ በሐዋላ ከውጭ ሀገራት ገንዘብ ከሚልኩ ዜጎቿ ሁለት በመቶ ቆርጣ ትወስዳለች፡፡ ይህንን በመሸሽ በርካታ ኤርትራዊያን በኢትዮጵያ ባንኮች ገንዘብ አስልከው እዚሁ ንግድ ቢጀምሩ የአስመራ መንግሥት እጁን አጣጥፎ ይቀመጣል ወይ…?

ከደቡብ ሱዳን ቀጥሎ በርካታ ስደተኞች በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩት ኤርትራዊያን ናቸው፡፡ እነዚህ ኤርትራዊያን ደግሞ አብዛኞቹ (ሁሉም በሚያስብል ደረጃ) ወታደራዊ ሥልጠና የወሰዱ የሳዋ ምሩቃን ናቸው፡፡ እነዚህን ሰዎችም ሆነ ለሌሎችን ከካምፕ አስወጥቶ በከተሞች ማሰራጨት፣ የሕዝብን ደኅንነት አደጋ ውስጥ እንደማይጥል ምንድን ነው ማረጋገጫው…? የከተማ ላይ ወንጀል ተስፋፍቶ ዜጎች ወጥተው መግባት ቢቸገሩስ…? እንደ ሱማሊያ ካሉ ሀገራት የሚመጡ ስደተኞችን ተከትለው የሚመጡ ጽንፈኛ አስተሳሰቦችና ገዳይ አጀንዳዎች፣በሕዝብ መሀል መከፋፈልንና እልቂትን ቢዳርጉስ…? ውሻ በቀደደው ነው እኮ ጅብ የሚገባው፡፡

እንደ መውጫ፤
በጥቅሉ አዋጁ ‹‹ኢትዮጵያዊያን እንግዳ ተቀባይ ነን›› የሚለውን ትውፊታዊ ብሂል መነሻ ያደረገ ሆኖ የተዘጋጀ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ለስደተኛው የተለጠጠ መብት በመስጠት በጊዜ ሂደት ቀውስ እንዲመጣ ሊያደርግ በሚችሉ ድንጋጌዎች የተሞላ ነው፡፡ ‹የራሷ እያረረባት› እንዲሉም፣ 25 ሚሊዮን ሥራ አጥ፣ ሶስት ሚሊዮን የውስጥ ተፈናቃይ ያለባት ኢትዮጵያ ከውጭ ሀገር የሚመጡ ስደተኞችን ያለምንም ክልከላና ቁጥጥር ለማኖር ወስናለች፡፡ጉዳዩ እንደ ጥሩ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ተቆጥሮም፣ከፈረንጆቹ ሙገሳና ውደሳን አምጥቷል፡፡ መንግሥትም ‹‹የምዕራቡ ዓለም ወዶልናል›› በሚል ደስታውን እየገለጸ ነው፡፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** የተለያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዝኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close