Connect with us

Africa

ራስ አሉላ አፍሪካዊ እንጂ መንደራዊ ጄነራል አይደሉም

Published

on

ራስ አሉላ አፍሪካዊ እንጂ መንደራዊ ጄነራል አይደሉም

ራስ አሉላ አፍሪካዊ እንጂ መንደራዊ ጄነራል አይደሉም።

ራስ አሉላ ኢትዩጵያዊ ስለሆኑ የኛ ናቸው። እኛ ከሰፈር እና ከዘር በላይ የተሰራነው በራስ አሉላ ነው።

ከስናፍቅሽ አዲስ

የሕወሓትን ታሪክ አከብራለሁ። ወደ ደደቢት መሄድ ያለበት ባንዲራ ወደ አድዋ በመሄዱ አፍራለሁ። የኔ ትውልድ ተወናብዷል።

አድዋን ተጠይፎ አሉላን ማድነቅ የሚቻል መስሎታል። አሉላ የሚወዱት ፌደራሊዝምን የሚጠየፍ የኢትዩጵያ ጌጥ ነው።

ሰሞኑን የህወሓት ወጣቶች ጉዞ አድዋ ብለው ወደ ምኞታቸው የሄዱበት ነው። መንፈሱ ግን ግራ ተጋብቷል። የህወሓትን ባንዲራ ከፍ አድርጎ ራስ አሉላን መዘከር ስመ ጥሩውን የተንቤን ጀግና ማኮሰስ እንጂ ማተለቅ አይደለም።

ለመሆኑ ባለፍት ሃያ አምስት አመታት ራስ አሉላን ለመዘከር ምን ተሠራ? ሀገሩ በሙሉ በመለስ ዜናዊ ስም ሲሰየም ራስ አሉላንም ሆነ እንደ ባሻ አዋሎም ያሉ ጀግኖችን ለመዘከር ማን ነበር ከፊት የቆመው? ህወሃት ትግራይን ይጠላል የምትለው ደርግ ነው ራስ አሉላን እዚህ ትውልድ ልብ አትሞ ያሻገረው።

አድዋ ከእኛ አልፎ ጥቁርን ያኮራው ትርጉሙ መሞትና መግደል ስለሆነ ብቻ አይደለም። አድዋ ጥቁር ለነፃነት አንድ ስለሆነ ነው።

የነ አቦይ ስብሃት ደጋፊዎች ሲሆን ከአቦይ ስብሐት እንደሚቀድሙት አባቶቻቸው ስለ አንድነት ቢቆሙ መልካም ነበር። ሰው ዘመኑንም ውሎውንም ስለሚመስል አልፈርድባቸውም። ራስ አሉላን ግን በሰፈር ማጠር የዘር ኩታ ማልበስ የጠላት እንጂ የወዳጅ ተግባር እንዳልሆነ ታሪክ ያነበበ ሁሉ ይረዳዋል።

አፍቃሪ ምኒልክ የሆኑት የለም ምኒልክ የዓለም ጣዕም ነው ሲሉ ምኒልክ ከአንኮበራውያን በላይ ከኢትዮጵያ ምናብ የሰፋ የምድራችን አንድ ታላቅ ሰው ነው እያሉ ነው። የነ አቦይ ስብሐት ቡራኬ ተቀባዮች ራስ አሉላን በፓርቲ ባንዲራ ሲያከብሩ ማሳነስ ነው። ሲሆን የሚወዱትን ሰው ጨምረው አግነው ያከብሩታል እንጂ እንዴት ካለው ያሳንሱታል። ራስ አሉላ እኮ ከኢትዮጵያ አልፈው ጥቁር የሚያስመኩ አፍሪካዊ ጄነራል ናቸው።

ወጣቶቹን መርቀው ባንዲራ አስይዘው የሸኙት አቦይ ስብሐት ለራስ አሉላ የሚሰማቸውን ስሜት እናውቀዋለን። በወጣቶቹ የተምታታ ሀሳብ በውስጣቸውም ፈገግ ሳይሉ አይቀሩም። አሉላን ለመዘከር አቦይ ስብሐትን መርቀው ሸኙኝ ሲሉ ህዝብ በተሰበሰበበት መድረክ አንድም ቀን ስለ ታላቁ ጀግና አውርተው የማያውቁ የኢትዮጵያን ገናና ታሪክ የሚፀየፍ ናቸው።

አሉላን ወዶ ምኒልክን መጥላት ታሪክ መሸሽ ነው። እኛ ለምኒልክ መታመንን የተማርነው ከራስ አሉላ ነው። የጋራ ታሪኮቻችንን እንደ በጀት ተካፍለን ያሻው ይብላው ያሻው ይድፋው መባባሉ ዛሬ ብቻ ሳይሆን ትናንትና ነገ እንዳይኖረን ያደርገናል። ታሪክ ድርሻችንን አንስተን በልካችን የምንሰፋው አይደለም። የሆነው እውነት ነው። የነበረነው ሀቅ ነው።

የራስ አሉላን ክብር የምንደግፈው ስላስከበሩን ነው። የራስ አሉላን የመንደርና የብሔር ታርጋ የምንኮንነው እሳቸው ለታላቋ ኢትዮጵያ እንጂ ለሰፈር ልጅ ክብር ስላልኖሩ ነው። አሳንሶ መዘከር አብልጦ መናቅ ነው። በራስ ከረጢት ጀግኖቻችንን ለመክተት መሞከር ትርፍ ድካም ነው። ራስ አሉላ ደጃች ባልቻ ደጃች ዑመር ዘርዓይ ደረስ እያልን የምንቆጥራቸው ጀግኖቻችን በሙሉ ከእኛ ከረጢት የሚበልጡ የታላቋ ኢትዮጵያ ጌጥ የአፍሪካ መልካም ታሪክ እውነታዎች ናቸው።

(ከአዘጋጁ፡- ይህ ጹሑፍ የጸሐፊውን እንጂ የድሬቲዩብን ኤዲቶሪያል አቋም አይወክልም)

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close